>

እንኳን ለስዑር ቅዳሜ በሰላም አደረሳችሁ። (ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው)

እንኳን ለስዑር ቅዳሜ በሰላም አደረሳችሁ።

 

ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው

 

በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፦ቅዳሜና እሑድ ጾም ነው ተብሎ፥እንደ ሌሎቹ ዕለታት እስከ ተስዐት ወይም እስከ ሠርክ አይዋልም።በማለዳ ተቀድሶ እህል ውኃ ይቀመሳል።ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየ ሱስ ክርስቶስ፦ድኅነተ ዓለምን በመልዕልተ መስቀል ፈጽሞ ወደ መቃ ብር የወረደው፥ዓርብ በሠርክ ነው።ታድያ የጌታችን ወዳጆች፦እስከ እሑድ ድረስ(ትንሣኤው እስከሚገለጥ)እህል ውኃ አልቀመሱም ነበር። ዛሬም ጽናቱን የሰጣቸው ምእመናን እና ካህናት፦ሐሙስ በሠርክ እህል ውኃ የቀ መሱ፥እስከ እሑድ ንጋት ያከፍላሉ።የሚቀምሱት እሑድ ሌሊት ከቅዳሴ በኋላ ነው።በዚህም ምክንያት ተጹማ የማታውቅ ቅዳሜ ለጊ ዜው ሥርዓተ ጾም ተሽሮ፥በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ሥዑር (የተሻ ረች) ቅዳሜ ተብላለች።ዋናው ምሥጢር ግን፦ድኅነታችን በቀራንዮ መካን ዓርብ ስለተፈጸመልን፥ኃጢአት መሻሩን፥በደል መደምሰሱን ያመ ለክታል።

ቄጠማው ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ምሳሌነት አለው።በምድር ላይ የሰው ሰውነቱ ከፍቶ፥ኃጢአቱ በዝቶ፥፵ መዓልትና ፵ ሌሊት የጥ ፋት ውኃ በወረደ ጊዜ፦ኖኅ እግዚአብሔር አዝዞት፥ቅዱሳን መላእክት ተራድተውት በሠራው መርከብ እስከ ቤተሰቡ ድኗል።ይህች መርከብ ለወላዲተ አምላክ ለድንግል ማርያም እና በደሙ ለተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት።ምክንያቱም፦መርከቢቱ ሦስት ክፍል እንደነበ ራት እመቤታችንም፦፩ኛ፦ንጽሐ ሥጋን፤ ፪ኛ፦ንጽሐ ነፍስን፤ ፫ኛ፦ንጽሐ ልቡናን ይዛ ተገኝታለች።ቤተ ክርስቲያንም፦መቅደስ፥ቅድስት እና ቅኔ ማኅሌት አላት።አንድም፦ወጣንያን፥ማዕከላውያን እና ፍጹማን አሉባት። አንድም ሕፃናት፥ወራዙት እና አረጋውያን ይገለገሉባታል።አንድም፦ካህ ናት፥ወንዶች ምእመናን እና ሴቶች ምእመናን ፈጣሪያቸውን ደጅ ይጠኑ ባታል። ለኖኅ ቤተሰቦች መዳን መርከቢቱ ምክንያት እንደ ሆነች ሁሉ፦ እመቤታ ችንም ለአዳምና ለልጆቹ መዳን ምክንያት ሆናለች።በእርሷ በኵል (ከእ ርሷ የነሣውን ሥጋና ነፍስ ተዋህዶ ሰው በመሆን)ወደ ዓለም የመጣው ለዚህ ነው።ለድኅነታችን በመስቀል ላይ የቆረሰልንን ሥጋ፥ያፈሰሰልንን ደም እና አሳልፎ የሰጠልንን ነፍስ የነሣው ከእርሷ ነው።ይኸንን በተመ ለከተ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፦”ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መሣሪያ ሆና ተገኝታለችና፤”ይሏት ነበር።ቤተ ክርስቲያንም እንደ ኖኅ መርከብ የተጠለሉባትን ሁሉ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ ለድኅነተ ነፍስ ታበቃቸዋለች።
ኖኅ፦የጥፋት ውኃውን መድረቅ እንዲያረጋግጥ ቁራን ቢልከው፦ ለጊዜው የሚያርፍበት ቅርንጫፍ፥የሚበላውም ፍሬ በማግኘቱ በዚ ያው ቀልጦ ቀርቶአል።”ኢተመይጠ ቋዕ እስከ አመ ነትገ ማየ አይኅ፥ ቁራ የጥፋት ውኃ እስከሚደርቅ ድረስ አልተመለሰም፤”ይላል።ዘፍ፡፰፥ ፰።”ከዚያ በኋላ ተመልሷል፤”ማለት አይደለም፥ፍጻሜ(መጨረሻ)የሌ ለው እስከ በመሆኑ ጨርሶ አልተመለሰም ማለት ነው።ርግብን ቢልካት ግን፦በመጀመሪያ በምድር ላይ እግሮቿን የምታሳርፍበት ስፍራ በማ ጣቷ ወደ ኖኅ ተመልሳለች።ዳግመኛ ቢልካት፦ከዛፍ ቅርንጫፍ የወይራ ቅጠል፥ከምድር ደግሞ ቄጠማ ይዛ፦”ሐፀ ማየ አይኅ፥ነትገ ማየ ድም ሳሴ፤የጥፋት ውኃ ጎደለ፥የጥፋት ውኃ ደረቀ፤”እያለች ተመልሳለች። ኖኅም የውኃውን መጉደል በዚህ አውቆአል።

