>
5:13 pm - Sunday April 19, 8764

ወገናዊ ጥሪ! ለዋኖቻችን፣ ለታሪክ ምሁራን እና  ለግብርና ምርምር ባለሙያዎች (ከይኄይስ እውነቱ)

ወገናዊ ጥሪ

 

ለዋኖቻችን፣ ለታሪክ ምሁራን እና  ለግብርና ምርምር ባለሙያዎች

 

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያና ሕዝቧ ጥንትም ዛሬም የሚመኩት በፈጣሪያቸው ነው፡፡ ከውስጥም ከውጭም ጦርነቱ ቀላል ባይሆንም ወደፊትም ይኸው እንደሚቀጥል አምናለሁ፡፡ በዚህች ምድር የበቀሉትም ሆነ የአገራችንና የእግዚአብሔርን ቁርኝት በሚገባ ተረድተው ከውጭ መጥተው ዐረፍተ ዘመናቸው እስኪገታ የኖሩባትን ምድር በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ በቅድስናቸው የቀደሱ አባቶቻችንና እናቶቻችን በዕውቀታቸው በጥበባቸው ተመክተው አያውቁም፡፡ ዕውቀትና ጥበብ የባህርይ ገንዘቡ ከሆነው አምላካቸው በጸጋና መንፈሳዊ ተጋድሎ ያገኙት መንፈሳዊ ሀብት በምንም የማይተመን ሆኖ ሳለ አምላካቸውን መስለውና አክለው፣ አትኅቶ ርእስንና ‹ንዴትን› ገንዘባቸው አድርገው ለትውልድ በቊዔት ያለው ሥራና ቅርስ ትተው በክብር ዐርፈዋል፡፡ በዚህ ረገድ ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ያላት ድርሻ ግዙፍ ነው፡፡

ዛሬ ያለነው ትውልዶች በስም ካልሆነ በቀር (በስምም የነሱ ልጆች ተብሎ መጠራትን አልፈልግም ያለው ቊጥሩ ቀላል አይደለም) በመንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ተጋድሎ ክብርና ኩራት የሆኑንን አባት እናቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያስረዳ አንዳች ምስክር የለም፡፡ ገሚሱ እነርሱ የገነቡትን ያፈርሳል፤ ገሚሱ ደግሞ እነርሱ በጣሉት መሠረት ላይ አንዲት ጡብ ሳያኖር በባዶ ኩራት ተወዝፏል፡፡

ኻያ አራት ሰዓታት ስብሐተ እግዚአብሔር የሚቀርብባት ኢትዮጵያ ዛሬ ለቸነፈር ተጋልጣለች፡፡ ልጆቿ ዓመፃን ገንዘብ አድርገን፡፡ ቤተመንግሥቱም፣ ቤተክህነቱም፣ ቤተመስጂዱም፣ ሕዝቡም/የየእምነቱም ተከታይ ተካክሎ ስለበደለ ከሥጋዊውም ከመንፈሳዊውም ከሁለት ያጣ ሆነናል፡፡ ግን እግዚአብሔር ጨርሶ የተወን አይመስለኝም፡፡ እሱ የሚያውቃቸው ጸሎታቸው መንበረ ጸባዖት የሚደርስ አባቶችና እናቶች ስላሉን፣ ወረርሽኙም ‹‹የምንማርበት ከሆነ›› ገሥፆን ያልፋል፡፡ ከዛስ በለመድነው መንገድ (business as usual) እንቀጥላለን? እስካሁን ከጥፋትና ስህተት የመማር በጎ ልምድ የለንም፡፡ እነዚህ ጥፋቶችና ስህተቶች በማንመልሰው ጊዜ፣ በሕዝብ ሕይወት፣ አካል፣ ነፃነት፣ ባገር ዕድገትና ልማት፣ የአገር ህልውናን እስከመፈታተን የሚያደርስ  መጠነ ሰፊ መሥዋቶችን አስከፍለውናል፡፡ የበቃን አይመስልም፡፡ በርካታ መልካም ዕድሎች በድንቁርና፣ በትእቢት፣ በስግብግብነት መክነው መና ቀርተዋል፡፡ ከፍ ብዬ ‹‹የምንማርበት ከሆነ›› የሚለውን ቃል በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ያደረግኹት ‹መማር› ያለውን መንታ ትርጕም ለማመልከት ፈልጌ ነው፡፡ አንድም አምላካዊ ምሕረትን/ይቅርታን ማግኘት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርትን ለማመልከት ነው፡፡ ትምህርት ለማወቅ ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ እውነት ላይ ለመድረስ ነው፡፡ እውነቱን የሚበጀውን ተረድቶ ተገንዝቦ ስህተትን ለማረም፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ የጠመመውን ለማቅናት ነው፡፡ 

