>

የሰይጣን ፈረሶች “ነፃነት” “ዘረኝነት” “ጥላቻ”... — እኛ ሰዎች ግን ምንድን ነን? (አሰፋ ሃይሉ)

የሰይጣን ፈረሶች “ነፃነት” “ዘረኝነት” “ጥላቻ”…

— እኛ ሰዎች ግን ምንድን ነን?

አሰፋ ሃይሉ
ነፃነት ሚዛን ነው፡፡ አስተውሎትን ይጠይቃል፡፡ የህሊናን ዳኝነት፣ ፍትሃዊነትን ይጠይቃል ነፃነት፡፡ ነፃነት ሚዛኑን ከሳተ፣ ነፃነት በጥላቻ ከደፈረሰ፣ ፍፃሜው መራር ነው፡፡ ነፃነት ማለት የመምረጥ ነፃነት ነው፡፡ ሁሉ ተሰጥቶሃል፡፡ የሚበጅህን የመምረጥ ነፃነቱም አለህ፡፡ ስትመርጥ መንገድህን ነው የምትመርጠው፡፡ ስትመርጥ ድርጊትህን ነው የምትመርጠው፡፡ ስትመርጥ ሞትን ወይም ሕይወትን ነው የምትመርጠው፡፡ አስተውሎት የሌለው ነፃነት፣ ሚዛኑን ያጣ ነፃነት፣ የህሊና ዳኝነት ያልገራው ነፃነት፣ ፍትህን አሻፈረኝ የሚል ነፃነት –  ሰለባዎቹን ያበዛል፡፡ የሚዛን የለሽ ነፃነት ጥላቻው ከተራራዎች የገዘፈ ነው፡፡ የሚያረግፋቸው ሰለባዎቹ ደግሞ እንደከዋክብት የበዙ ናቸው፡፡
በናዚ ጀርመኒ የሆነው ይህ ነው፡፡ ሒትለር፡፡ ሒምለር፡፡ ኤክማን፡፡ ጎብልስ፡፡ ጎሪንግ፡፡ ሔይድሪች፡፡ ሪበንትሮፕ፡፡ እና ሌሎች ጥቂት ሰዎች፡፡ በጣም ጥቂት፡፡ ግን እንደ ሠማይ የገዘፈ ታላቅ ጥላቻን በውስጣቸው የሰነቁ – ጥቂት ሰዎች፡፡ እነዚህ ናቸው የጥላቻን አማራጭ ለሕዝባቸው ያቀረቡት፡፡ እነዚህ ናቸው የአጥፍቶ መጥፋትን አማራጭ ለጀርመናውያን አቅርበው ያሳመኑት፡፡ የእነዚህ ሰዎች አማራጭ ነው ነፃነት ለተሰጠው ሕዝብ ለምርጫ የቀረበው፡፡ እና አሸነፈ፡፡ ሒትለር በ1933 እ.ኤ.አ. ለምርጫ ሲቀርብ ታይቶ በማይታወቅ ታላቅ ሕዝባዊ ማዕበል ነበረ ያሸነፈው፡፡ የሒትለር ምርጫ የጀርመናውያን ምርጫ ሆነ፡፡
ቆይ፡፡ ሁሉ ተሰጥቷችኋል፡፡ የሚበጃችሁን ግን አስተውላችሁ ምረጡ፡፡ ብሎ የሚመክራቸው ባለ ሕሊና ጠፍቶ ነው ወይ? አልጠፋም፡፡ ቁጭት፡፡ ለዘመናት የተከማቸ ጥላቻ፡፡ የጥፋት ነጋሪት፡፡ ቂም፡፡ በቀል፡፡ ያገነገነ ማንነታችንን እናሳያለን፡፡ እና የፈለገው ይምጣ፡፡ የሚል፡፡ የሚል ታላቅ የጥላቻና የጥፋት ነጎድጓድ – የባለ ሕሊናዎቹን ጩኸት ዋጠው፡፡ ሒትለርና ጥቂት ጓደኞቹ ቢያንስ 20 ሚሊየን የሚሆነውን የጀርመን ወጣት ልብ ተቀራመቱ፣ አሸነፉ፣ ገዙት፣ እና የጥላቻቸውን ወንጭፍ ተሸክሞ ነጎደላቸው፡፡
ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይሆናል፡፡ ታሪክ ብዙ ነው፡፡ ህይወት አጭር ናት፡፡ ሁሉንም ታሪክ ለመንገር ዕድሜያችን በቂ አይደለም፡፡ መቆንጠር የሕይወት ህግ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ከክፉውም ከበጎውም መቆንጠር – ታላቁ የሕይወት መርህ ነው፡፡ ከክፉውም አታብዛ – በዝቶ ደምህን እንዳያመረው፡፡ ከጣፈጠውም አታብዛ – ማርም ሲበዛ ይመራልና፡፡ እና በመጠኑ ቆንጥር፡፡ ብዙዎች የሚስቱት ይህን መርህ ነው፡፡ ነፃነት ከመጠን፣ ነፃነት ከልኬት፣ ነፃነት ከህሊና ጋር ካልሆነ – ቆጥሮ መስጠትም፣ ቆንጥሮ መቀበልንም አያውቅም፡፡ ያገኘውን ያግበሰብሳል፡፡ እና ዕዳውን፣ ገፈቱን ያበዛል፡፡
ያ የጀርመናውያን ለከት የሌለው ነፃነት፣ ያ የጀርመናውያን የተሳሳተ ምርጫም፣ የጥላቻን ማዕበል ከተቆለፈበት ታላቅ ሳጥን አውጥቶ በምድራቸው ላይ ዘረገፈው፡፡ እና ጥላቻ፣ እና ጥፋት፣ እና ምታ ነጋሪት፣ እና ስሜት፣ በቀል፣ የደም ጥም፣ የመጠፋፋት ጋኔን – ነፍስ ዘርቶ፣ አካል አውጥቶ፣ ዘር አብቅሎ – ነገሠ በኮስታሮቹ፣ በታታሪዎቹ፣ በጠንካሮቹ በራይኽ ሕዝቦች ምድር! እና እንደማንኛውም አሳቢ እረኛ እንዳጣ ነፃነት – ያ የጥላቻ ገሞራ – እንደ ሰደድ እሳት – በዙሪያው ያገኘውን ሁሉ በላ! እንደ ማንኛውም ለከት የሌለው ምርጫ – ያም የጀርመናውያን ምርጫ – ሰለባዎቹን አበዛ፡፡
የዚያ ሁሉ በዘር አባዜ የተለከፉት፣ እና ዘረኝነትን የመንግሥት ቅርፅ ሰጥተው ያነፁት፣ እና ዘረኝነትን የጦር ኃይል፣ ዘረኝነትን ፍልስፍና፣ ዘረኝነትን የሀገር መተዳደሪያ ህግ፣ ዘረኝነትን ታላቅ አንጡረ-ሃብት አድርገው በዙፋኑ ላይ የተቀመጡት የ20ኛው ክፍለዘመን የጥላቻ ነገሥታት – ሒትለርና ጓደኞቹ – የጥላቻ ገሞራቸውን በአውሮፓ ላይ አፈነዱት፡፡ ጥላቻ እንደ ኮሮና ነው፡፡ የመዛመት ጠባይ አለው፡፡ እና አውሮፓን፣ እስያን፣ አሜሪካን፣ አውስትራሊያን፣ አፍሪካን አህጉራት ሁሉ አዳርሶ – ሌላውን እንተው – ሆነ ተብሎ በሰው ልጅ በቦምብ የጋዩት፣ የተረሸኑት፣ በጅምላ የተጨፈጨፉት፣ በበሽታና በረሃብ ያለቁት፣ የተተዉትና የተረሱት እና የሞታቸውን ምክንያት ሳይጠየቁ ብቻቸውን የፀጥታ ሞት የሞቱት ሰላማዊ ሰዎች ስንት ነበሩ?
40 ሚሊየን ንፁሃን ሰላማዊ ሰዎች፡፡ ጀርመኖችን ራሳቸውን ጨምሮ፡፡ 40 ሚሊየን ንፁሃን ሃይ ባይ የሌለው የጥላቻ ምርጫ ሰለባ ሆኑ፡፡ ተጨማሪ 30 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በተለኮሰው ጦርነት የተማገዱ ንፁህ የሰው ልጆች ናቸው፡፡ ሰው ከሰማይ ወታደር ሆኖ አይፈጠርም፡፡ ንፁህ ሰው ነው ዩኒፎርም ለብሶ፣ መሣሪያ አንግቦ ወደ ወታደርነት የሚቀየረው፡፡ ከዚያም መሐል ከልቡ ለእውነት ነው የምዋደቀው ብሎ የጥላቻ ነጋሪት ጎሳሚ ሆኖ ያለፈው ብዙ ነው፡፡ አሁንም ቆንጠር አድርጎ መዝገን የሕይወት መርህ ነው፡፡ ሁሉንም ቆጥሮ መጨረስ ስለማይቻል፡፡ ታሪክ ብዙ ሆኖ፣ ዕድሜ ትንሽ ስለሆነች፡፡ እና ሌላ ሌላውን እንተወው፡፡ እና ጥቂቱን ብቻ እንናገረው፡፡
ሌላ ሌላውን እንተወው፡፡ ሆነ ተብሎ ዘር ተመርጦ – ሰፋሪ፣ መጤ፣ ስደተኛ፣ በዝባዥ፣ ምስጥ፣ ዶላች፣ ጠንቀኛ፣ መርዘኛ… ወዘተ የሚሉ አጠልሺ ስሞች እየተሰጣቸው ከየሀገሩ እየተለቀሙ ለከባድ የጉልበት ሥራ፣ ለባርነት፣ ለወሲብ ጥማት መወጫ፣ ለምርምር ግብዓትነት፣ ሌላ ቀርቶ የአካል ክፍሎቻቸው ተቃጥለው ለሳሙና መስሪያነት የዋሉትን – በጊዜ የሚያመልጡበት ጥግ ያጡትን – ከጀርመንና ከመላው አውሮፓ ከየሀገሩ የተጋዙትን – በዘራቸው ተለይተው እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ጥቃቅን ነፍሳት በግፍ የተጨፈጨፉትን – 5 ሚሊየን ትውልደ አይሁዳውያንንስ – የእነርሱንስ ግፍ፣ የእነርሱንስ ስቃይ፣ የእነርሱንስ እንባ፣ የእነርሱንስ ጣዕር፣ የእነርሱንስ ርሃብና እርዛት፣ የእነርሱንስ የሚሊየኖች ሞት – ዘረኝነት ያነገሠባቸው አስፈሪ፣ አስቀያሚና የሰውልጅ አዕምሮ ያስበውና ያልመው ዘንድ እጅግ ዘግናኝ የትውልደ እስራኤላውያኑን የዘር ጭፍጨፋንስ ምን እንበለው? የእነ ሒትለር በምርጫ ቅስቀሳ ግለት በታላቅነት ተስፋ ተለውሶ የተነሰነሰ የዘረኝነት መርዝ – እጅግ የከፋው ውጤት – እንበላቸው? የሆነውን ክፋት ቃላት አይገልፀውም!
ከዚህ ሆነ ተብሎ በዘሩ ተመርጦ 5 ሚሊየን የሰው ልጅ ከተጨፈጨፈበት ቀጥሎ ደግሞ – በጅምላ በጦርነት የመጠፋፋት አባዜ ያለቀውየ70 ሚሊየኑ የዓለም ሕዝብ ክፉ እጣ! ይህ ይህ፡፡ ከብዙው መሐል ሲያስቡት እጅግ ይዘገንናል፡፡ በዘረኝነት ጦሱ በአካል የቆሰሉትን፣ ውዶቻቸውን ያጡትን፣ የሕይወት ትርጉም እስከዘላለሙ የጠፋባቸው እና ልባቸው ቆስሎ የቀሩትን ደግሞ – ቤቱ ይቁጠራቸው!
ብዙዎቻችን የአና ዳያሪን አንብበን ይሆናል፡፡ ብዙዎቻችን የዓለም ጦርነቶችን ጉዳቶች አንብበን ይሆናል፡፡ ሰምተንም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ ተነበው የሚያልቁም አይደሉም፡፡ ማለቂያ የላቸውም፡፡ በቅርቡ የዛሬ 2 ዓመት የታተመ አንድ መጽሐፍ አግኝቼ ከናዚ የሞት ካምፕ ከነአባቱ የተረፈ ሰውን ታሪክ አነበብኩ፡፡ መከራ፡፡ መከራ ነው፡፡ የመከራ ታሪክ፡፡ እንባ ሀዘንህን አያጥብልህም፡፡ እርሱ ራሱ ይላል፡፡
