>

አርበኛ፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩ 11ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ!!! (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

አርበኛ፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩ 11ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ!!!

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመናገሻ አውራጃ፣ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘደንት፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት፣ በዳግማዊ ምኒልክ ሹመትም የመጀመሪያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ ታናሽ እህታቸው ደግሞ የውብዳር ገብሩ (እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ) ናቸው።
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት በቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህርት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም ድረስ ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱ ገብሩን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (የኋላው አፄ ኃ/ሥላሴ) ጋርም እንዳስተዋዋቋቸው ታሪካቸው ያስረዳል።
አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ በ1920 ዓ.ም ወደ ስዊዝ ሄዱ፡፡ እዚም ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በዚያም በዲፕሎማ ተመረቁ። ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በአዲስ አበባ በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ።
ፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ ሆለታ የጦር ት/ቤት ውስጥ ከሚገኙ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ወራሪውን ኃይል ለመፋለም ተነሱ። የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተምረው። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝቡን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት።
በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ድርጅት ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ አማክረው በተሰጣቸው አምስት መቶ ብር ድርጅቱን አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲሸነፍ በፋሺስት ጦር እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ ተወስደው የቁም እስረኛ ሆኑ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ ይፈለጉ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ።
ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብ ‹‹አዚናራ›› ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ለዘጠኝ ወራት ታሰሩ። ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥምና በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበልና መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ወይዘሮ ስንዱ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በሀገር ፍቅር ስሜት በመነሣሣት በርካታ ስሜት ቀስቃሽ ግጥሞችን ጽፈዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ትግል››፣ ‹‹ዓድዋ››፣ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹የታጋዮች ስሜት ከግራዚያኒ ንግግር በኋላ››፣ ‹‹ኮከብህ ያው’ና ያበራል ገና››፣ ‹‹የየካቲት ቀኞች››፣ ‹‹ከማይጨው መልስ››፣ ‹‹የኑሮ ስህተት››፣ ‹‹የልቤ መጽሐፍ››፣ ‹‹የታደለች ሕልም››፣ ‹‹ርዕስ የሌለው ትዳር››፣ እንዲሁም ‹‹ፊታውራሪ ረታ አዳሙ›› የሚሉት ሥራዎቻቸው የወይዘሮ ስንዱን የሀገር ፍቅር ስሜትና የሥነ ጽሑፍ ችሎታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል።
ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነውም አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና ‹‹የወንድ ዓለም›› በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ናቸው።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝደንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊና አስተዳዳሪ፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆንም አገልግለዋል። ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥተ ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
አርበኛ፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ የክብር ዶክተር ስንዱ ገብሩ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፎ ስርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic