>

ኢትዮጵያና ከ1966ቱ 'አብዮት' በዃላ  የተፈራረቁ መንግሥታት ጠባይ (ናኾም ውብሸት)

ኢትዮጵያና 1966አብዮትበዃላ  የተፈራረቁ መንግሥታት ጠባይ

 

ናኾም ውብሸት

 

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት ጨምሮ፣ ከዚያም  በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ  መንግሥታት ኹሉ፣ መንግሥታዊ አስተዳደራቸውን ማዕከል ያደረጉባቸው፣ ሦስት መሠረታዊ የኾኑ፣ ሳይነጣጠሉ  ይሠሩባቸው የነበሩ ሕዝባዊ እሴቶች  ነበሩዋቸው።እነሱም ሃይማኖት፣ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት(Nationalism) እና ባሕል (በውስጡ ቋንቋን፣ ታሪክን እንዲኹም  ሀገራዊ ልማዶችን ጨምሮ የተጠቀለሉበት) ናቸው።

 

ደርግ

ከድኅረ 1966ቱ ‘አብዮት’ ወዲኽ የተፈራረቁት ሦስት መንግሥታት፣ ያኹኑን ጨምሮ እነዚኽን  ለረጅም ጊዜ የኖሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥታት ይሠሩባቸው የነበሩትን የኢትዮጵያን ሕዝብ  ማንነት የቀረጹና የኢትዮጵያዊነት መለያ የነበሩትን ሕዝባዊ እሴቶች፣ አሟልተው ያልተቀበሉና ያልተገበሩ  ኾነው እናገኛቸዋለን።  ከእነዚኽ ሦስት መሠረታዊ  እሴቶች አንጻር፣ ሦስቱን መንግሥታት ስንመረምራቸው፣ የሚከተለውን ሐቆች ልናወጣ እንችላለን።

የደርግ መንግሥት፣ እራሱን ከሶቭየት ሶሽያሊስት ጎራ  ከመደበበት ጊዜ ጀምሮ   የተዋሰውን የሶሻሊስት አይዲዎሎጂ፣ የአገዛዙ ዋና መርሑ አድርጐ በመነሳት፣ በባሕልና ቋንቋ በኩል ዐዳዲስ ሶሻሊስታዊ ባሕሎችን ለማስተዋወቅ ቢጥርም፣ ነባርናቀደምት ባሕልን እምብዛም የሚቃረኑ ድርጊቶችን አልፈጸመም። ቋንቋን በተመለከተ፣ ጥሩ ሊባል የሚችል፣ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል። የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ፣ ለዚኽ ጥሩ ምሳሌ ሊኾን ይችላል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሉዓላዊነትንበተመለከተም፣ የኢትዮጵያን ብሔረተኝነት(Ethiopian Nationalism)ን  ከሶሻሊስት መርሖዎች ጋር አጣጥሞ ለማጐልበትና ለማሳደግ፣ ብዙ ጥሯል፣ የኢትዮጵያ  ብሔረተኝነት በኹሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ልብ ውስጥ እንዲነሳሳ ሠርቷል።  ይኽ ጥረቱለ17ት ዓመታት የፈጸማቸውን ይቅር የማይባል ግፍና በደል   ባያስረሳም የሀገር ሉዓላዊነት እና ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ላይ ያራምደው  የነበረው አቋም እስካሁን ድረስ በሕዝብ ዘንድ እውቅና ያሠጠው ነው። በአንጻሩ የደርግ መንግሥት፣ የኢትዮጵያሕዝብ መልክ የኾነውን  ሃይማኖት በመካድና  በማዳከም፣ ብሎም ለማጥፋት የሚቻለውን ኹሉ በማድረጉ፣ ከሕዝብ ጋር ልብ ለልብ ሳይገናኝ፣ የሶቭየት ኅብረት ውድቀትን ተከትሎ፣ አየር ላይ  ከተንሳፈፈበት የሶሻሊስት አስተሳሰብ  ማማ ላይ የሀገሩንአንድነትና ዳርድንበር እንኳን ማስጠበቅ ሳይችል ለውድቀት ተዳርጓል።

ወያኔ-ኢህአዴግ

የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት በተራው ከሦስቱ ጥንታዊት ኢትዮጵያ መንግሥታትና ሕዝብ  መገለጫዎች ከኾኑት ኹለቱን  ሃይማኖትና ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን፣ ክፉኛ  ሲዋጋ የኖረና የኢትዮጵያ ሕዝብን ተቀባይነት እስከ መጨረሻው እድሜውሳያገኝ፣ ሕዝብ ዓይንኽን ላፈር ያለው መንግሥት ነበር። የወያኔ መንግሥት፣ በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን ሲያንቋሽሽና ሲያዳክም፣ የእርስ በእርስ ጎሳን ከጎሳ የሚያጋጩ  ሴራዎችን   ሲጎነጉንና በዋነኛነት የጎሳ ፖለቲካን ሲያራምድ የነበረ ነው። ለዚኽም ዋነኛ ማስረጃ የሚኾነው፣ ሀገሪቷን በጎሳ በመከፋፈልና ድንበር በማከፋፈል፣ ለእያንዳንዱ ብሔረሰብ፣ የብሔር ፖለቲካን የሚያራምዱ፣ ታማኝ  ድርጅቶችን በመፈልፈል፣ ጎሳና ቋንቋን መሠረት ያደረገ፣ ፌደራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን  መመሥረቱ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ ከጥንስሱ፣ ልክ እንደ ደርግ የሶሻሊዝም አይዲዎሎጂ ፅንሰሐሳብ  አቀንቃኝ ስለነበረ፣ ለሃይማኖት ቦታ የለውም ነበር። ሃይማኖትን ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም ካልኾነ በስተቀር፣ እንዲዳከምና ብሎም ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ፣በረቀቀ መንገድና በትጋት  ሲሠራ ኖሯል። ለዚኽም ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የቤተክርስቲያን አስተዳደር መሪነቱን፣  ለፖለቲካው  ታማኝ በሆኑ

ከአሜሪካ ባስመጣቸው ጎሰኞች እና መናፍቃን በማስያዝ፣ ቤተክርስቲያንን ከውስጥ ኾኖ የማፍረስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱ ነው። ይኽ ዘዴ ወያኔ የፈጠረው ሳይኾን፣ ከፈረንጅ አለቆቹ ግሎባሊስቶቹ  የቀዳው ነው። የኔኦሌበራል ግሎባሊስቶች(Neoliberal Globalists)፣ የካቶሊክን ቤተክርስቲያን አዋርደውና ቅሌት ውስጥ ከተው፣ ከአውሮጳ ምድር  እንዲኮሰምን ያደረጉት፣ ከውስጥ መናፍቃንን ሰግስገው  በማስገባትና ሃይማኖቱ የማይፈቅደውን ኹሉ፣ እነዚኽ የተሰገሰጉ መናፍቃን እንዲፈጽሙበማድረግና ድርጊቱን ወደአደባባይ፣ በመገናኛ ብዙኃን በዘመቻ መልክ በማውጣት፣ የእምነቱን ተከታዮች አንገት አስደፍቶና አሳፍሮ  ከሃይማኖታቸው እንዲርቁ በማድረግ ነው።   ወያኔ፣ በዚኽ ፀረ ሃይማኖት እርምጃው፣ በየቤተክርስቲያናቱ አስተዳደርቦታዎች ላይ፣ መንፈሳዊ ዓላማን የሳቱ፣ ገንዘብና ንዋይን የሚያፈቅሩ፣ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ አድርጓል። ለዚኽ ማስረጃ  የሚኾነው፣ በወያኔ ዘመን፣ ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ውጪ በንግድሥራ መጠመዷ ነው።ለዚኽ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ  በየቤተክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ የተገነቡ፣ ለንግድ የዋሉ ሕንፃዎች፣ ኹነኛ ምስክሮች ናቸው።

  የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት፣ በእስልምና ሃይማኖትም ላይ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የተከተለውን የጥፋት መንገድ፣ በተመሳሳይ አራምዷል።

በባሕል ረገድ፣ አንዳንድ ጎጂ ባሕሎችን፣ በተለይ በገጠር ሴቶች ላይ  ይደርሱባቸው የነበሩት ጎጂ ባሕላዊ ግዴታዎችን፣ ሕግን በማወጅና በማስከበር፣ ብዙዎቹን  ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ችሏል። ከነዚኽ ውጤታማ ሥራዎቹ፣ እንደ ምሳሌሊወሰድ የሚችለው፣ ልጃገረዶችን ወደትምህርት ቤት እንዲመጡና እንዲማሩ የተደረገው ጥረት፣ በብዛት ያሳየው ስኬታማነት ነው።

በሌላ በኩል፣ በወያኔ ኢህአዴግ መንግሥት፣  ከፍተኛ የባሕል ውድመት የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊ የኾኑ  ባሕላዊ እሴቶች፣ ብዙ ናቸው ከነዚኽም ውስጥ፣ በጥቂቱ ለምሳሌ ብንወስድ፣ ከፍተኛ የሞራል መላሸቅ፣ ጎሰኝነት፣ ልክ ያጣ ስግብግብነት፣ እራስወዳድነት፣ ዐይን ያወጣ ጉቦኝነት፣ ከዳተኛነት፣ አድርባይነት፣ ይሉኝታ ቢስነት፣ ፍርሃትና ወኔ ቢስነት፣ ልመና፣ ነውረኝነት፣ ሴተኛ አዳሪነት መስፋፋት  ይጠቀሳሉ።  እነዚኽ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አስጻያፊ የነበሩ ምግባሮች፣ በወያኔ ኢህአዴግ ዘመን ክፉኛየተስፋፉበትና የተንሰራፉበት ጊዜ ነበር።

ኦዴፓ-ኢሕአዴግ(ብልጽግና)

አኹን በሥልጣን ላይ የተቆናጠጠው ኦዴፓ መራሹ ኢሕአዴግ(ብልጽግና) መንግሥት፣ እንዲኹ በደፈናው ሲያዩት፣ ሦስቱንም የኢትየጵያ ሕዝብ እሴት ምሰሶዎች(pillars)  ባሕል፣ ሃይማኖትን እና ኢትዮጵያዊ  ብሔረተኝነትን ለማቀፍ እየታተረ ያለይመስላል።  ነገር ግን  ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ነው ለማለት የሚያስደፍር፣ ከሦስቱም  እሴቶች ጋር፣ የጠበቀ ግንኙነት የለውም። ለዚኽም ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው፣ የቀድሞውን የለየለት ፀረ አንድነት ወያኔ መራሽ መንግሥት ያወጣውን አዋጅ  ፈለግበመከተል፣ የብሔራዊ  ማንነት ዋነኛ መገለጫ የኾነውን፣ ሕዝብ የሚወደው ከጥንት ጀምሮ የተላለፈን የነጻነት   ብሔራዊ አርማ  ንጹሕ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ፣ በሀገሩ ላይ እንዳይውለበለብ በሕግ ማገዱ ነው።  ዜጎች የሚወዱትን፣ኢትዮጵያዊነታቸው የሚገለጥበትን ሰንደቅ ዓላማን፣  ለበዓላት ማድመቂያ እንዳይዙ ጭምር ከልክሏል። የወያኔ ኢሕአዴግን ባንዲራ ጨርቅ ነው!” ያለውን ስናስታውስ፣ የአኹኑ ኦዴፓ ኢሕአዴግ-ብልጽግና ደግሞ  መላ የኢትዮጵያ አርበኞች፣ ጀግኖችአባቶች በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ከጠላት ወረራ ጠብቀው ያቆዩዋትን፣ የነጻነት ምሳሌ የኾነችውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን፣ ከጐሳ ድርጅት አርማ ጋር፣ እንዲኹም ከተመሠረቱ ጥቂት መቶ አመት  ብቻካስቆጠሩ የፈረንጅ ሀገራት  ባንዲራ ጋር በማወዳደር እና በማነጻጸር፣ ባንዲራ ሊቀየር ይችላል! ሊቃጠልም ይችላል! ሲል፣ ለኢትዮጵያ ባንዲራ ያለውን ዝቅተኛ ግምት እና ስሜት አልባነት መግለጹ ነው።

ባሕልና ቋንቋን በተመለከተ፣  የኢትዮጵያን ሕዝብ ከኖረበትና በቋንቋ ከሚያስተሳስረው አማርኛ ቋንቋ ለማለያየት፣ አደገኛ የቋንቋ አጠቃቀምና የቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ በሀገር ደረጃ ለመዘርጋት ዝግጅት እያደረገ ነው። መጪው ትውልድ በአንድሀገር እየኖረ፣ በቋንቋ የማይግባባበትን ኹኔታን በመፍጠር፣ የጎሳና ቋንቋ ልዩነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደመለያየት የሚያደርሰውን የኢትዮጵያን የሥራ ቋንቋ ወደ  ስድስት ለማሳደግ ድንጋጌዎችንም እያዘጋጀ  ነው።

ሃይማኖትን በተመለከተ እንዲኹ ላይ ላዩን ሃይማኖትን አቻችሎ ለማቀፍ  የተዘጋጀ ቢመስልም፣ በተቃራኒው  የሃይማኖት ግጭቶችን ለሚያባብሱ  ለጎሰኞች እና ከውጪ ድጋፍ ለሚያገኙ አክራሪ ሃይማኖተኞች አሉታዊ ነፃነትን(Negative-freedom)በመስጠት፣ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል፣ የሃይማኖት ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ኾኗል።  ለዚኽ ማስረጃ  የሚኾነው በጅጅጋ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረር ላለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ ሲደርስ የነበረው የቤተክርስቲያን መቃጠልና የቀሳውስት ግድያነው።  እዚኽ ላይ፣  መንግሥት  ይኽን ኹሉ ግፍና ወንጀል  አይቶ እንዳለየ ያሳለፈበት ምክንያት፣ መንግሥት  እግሩ ሥልጣን ላይ በወጣ ማግስት  ጀምሮ የጎበኙትና የጎበኛቸው የዐረብ ሀገራት ካበረከቱት የቢሊዮን ዶላር  ሽልማትና ብድር  ከሚያስከትለው ድብቅ ተጽእኖ  ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይገመታል።

ኮሮና ቫይረሰን በተመለከተ ኢትዮጵያን የሚመራው ኦዴፓ መራሹ ኢሕአዴግ-ብልጽግና ሳያውቀውም ይሁን ፣ ያወቀ እየመሰለው፣ የግሎባሊስቱን ኤሊት ቡድኖች እኩይ አጀንዳዎች አንዱ  የኾነውን ፀረ-ሃይማኖት አጀንዳ ኮሮና ቫይረሰን ስርጭት አስታከው በኢትዮጵያ  ላይ እንዲተገብሩ  እየተባበራቸው ይገኛል።  እነዚኽ ግሎባሊስቶች ልክ ኢቦላና ኤችአይቪ ቫይረሶች ላይ እንዳደረጉት ኹሉ፣   በፋርማ ካምፓኒዎች (GAVI vaccine alliance group) ኽብረት በቢልጌትስ መሌንዳ ፋውንዴሽን(BMGF) መሪነት የኮሮና ቫይረስንም የባለቤትነት መብት(patent right)  በመውሰድ፣  በገንዘብ  በሚደጉሟቸው በቻይና ሁዋን ቫይሮሎጂ  ላቦራቶሪዎች እንዲሁም አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ካሮላይና በሚገኙ ቫይሮሎጂ ላቦራቶሪዎች ውስጥ  የቫይረሱን ጸባይና ውስብስብነት ለማሳደግ  ኤችአይቪ ኤለመንት ተጨምሮበት ወደ ሕዝብ በመልቀቅ፣   የዓለምን ትልልቅ  መንግሥታት አሜሪካንንና ግሬት ብሪትን  ፖፑሊስት መንግሥታትን ጨምሮ  የዓለምን ሕዝብ እያስጨነቁት ይገኛሉ።  በባለቤትነት በሚቆጣጠሩዋቸው ኢንተርናሽናል ሜዲያዎች  እንዲኹም እንደ ጐግል፣ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ዩቲዩብ ያሉ ግዙፍ የዲጂታል ኢንፎርሜሽን ማሰራጫ ፕላትፎርሞች በተቀናጀ መልክ በመጠቀም ለነሱ የሚመቹ  በፕሪዲክቲቭ ሞዴል ስታትስቲካዊ መረጃዎች  እንዲኹም  ሳይንቲፊክ ኮንሰንሰስ በሚሉት አዲሱ አስተሳሰብ የሚፈበርኩትን ሳይንሳዊ ዳታና መረጃዎች  በማጥለቅለቅ  የዓለምን መንግሥታት ለ7.5 ቢሊየን ሕዝብ የሚኾን አስገዳጅ  ቫክሲን ግዢ እያንዳንዱን ሰው መከታተያ ባዮሜትሪክ መከታተያ ሲሰስተም ID2020  በጀት እንዲመድቡ ለማስገደድ እየሠሩ ነው።  በዚኽ ዘዴ ከዚኽ ቀደም እ.ኤ.አ በ2009 የስዋይን ፍሉን  H1N1  ስርጭት ለመግታት  የሚውል  ቫክሲን ዴቨሎፕመንት በጀት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያለአግባብ  እንዲመድቡ አድርገው መንግሥታትን አቅልጠዋቸዋል። ለመንግሥታቱ ኪሣራ ዋነኛ ተባባሪ የነበረው ግሎባሊስቶቹ አኹንም ድረስ እጅ አዙር እስፖንሰር እያደረጉ የሚያሽከረክሩት የዓለም ጤና ድርጅት/WHO አንድ ሶስተኛው የዓለም ሕዝብ በቫይረሱ ሊጠቃ ይችላል ብሎ ያወጣውን የተሳሳተ መረጃ በመጠቀም ነበር።

ይኽን የመሰለ የዓለም ሀገራትን ኹሉ ኢኮኖሚ ያናጋ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የግሎባሊስቶች ማጭበርበር እና የታላላቅ መንግሥታትን መጭበርበር ኹኔታን ስንመለከት፣ በአፍሪካ መንግሥታት አቅም እነዚኽን ግሎባሊስት ዲፕ ስቴት የሚሏቸውን ኃይሎች፣ መጋፈጥ እንዴት ከባድ እንደሚኾን መገመት አያስቸግርም። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አቅምንም ስንፈትሽ  ኢትዮጵያ ላይ እነዚኽ ግሎባሊስት ኃይሎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመከላከል የሚያስችል የደረጀ የቢሮክራሲ አቅምም ዝግጅትም እንደሌለው እንረዳለን። ስለኾነም  ያዘዙትን ሳያቅማማ  ከመፈጸም ይልቅ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ የሚገኙ በኽክምናና በሌላ የሞያ ዘርፎች ብዙ ልምድና እውቀት ያላቸውን ባለሞያዎች አሰባስቦ የመጠቀም እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተገቢ ይኾናል።  ባለፈው ሳምንት በጤና ሚኒስትር መሥሪያ ቤት  ትብብር ጭምር የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሐፍ ተብሎ፣ በየዜና አውታሮቹ  የተለቀቀው፣ እስከ ሰኔ መጨረሻ  ከ28 እስከ 38 ሚሊዮን ሊደርስ የሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ በኮረና ቫይረስ ሊጠቃ ይችላል ብሎ ያስቀመጠው ዳታ ማንኛውም ሪፖርቱን ያነበበና ያዳመጠ ኢትዮጵያዊን የሚያስደነግጥ ነው። በተለይ የቁጥሩ ስሌት መሬት ላይ ካለው ነባራዊ የሀገር ውስጥም ኸኖ የዓለም ኹኔታ ጋር የማይጣጣም መስሎ ስለሚታይ ችላ ሊባል ይችላል፣ ነገር ግን  በቢል ጌትስ መሌንዳ BMGF  ፋውንዴሽንና ሚካኤል ብሉምበር  ጆንኾብኪን ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ  አማካኝነት ባለፈው ኦክቶበር 2019  ባልቲሞር ላይ ከተደረገው የ”2019 nCoV” ቫይረስ ሲሙሌሸን፣ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ፣  የዓለም ሕዝብ በቫይረሱ ተጠቅቶ እንደሚሞት ትንበያ ውጤት ጋር አንዲኹም፣  የለንደን ሮያል ኮሌጅ የኮቪድ 19 ሪስፖንስ ቲም በበኩሉ፣ ማርች 17, 2020 ፕሪዲክቲቭ ማቲማቲካል ሞዴልን ተጠቅሞ ባወጣው   ግምት መሠረት ግማሽ  ሚሊዮን እንግሊዛውያን፣ ሁለት ሚሊዮን  አሜሪካውውያን በቀጣዩ ወራት በበሽታው ተጠቅትው ይሞታሉ ከሚሉት ግምቶች ጋር መቀራረቡን ማስተዋል ግን ይቻላል። ይኽን ዘግናኝ ቁጥር  በኢትዮጵያ ላይ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተተንብዮ ስናነብ ቫይረሱን  ወደ አፍሪካ ሲያመጡት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን የመጨረስ አላማ ሊኖራቸው እንደሚችል ያስጠረጥራል።  ቢል ጌትስ  ፋውንዴሽን፣ አፍሪካ ላይ ትኩረቱን አድርጐ  የአፍሪካን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ እየሠራ ያለ መኾኑን ስናውቅ ደግሞ ስጋታችንን በጣም ከፍ ያደርገዋል። አስር ሚሊዮን የሚቆጠር የአፍሪካ ሕዝብ በቫርይረሱ  አፍሪካ ውስጥ ሊሞት እንደሚችልም ገና ከጅምሩ ነበር የገመተልን፣ እ.ኤ.አ 2009 ላይ ደግሞ  “የህጻናት ቫክሲኔሽን ላይ ጥሩ ከሰራን የአለምን ሕዝብ ቁጥር ከ10 እስከ 15 ፐርሰንት ልንቀንሰው እንችላለን/If we are doing a real good job vaccinating children, we can reduce the world population by 10% to 15%” (2009 TED talk)። ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ስፖንሰር መኾኑን እዚኽ ላይ ማስታወስ ይጠቅማል።

በአጠቃላይ ሲታይ፣ ኦዴፓ ኢህአዴግ መንግሥት፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ መንግሥታት እና ሕዝብ ማንነት የሚያንጸባርቁትን ሦስቱን  እሴቶች ያቀፈ የሚመስል፣ ነገር ግን በተቃራኒው እየሠራ ያለ ኾኖ እናገኘዋለን።  

እነዚኽ፣ ሦስት፣ 1966አብዮት‘  ወዲኽ የተፈራራቁ መንግሥታት፣ በአንድም ኾነ በሌላ መልኩ ሦስቱን ኢትዮጵያዊ ሕዝባዊ እሴቶችን  በአንድ ላይ፣ በአስተዳደራቸው ውስጥ ማስተናገድ ስለተሳናቸው፣ የሕዝብን ልብ ማሸነፍ አልቻሉም። በዚኽም ምክንያት፣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአንድ ልብ ከጐናቸው ለማሳለፍና ለሀገር  ኹለንተናዊ እድገት ሊውል የሚችልን ትልቅ አቅም ለመገንባትና ለመጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

 ኹሉን የሚያይ ኃያሉ እግዚአብሔር ሀገራችንን ከክፉ መዓት ይጠብቅልን!!!

አሜን! 

 

Filed in: Amharic