ዛሬ በኢትዮጵያችን ከጠፋውና ከተበላሸው ሀገር-በቀል ዕውቀት፣ ጥበብ፣ በተለይም ብሔራዊ ታሪክ፣ ብሔራዊ ምልክቶች፤ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሕይወት በጽሑፍና በቅብብሎሽ ሲተላለፉልን ከቈዩ ሥርዓቶች፣ ትውፊት፣ የእሤት ሥርዓቶቻችን፣ ቅርሶቻችን፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት/ዲፕሎማሲ፣ ንግግራችንና ጽሑፋችን ጭምር ወዘተ. ይልቅ ቀረን የምንለውን መቊጠር የሚቀል ይመስለኛል፡፡ የእናት አባቶቻችንን አደራ የበላን ትውልዶች በመሆናችን፡፡ 

አንዳንዶቻችን የአገር ህልውና ከውጭ ከሚመጣ ጠላት ጋር በሚደረግ የጦርነት ፍልሚያ ወይም በርስ በርስ ጦርነት ወይም የዘመኑ መንደርተኞች ባሰኘን ጊዜ ተገንጥለን የመንደር ‹መንግሥታትን› እንመሥርታለን በሚሉት ዛቻ ብቻ የሚጠፋ ይመስላቸዋል፡፡ ሃይማኖት፣ ባህል፣ የማንነት መታወቂያ ብሔራዊ ምልክቶቻችን፣ ታሪክ፣ መልካም እሤቶቻችን ወዘተ. ቀስ በቀስ ተሸርሽረው ካለቁ ባዷችንን እንቀራለን፡፡ ቀፎ ታቅፎ መቀመጥ ይከተላል፡፡ እነዚህ ጥፋቶች ከሚያሰጓቸው ዜጎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡

ዛሬ ለታላላቆቼ ለማሳሰብ የምፈልገውና ትምህርት÷ ንባብ÷ ልምድና ዕድሜ ያስተማራችሁንና በጥበብ የለዘበ ምክራችሁን እንድታካፍሉን የምፈልገው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ ዘርፈ-ብዙ የሆኑ የአገራችን ችግሮች በተናጥል የሚፈቱ ባይሆንም፤ ሕዝባችን ግን በተለያዩ ጊዜ በአገዛዙ እና በእሱም በሚደገፉ ተረኞች ዘላቂ ውጤት ሊኖራቸው የሚችሉ አገራዊ ጥፋቶች ሲፈጸሙ እና አንዳንዶቹም ከመፈጸማቸው በፊት መረጃ ሲደርሰን ለሕዝባችን እውነቱንና ትክክለኛውን መረጃ በማስረጃ አንጥሮ በማውጣት ማሳወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የኔ ቢጤ አላዋቂም ዘባርቆ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ ከመክተትና ከስህተት መታደግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በዚህም መሠረት ሰሞኑን ሁለት ርእሰ ጉዳዮች ጎልተው እየተነሱ ነው፡፡

1ኛ/ የዓፄ ምንይልክ ቤተመንግሥት መግቢያ ላይ የዐቢይ አገዛዝ በአንበሳ ምስል ምትክ ያስቀመጣቸው ግዙፍ ዖፈ ጣዎሶች ምስል እና የአንበሳ ተምሳሌትነት በኢትዮጵያ፤ በዚህ ረገድ አቶ ገለታው ዘለቀ ጥሩ ምልከታውን አካፍሎናል፡፡

2ኛ/ በሽግግር ላይ ያለ አገዛዝ (ዐቢይ በገዛ ፈቃዱ አሸጋግራችኋለሁ ሲል ተሰምቷልና) የሥልጣን ዳር ድንበሩ እስከምን ድረስ ነው?

3ኛ/ አወዛጋቢ ሆኖ የቈየውን፣ የዘረመል ምህንድስና በሚባል ሳይንሳዊ ዘዴ በመጠቀም የዘረመል ይዘታቸውን በማዳቀል እንዲቀየሩ የሚደረጉ ሰብሎችን/ዕፅዋትን (ዘዴው እንስሳትን ይጨምራል) (Genetically Modified Organisms/GMO) በሚመለከት አገዛዙ እስካሁን ተይዞ ከቈየው ነባር አቋም በተለየ፣ በዚህ መልኩ የሚዘጋጁ ዘሮችን በመጠቀም ሰፋፊ የንግድ እርሻዎች በውጭ (አሜሪካ) ‹ኢንቨስተሮች› እንዲካሄዱ ፈቃድ መስጠቱን፤ በዚህም አ.አ. የሚገኘው በአሜሪካ መንግሥት የግብርና ሚኒስቴር የውጭ ግብርና አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ የተሰማው መሆኑን የሚገልጽ መረጃ “Ethiopian Observer” በተሰኘ ምንጭ ተገልጾአል፡፡ 

የመጀመሪያ ሁለት አርእስተ ጉዳዮችን በሚመለከት ከዋነኞቻችን መካከል የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያም እና ሌሎችም በስም ያልጠቀስኳችሁ፤ ከታሪክ ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የታሪክ ምሁራን አስተያየት እንድትሰጡበት፤

ሦስተኛውን ርእሰ ጉዳይ በሚመለከት በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጋችሁ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ አስተያየታችሁን እንድትሰጡበት፤

ታናሽ ወንድማችሁ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic