>

የቻይናው የቫይረስ ምርምር ተቋምና ፖለቲካ!!!  (ሳምሶም ጌታቸው)

የቻይናው የቫይረስ ምርምር ተቋምና ፖለቲካ!!! 

ሳምሶም ጌታቸው
የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ሲሲቲቪ ቴሌቪዥን ከሁለት ወራት በፊት አካባቢ አንድ ፕሮግራም አስተላልፎ ነበር። ዝግጅቱ በቻይና ሳይንስ አካዳሚ ስር ስለሚገኘው እና 35 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር (ከ1 ቢሊየን ብር በላይ) ያህል ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎበት ስለተገነባው ስለ ዉሃን የቫይረስ ምርምር ተቋምና ሥራው በአጭሩ የሚያስቃኝ ፕሮግራም ነበር። ማዕከሉ ሶስት የምርምር ክፍሎች፣ ሁለት እንስሳት ማከማቻ ክፍሎች፣ አንድ ቫይረስ ማከማቻ ክፍል (virus bank) እና አንድ እንስሳትን ለምርምር መበላለቻ ክፍል ያለው ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ 24 ሳይንቲስቶች ሊሰሩበት የሚያስችል አቅም እንዳለው ትረካው ያትታል።
በፕሮግራሙ ላይ ስለ ተቋሙ ገለፃ የሚያደርጉት ዣንግ ሁዋጁን የተባሉ ተመራማሪ እሳቸውም ሆኑ ሁሉም የስራ ባልደረቦቻቸው ወደ ውስጠኛው የምርምር ክፍል ለመግባት፣ በሁለት ድርብ የተሰራ ጠንካራ መከላከያ ልብስ መልበስና ፈፅሞ አየር በማያስተላልፉ አምስት ክፍሎች ውስጥ ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳሉ። [ስለዚህ ተመራማሪዎቹ በእነዚህ ክፍሎች ሲያልፉ አየር ለመተንፈስ እንደ ባህር ጠላቂዎች አየር መስጫ መሳሪያ ያጠልቃሉ ማለት ነው።] ከዚህ በተጨማሪም ተመራማሪው ስለ ተቋሙ ሕንፃ ዲዛይን ሲገልፁ፤ የምርምር ክፍሎቹ ፈፅሞ አየር እንዳያስተላልፉ ተደርገው እንደተገነቡት ሁሉ፣ ቀሪዎቹ የሕንፃው ክፍሎች ደግሞ አየር ከውጭ ወደ ሕንፃው እንዲገባ እንጂ ከውስጥ ወደ ውጭ ፈፅሞ መውጣት እንዳይችል ተደርጎ የተገነቡ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ። ይህም ምናልባት ቫይረስ ከምርምር ክፍሉ ቢያመልጥ ከአየሩ ጋር አብሮ ወደ ውጭ እንዳይወጣ በማለም እንደሆነ ያብራራሉ።
ይህ ሁሉ ሀተታ የምርምር ተቋሙ በረቀቀ ቴክኖሎጂ ስለ መገንባቱ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት አሰራር ስለመከተሉ ገለፃ ለማድረግ የሞከረ ነበር። ሆኖም ግን የኮሮናቫይረስ ከተቋሙ ነው ያመለጠው የሚለውን ጥርጣሬ ጭራሽ ከማጉላት ያለፈ ጠቀሜታ ያስገኘ አይመስልም። ተቋሙም ሆነ የቻይና መንግስት በቫይረሱ መንሥዔነት የመወንጀላቸውን ነገር በሚችሉት አጋጣሚ ሁሉ ደጋግመው ከማስተባበል አልቦዘኑም። ለምሳሌ በዚህ ሰሞን እንኳ የዚሁ ጥናትና ምርምር ተቋም ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ዩዋን ዢሚንግ በምዕራባውያን መንግስታትና ፖለቲከኞች እየጠነከረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ምንጩ ይሄ ተቋም ነው የሚለውን ክስ አስተባብለዋል። “ይኼ ፈፅሞ የሚሆን ነገር አይደለም። ቫይረስን በላብራቶሪ “አዳቅሎ” ይመረት ቢባል እንኳ አሁን ባለው የሰው ልጆች የአስተሳሰብ ብቃት የሚሞከር እንዳልሆነ ይታወቃል። እናም በዚህ ዘመን ኮሮናቫይረስን በላብራቶሪ ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ምንም ዓይነት የሰው ልጅ ዕውቀትም ሆነ አቅም አለ ብዬ አላምንም” ብለዋል።
“በእርግጥ ሰዎች የቫይረስ ምርምር ማካኼጃው እዚህ ውሃን ውስጥ ስለሚገኝና የመጀመሪያው ኢንፌክሽንም እዚሁ ዉሃን ውስጥ ሪፖርት ስለተደረገ ብቻ ቫይረሱ በዚህ ተቋም የተፈጠረ ቢመስላቸው አይፈረድባቸውም” ሲሉ ዶክተሩ አክለዋል። “ነገር ግን ሆን ብለውና ቢጠየቁ ማብራራት ስለማይችሉት ነገር እየቀባጠሩ ወሬ በመንዛት ሕዝብ የሚያሳስቱ ሰዎችና ተቋማት አሉ” በማለት የኮሮናቫይረስ መነሻውን ከጅምሩ ከቻይና ጋር በማያያዝ የሚታወቁትን ቶም ኮተን የተባሉ የአሜሪካ ሴናተር እና ዘ ዋሽንግተን ፖስተን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ዶክተሩ ሀሳባቸውን በመቀጠል “ይህን የሚያደርጉብን ደግሞ በወረርሽኞችና በአጠቃላይ በምናደርጋቸው ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ በሕዝብ ዘንድ ውዥንብር በመፍጠር ተቃውሞ እንዲነሳብን ለማድረግ ነው” ሲሉ ይኮንናሉ።
በተመሳሳይም የማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑ ሺ ዤንግሊ የተባሉ አንድ ዕውቅ የቫይረስ ተመራማሪ ሴትዮ ደግሞ ቫይረሱ ከእሳቸው ተቋም ስላለመውጣቱ እርግጠኛ ስለ መሆናቸው በነፍሳቸው እንደሚወራረዱ ይገልፃሉ። ከምርምር ተቋሙ መጀመሪያ በቫይረሱ እንደተጠቃ የሚነገረው አንድ የተቋሙ ሰራተኛ እንደሆነ የሚነገረውንም መረጃ ፈፅሞ ስህተት መሆኑንና አንድም የተቋሙ ሰው ከላብ ውስጥ በተነሳ ቫይረስ እንዳልተጠቃ አብራርተዋል። እንደሚባለው ከሆነ እኚህ ሴትዮና የምርምር ቡድናቸው ኮሮናቫይረስ ዉሃንን ገና ከማናወጡ 11 ወራት አስቀድሞ አንድ አደገኛ ሳርስን የሚመስል የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቻይናን ሊመታ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር። ይህን ማስጠንቀቂያ ሴትዮዋና የጥናት ቡድናቸው የሰጡት ከሌሊት ወፎች ላይ ስለሚነሱ ቫይረሶች ጥናት ካካኼዱና አሳሳቢነቱን ከተረዱ በኋላ ጉዳዩ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለው ባሳሰቡበት ጊዜ ነበር ተብሏል።
እነኚሁ የቻይና ተመራማሪዎች ያጤኑትን ያህል የሌሊት ወፎችና የአደገኛ ቫይረሶች ተያያዥነት የዚህን ያህል የከፋ መሆኑ በብዙዎች ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አይመስልም። ውሃን የቫይረስ መመርመሪያ ተቋምን ለመገንባት ዋነኛ መነሻ ነው የተባለው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 እና 2003 የተከሰተውና 775 ሰዎችን የፈጀውን የሳርስ ኮሮናቫይረስ ጥፋት ነበር። የያኔውን ወረርሽኝ ያስከተለው ቫይረስም መነሻውን ያደረገው ከሌሊት ወፎች ነበር። እናም ተቋሙ ለ15 ዓመታት ሲገነባ ኖሮ በይፋ በ2018 ሲከፈት ዋነኛ ዓላማው ገዳይ በሆኑ ቫይረሶች ላይ ምርምር ማካኼድ ሲሆን፣ አደገኛ ቫይረሶችን ተሸክመው ለረዥም ዓመታት ምንም ሳይሆኑ መኖር ስለሚችሉትና ቫይረስ ስለሚያስተላልፉት የሌሊት ወፎች የተፈጥሮ መከላከያ አቅምና ተያያዥ ጉዳዮች ማጥናትም እንደ አንድ ዕቅድ የተያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።