የኖኅን ፈቃድ ያልፈጸመ፥ወደ እርሱም ጨርሶ ያልተመለሰ ቁራ፦ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ላልፈጸመ፥ጨርሶም በንስሐ ለማይመለስ ለሰ ይጣን ምሳሌ ነው።ርግብ ግን፦”ማየ መርገም ጠፋ”እያለ በርግብ አም ሳል በዮርዳኖስ ለተገለጠ ለመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት።ማቴ፡፬፥፲፮።አን ድም፦”ሐፀ ማየ መርገም፤”ስትል ጌታን ፀንሳ ለተገኘች፥ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምም ምሳሌ ናት።ጠቢቡ ሰሎሞንም እግዚአ ብሔር ቢገልጥለት እመቤታችንን ርግብ ብሏታል።”ርግቤ መደምደሚ ያዬ አንዲት ናት፤(ወላዲተ አምላክ አንዲት እርሷ ብቻ ናትና የሚመስላት የለም)፤ለእናቷ (ለቅድስት ሐና) አንዲት ናት፥ለወለደቻትም የተመረጠች ናት።(ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተመረጠች ናት)።ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ንግሥታትና ቁባቶችም አመሰገኑአት፤(ሰማያውያን መላእ ክት ቅዱስ ገብርኤልን፥ምድራውያን ሰዎች ደግሞ፦መንፈስ ቅዱስ ያደ ረባትን ቅድስት ኤልሳቤጥን ተከትለው አደነቋት፥አመሰገኑአት)፤ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ፥(ቅዱሳን መላእክት በቤተ መቅደስ ኅብስት ሰማያዊ እና ጽዋዕ ሰማያዊ ይዘው በዝማሬ የጎበኟት፥የሰገዱ ላትም፤አንድም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፦ብሥራት ሰማያዊ ይዞ ሰላም ለኪ፥ተፈሥሒ ፍስሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ እያለ የጎበኛት፥የሰገዱላ ትም፤ቅዱሳን ሐዋርያት እና አርድዕት፥ካህናት እና ምእመናን፦በምስጋና የጎ በኟት፥የሰገዱላትም)፤እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠ ራች፥(መርገመ ሥጋ፥መርገመ ነፍስ ያላረፈባት፥ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የጠበቃት ንጽሕተ ንጹሐን)፤ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ(በመላእክትም በሰውም ዘንድ ግርማ ሞገስ ያላት) ማን ናት?”ይላል።መኃ፡፮፥፱-፲።

እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፦ሁለን ተናዋ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመሆኑ በዛሬዋ ዕለት (በስዑር ቅዳሜ) “ሐፀ ማየ ኃጢአት፥ነትገ ማየ ድምሳሴ፤በዕለተ ዓርብ በተፈጸመው በጌታችን ቤዛነት፦የአዳምን ልጆች በጠቅላላ አጥለቅልቆ የነበረ የኃጢአት ውኃ፥የጥፋት ውኃ ደረቀ፤(ኃጢአት ተሰረየ፥በደል ተደ መሰሰ)፤እያለች ርጥብ ቄጠማ ባርካ ለምእመናን ታድላለች።ምእመና ንም በደስታ ተቀብለው እንደ አክሊል፥እንደ ዘውድ ከራሳቸው ላይ ያደር ጉታል።የእግዚአብሔር ቸርነት፥የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥ አሜን።

Filed in: Amharic