“ታሪኬን ስናገር የሚሰሙኝ ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡
እነርሱን ለማበርታት እኔ መንፈሰ ጠንካራ
መሆን ነበረብኝ፡፡ አሁን በመጽሐፍ ታሪኬን
ስናገር አጠገባችሁ አልገኝም፡፡ እባካችሁ
መንፈሳችሁ አይሸበር፣ ልባችሁ በሀዘን አይሰበር፣
አሁን የልጅ፣ ልጅ፣ ልጆች ያየሁ – መንፈሰ
ጠንካራ ሽማግሌ ነኝ፡፡ ያለፈው እንዳይረሳ
ነገርኳችሁ፡፡ ለቂም አይደለም፡፡ ለወደፊቱ
በየትኛውም ስፍራ፣ በማንም ዘር ላይ፣
እንዳትደግሙት፡፡”
ነው የሚለው ከዚያ ሁሉ የመከራ ታሪኩ አልፎ የወጣው ባለ ወርቃማ ልብ ሰው፡፡ ‹‹የነፃነት ሸክም››፡፡ ‹‹ዘ ዌይት ኦፍ ፍሪደም›› – ይሄ ነው መጽሐፉ፡፡ አንብበህ፡፡ አልቅሰህ፡፡ ዝም የምትልበት መጽሐፍ፡፡ ዝም፡፡
የቤተ እስራኤላውያን የዘር ጭፍጨፋ – የሆሎኮስት ትምሀርትና ምርምር ማዕከል በበኩሉ – በ765 ገጾች ቀንብቦ በትልቅ ‹‹የሆሎኮስት ክሮኒክል›› መጽሐፍ ያሳተማቸው የብዙ የናዚ ዘረኝነት የሞት ሰለባ ያደረጋቸው፣ የስቃይ ሰለባ ያደረጋቸው፣ የብዙ የብዙ አሳዛኝ ህጻናቶች፣ እናቶች፣ እህታማቾች፣ ወንድማማቾች፣ ቤተሰቦች፣ አዛውንትና ብዙ በግፈኛ ዘረኞች የረገፉ የትውልደ እስራኤል ሰዎችን ፎቶግራፎችና ታሪኮች አውጥቶታል፡፡ ገጽ ገልጦ ሳያዝን የሚከድን ልብ – የሰው ልጅ ልብ አይደለም በእውነት፡፡ አቤት ግፍ! አቤት ሰቆቃ! አቤት በጥላቻ መታወር! አቤት ዘረኝነት! ዘረኝነት! ዘረኝነት! መልዕክቱ እጅግ የሚገርም ሆነብኝ፡፡
/ዳግም በዚህ ዘመን በሀገሬ የብሶትና የቂም ወሬ ሰንቀው ለጥፋት ላቆጠቆጡ ዘረኞች መከላከያ ቢሆነን – አልተረጉመውም ወይ? እስከዛሬ የሰማነው መከራ መች አነሰንና? እስከዛሬ ያነባነው እንባ መች አነሰንና ሌላን እንባ ይዤ ወደ ልምጣ? እስከዛሬ የሰማነው ጦስ ደግሞ መች አነሰንና! የሚል ሀሳብ ደግሞ መጣና ድል አደረገኝ፡፡ እና ዝም! ጭጭ!/
ብዙ ክፋቶችን አንብቤያለሁ፡፡ ብዙ መልካም ነገሮችንም አንብቤያለሁ፡፡ ከምናገረው በላይ አውቃለሁ፡፡ ከማውቀው ሳወጣ እየቆነጠርኩ ነው፡፡ ሁሉን ቢናገሩት – ሆድ ባዶ ይቀራልና፡፡ ሁሉም ነገር – በልክ ካላደረጉት – አይበጅምና፡፡ እና አሁን በዚህ የናዚ-አይሁድ የዘረኝነት ጥላቻ የወለደው ሰብዓዊ ጥፋት ዙሪያ ካነበብኳቸው እጅግ የገረመኝን አንድ ነገር ቢኖር – ዘረኝነት ሲነግስ፣ ‹‹አብሮ መኖር›› የሚባለው የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ፣ ትልቁ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሀብቱ – እንዴት በአፍታ በንኖ እንደሚጠፋ! አቤት! አቤት! ጉድ እኮ ነው የሚያስብለው! እንዴት ለብዙ ዓመታት በየዕለቱ ጉርብትና፣ አብሮ መኖር፣ አምቻና ጋብቻ የተገነባ የሰው ልጆች ትስስር – ዘረኝነት የሚባል ቫይረስ ድንገት መጥቶ – እንዴት ባንድ ጊዜ ያን ሁሉ የሰው ልጅ ትስስር ይበጣጥሰዋል? እንዴት ለብዙ ዘመን የተገነባን ፍቅር የአፍታ የዘረኝነት ጥላቻ ይንደዋል? ይሄ ነገር ሁልጊዜም ግርርም ይለኛል!
ይሄን የምለው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ትውልደ እስራኤላውያን እንደ አውሬ እየታደኑ በየተለቀሙባቸውና በየተጨፈጨፉባቸው የአውሮፓ ሀገራት ሁሉ – ቢያንስ ለ88 ዓመታት ብቻ ከኖሩበት ከኖርዌይ በቀር፣ ከ300 ዓመታት ላነሰ ጊዜ የኖሩበት አንድም ሀገር አይገኝም ነበረ! እስራኤሎችን ማግለል፣ ማፈናቀል፣ ብሎም ማዋከብና መጤ እያሉ ከየሀገሩ ማባረር፣ ሀብቶቻቸውን መንጠቅ፣ ለአስገዳጅ ጉልበት ማጋዝ በተጀመረበት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1939 ዓመተ ምህረት ላይ የነበረውን የእስራኤላውያንን ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች ጋራ አብሮ የመኖርና የመዋሃድ አሃዝ ምን ያህል ለዘመናት የቆየ እንደሆነ ብናየው የምራችንን ግርም ይለናል፡፡
ግርም ይለናል ብቻ ሳይሆን – ይሄ ማህበራዊ ህይወት፣ አብሮ መኖር፣ ዝምድናና የሀገር ልጅነት የምንለው ድንቅ የሰው ልጅ እሴት ሁሉ – እንዴት እንዲህ ይበንናል? ብለን የሰውን ልጆች ተፈጥሮ ደግመን ደጋግመን ለመፈተሽ መገደዳችን አይቀርም፡፡ ቢያንስ ግን ግራ እንጋባለን፡፡
ለምሳሌ በ1939 ዓመተ ምህረት ላይ ሆነን ታሪካቸውን ስናየው – እስራኤላውያን ከጀርመን ሕዝብ ጋር ተዋህደው ጀርመንን ሀገሬ ብለው መኖር ከጀመሩ 1ሺህ618 ዓመታት አስቆጥረው ነበረ፡፡ ብዙዎቹ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሳይቀር ደች ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜ (በ1939 ላይ) ትውልደ እስራኤላውያን በብዛት በተጨፈጨፉበት በፖላንድ ውስጥ ለ850 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በናዚዎች ከተያዘችው ፈረንሳይ እንደ ውሻ እየተመረጡ ሲታደኑ የነበሩት ትውልደ እስራኤላውያን በዚያን ጊዜ ፈረንሳይን ምድራቸው አድርገው መኖር ከጀመሩ 1ሺኅ936 ዓመታትን አስቆጥረው ነበረ፡፡
ቤተ እስራኤሎች በጣሊያን ኑሮ ከመሰረቱ 2ሺህ100 ዓመታት ሆኗቸው ነበር፡፡ በሮማንያ ለ1ሺህ800 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በግሪክ ለ2ሺህ239 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በሃንጋሪ ትውልደ እስራኤላውያን ለተከታታይ 1ሺኅ900 ዓመታት ኖረዋል፡፡ ለከፍተኛ ሞት፣ መፈናቀልና ስቃይ በተዳረጉባት በኦስትሪያ እስራኤላውያን ቤተሰቦች ለ1ሺህ30 ዓመታት ኖረውባታል፡፡ በሆላንድ ለ800 ዓመታት፣ በቤልጂየም ለ700 ዓመታት፣ በሉግዘምበርግ ለ653 ዓመቶች፣ በኢስቶኒያ ለ600 ዓመታት፣ በላትቪያ ለ400 ዓመታት፣ በሊትዋኒያ ለ600 ዓመታት፣ በቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ ግዛቶች ለ1ሺህ ዓመታት፣ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ግዛቶች እንዲሁ ለ1ሺህ ዓመታት ኖረዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀይላል የኑሮ ቆይታቸው ርዝመት፡፡
እንግዲህ እነዚህን ለመቶዎችና ለሺህ ዓመታት ከየማኅበረሰቡ ጋር ተግባብተውና ተከባብረው የኖሩ ሕዝቦችንና የትውልድ፣ ትውልድ፣… እስራኤላውያን ትውልዶችን ነው ‹‹መጤ!››፣ ‹‹ሠፋሪ››፣ ‹‹ጠንቀኛ››፣ ወዘተ የሚል ቅፅል እየሰጡ ከየሃገሩ ያፈናቀሏቸው፣ የገደሏቸው፣ በባርነት ያጋዟቸው፣ ያሰደዷቸው፣ ያደኑና ያሳደኗቸው፣ የጨፈጨፉና ያስጨፈጨፏቸው፣ አንገታቸውንና ልባቸውን የሰበሩና ያሰበሯቸው! እንዴ!? እኛ ሰዎች ግን ምንድን ነን? የአብሮ መኖር ትርጉም የማይገባን፡፡ ጥላቻ ዘመናትን የሚጋርድብን፡፡ ዘረኝነት ህሊናችንን የሚደፍንብን፡፡ እኮ እኛ ሰዎች ግን ምንድን ነን?
ከዘረኝነት፣ እና ከዘረኞች ጥፋት አንድዬ ይሰውረን!
Filed in: Amharic