በነገራችን ላይ እኚሁ ተመራማሪ በሌሊት ወፎችና ቫይረስ ላይ በሚያደርጉት ጥናት የተነሳ “የሌት-ወፏ ሴትዮ” (Bat woman) የሚል ቅፅል የተሰጣቸው ሰው ናቸው። እናም እኚህ ዕውቅ ተመራማሪ የኮሮናቫይረስ ገና በተከሰተ ሰሞን የጂን አወቃቀሩን በሶስት ቀናት ውስጥ ተንትኖ በማስቀመጥ ቀዳሚዋ ነበሩ ተብሏል። ነገር ግን ውጤቱ በቅርብ አለቃቸው እንዲታፈን ተደረገባቸው እንጂ። ሴትዮዋና የጥናት ቡድናቸው ከዓመት በፊት በፈረንጆቹ ጥር 2019 ላይ ከዚህ በፊት የተከሰቱትን ሶስት ከባባድ ወረርሽኞችን ማለትም ሳርስ፣ ሜርስና ሳድስ የተባሉትን የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን በማጥናትና በመተንተን ሌላ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ተንብየዋል። የምርምር ጽሑፉ እንደሚለው ሶስቱም ቫይረሶች በዝርያቸው ኮሮናቫይረሶች ሲሆኑ፣ የሁሉም መነሻ ደግሞ የሌሊት ወፎች ናቸው። በዚህም መሠረት ቀጣዩ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ወረርሽኝ ከሌሊት ወፎች ላይ የሚነሳ እንደሚሆን እና መጀመሪያ የሚያጠቃውም ቻይናን እንደሆነ ጽሑፋቸው ያትታል ነው የተባለው።
የአሜሪካ የደህንነት አገልግሎት የኮሮናቫይረሱ ከምርምር ተቋሙ ሆን ተብሎ እንዲወጣና የሚያስከትለውን ውጤት በተግባር እንዲያዩ ለተመራማሪዎቹ ተፈቅዶላቸዋል ስለሚባለውና ውጤቱም ዓለምን ለወረርሽኝ መቅሰፍት ዳርጓታል እየተባለ ስለሚነገረው “መረጃ” ጥብቅና ጥልቅ ምርመራ እያከኼደ እንደሆነ ተነግሯል። የአሜሪካው ፎክስ ኒውስም የምርመራው ውጤት ከሰሞኑ ለትራምፕና መንግሥታቸው እንደሚቀርብና ቻይና በምንም መልኩ ለክስተቱ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባት ከወዳጆቻቸው ጋር ተመካክረው ያሳውቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃ እንዳገኘ ዘግቧል።
ቻይናዎቹ ቫይረሱን እኛ አልፈጠርነውም እያሉ በብዙ መልኩ ማስተባበላቸውን ቢቀጥሉም፣ ትክክለኛው ምንጩ እንዲታወቅ እንፈልጋለን የሚሉና ጣታቸውን ወደ ቻይና የሚቀስሩ ሀገራት ቁጥር ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው። ገና ከጅምሩ አሜሪካንን ጨምሮ እነ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ብራዚልን የመሰሉ ሀገራት ከፍተኛ ፖለቲከኞቻቸው ሳይቀር ቻይና ላይ ጣታቸውን ሲቀስሩ እንደነበር ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል በበኩላቸው ቻይና ስለ ቫይረሱ መነሻና መንስዔ የበለጠ ግልፅ ማብራሪያ መስጠት እንዳለባት በአፅዕኖት አሳስበዋል። በተመሳሳይም የሩሲያ የቀድሞ ጤና ሚኒስትር እና የአሁኑ የሩሲያ የመድኃኒትና የስነሕይወት ጥናት ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ሰው በበኩላቸው፤ በደፈናው ቫይረስ በላብራቶሪ አይመረትም የሚለውን ቀልድ ተትቶ የኮሮናቫይረስ ጉዳይ መነሻ እና ምክንያቱ ላይ ጥልቅ ምርመራ ማካኼድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ታዲያ ኮሮናቫይረስን በላብራቶሪ አምርታዋለች በሚል ውንጀላ በመንገብገብ ላይ ላለችው ቻይና ጥቂት እፎይታን በሚሰጥ መልኩ፣ ከጅምሩ ድጋፉ ያልተለያት የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ በላብ ለመመረቱ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም ሲል ወቀሳውን አጣጥሎላታል። የጤና ድርጅቱ የምዕራብ እሲያ ሪጅናል ዳይሬክተር የሆኑት ታኬሺ ካሴይ ቫይረሱ በትክክል ምንጩ ይሄ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ከእንስሳት ስለመነሳቱ የበለጠ ግምት መያዝ ይቻላል ብለዋል።  የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ በፊት በሰጠው መግለጫ ቫይረሱ አብዛኛው ጄኔቲካል አወቃቀሩ በሌሊት ወፎች ላይ ከተገኘ ቫይረስ ጋር በጣም ቅርርብ እንዳለውና ይህም ቫይረሱ ከእንስሳ ወደ ሰው የተሻገረ ለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣል ማለቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን የመጀመሪያውን የቫይረሱን ተጠቂ (patient zero) በትክክል ለይቶ ማወቅ ካልተቻለ፣ ቫይረሱ ከየት እንደተነሳ እርግጠኛ መሆን አይቻልም የሚለውን የብዙ ተከራካሪዎችን አስተያየት ጤና ድርጅቱ ይቀበለዋል።
በዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅት በሚሰጣቸው መግለጫዎች ሁሉ ለቻይና ወግኗል በሚል በምዕራባውያኑ እየተብጠለጠለ ነው። በተለይ መሪውን ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምን ከመውቀስ ባለፈ በግልፅ ለማሸማቀቅ የሚደረጉ ዘለፋዎችና ትችቶች በየሚዲያዎቻቸው ተጧጡፏል። ምዕራባውያኑ እንደሚሉት ዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከሚወዳደሩበት ጊዜ አንስቶ ቻይና እንዲያሸንፉ በዲፕሎማቶቿ አማካይነት ሀገራትን ውስጥ ለውስጥ አግባብታላቸዋለች። በዚያም ምክንያት ዳይሬክተሩ ከቻይና ጋር ያላቸው ወዳጅነት የጠበቀና ውሳኔዎቻቸው ሁሉ ወደ ቻይና ያደላ ነው ሲሉ ይወነጅላሉ። የዶ/ሩ ለቻይና መወገን ለግላቸው ካስገኘላቸው ጠቀሜታ ባለፈ ሀገራቸው ኢትዮጵያም የጥቅም ተቋዳሽ ሆናለች ይላሉ። ለዚህም እንደ አንድ ማሳያ አድርገው ቴድሮስ ወደ ድርጅቱ ከመጡ በኋላ ቻይና ለኢትዮጵያም ሆነ ለድርጅቱ የምትሰጠው ርዳታ እየጨመረ ለመሆኑ የUNን መዛግብት ማየት ይቻላል በማለት የቴድሮስ መመረጥ ቻይና ድርጅቱንና አመራሩን በጥቅም በመያዝ እንደልቧ እንድትዘውረው አስችሏታል ሲሉ ይከሳሉ።
Filed in: Amharic