>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4778

የእንኳን አደረሳችሁ የብፁዕነታቸው ሙሉ መልእክት

የእንኳን አደረሳችሁ የብፁዕነታቸው ሙሉ መልእክት

 
* ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ለመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ምእመናን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤን በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምእዳን!!!
 + ከጨለማ በኋላ ብርሃን፤
 ከመከራና ከሐዘን በኋላ ደስታ፤
 ከህመም በኋላ ፈውስ፤
 ከሞት በኋላ ሕይወት፤
 በጨለማ ውስጥ የብርሃን ተስፋ አለ.. 
***
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጌታችን እና የመድኃኒታቸን
የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የእምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
=====+++++=====++++++====
የብፁዕነታቸውን ሙሉ መልእክት እነሆ!
====+++===+++===+++===
የተከበራችሁ በሀገር ውስጥ እና በውጭው ዓለም የምትገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ 2012 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
“መኑ ይከሥታ ለነ ለዕብን እምኆኅተ መቃብር ማር 16፡3”
“ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጅ አፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል”(ማን ያነሳልናል) የክብር ባለቤት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ካደረ (ከቆየ) በኃላ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት በድንቅ ምሥጢር መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በሕቱም መቃብር ሞትን ድል አድርጎ የሰዎችን በደል ይቅር ብሎ የቤዛነት ዋጋ በሞቱ ከፍሎ በክብር ተነስቷል ሞቱን እና መቃብሩን ያዩ እነ መግደላዊት ማርያም በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቶ ሊቀቡ ገሰገሱ ነገር ግን ከመቃብሩ ላይ አይሁድ ያስቀመጡት ድንጋይ አስጨንቋቸው በፍርሐት እና ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል እያሉ ይጨነቁ ነበር፤ በእርግጥ ወቅቱ አስደንጋጭ ነበር አሉባልታ የበዛበት፣ የሐሰት ወሬዎች የሚናፈሱበት፣ እውነትን ከሐሰት መለየት ያልተቻለበት፣አዋቂዎች የሳቱበት፣እውነት የተቀበረበት፣ ጨለማ የበረታበት ዘመን ነው፤የክርስቶስ ትንሣኤ ተደብቆ እንዲቀርም ጥረቶች ተደርገዋል፤ይህም በወቅቱ ክርስቶስን ለሞት ያደረሱ አይሁድ ከቀብር ሥነ ሥርዓት በኃላ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሳ እንዳይሉ መቃብሩን በወታደሮች ለሦስት ቀን ያህል እንዲጠበቅ አድርገው ነበር፤B ወታደሮቹም ድንጋዩን በመቃብሩ ላይ አትመውት ነበር ድንጋዩም ከሰው አቅም በላይ የሆነ ግዙፍ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበር ይሁን እንጂ የክርስቶስ ሥልጣን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው እና ድንጋዩን አንከባሎ ከመቃብሩ በላይ ታየ ዓለም ከባዱን ነገር ታሸክማለች ክርስቶስ ደግሞ በሰዎች ላይ ያለውን መከራ ችግር፣ ሕመም፣ በሽታ አንከባሎ ይጥላል ስለሆነም እነ መግደላዊት ማርያም መዓዛ ያለውን ሽቶ ይዘው በሌሊት ሽፍታ እና ወንበዴውን በማለፍ ጨለማ ሳይበግራቸው በግርግር ውስጥ አልፈው ወደ ክርስቶስ መቃብር ወጥተዋል፤ ይሁን እንጂ እነሱ ባሰቡት ልክ ሳይሆን መልአኩ ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀምጦ ደረሱ፤ መቃብሩ ባዶ ሆኖ መነሳቱን አዩ፤ መልአኩም እንደተናገረ ተነሥቷል እና በዚህ የለም የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ አለ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራች ተናጋሪ እንዲሆኑ ታዘዙ ማቴ 28፡6 ስለሆነም ሞት ሆይ መዉጊያህ የታለ? ድል መንሳትህስ ወዴት አለ? የሚል የድል ዝማሬ ተዘመረ፡፡ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች የትንሣኤ በዓል በክርስቲያን ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው በዓል ነው፣ይሄውም የደስታ፣የድል፣የነጻነት እና የዕረፍት በዓል ሥለሆነ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የዘንድሮውን ትንሣኤ በዓልን ስናከብር ከመቼውም በተለየ መልኩ በችግር ውስጥ ሆነን ቢሆንም ክርስቲያን የማይሻገረው የመከራ ወንዝ የለም እና
ከሞት ወደ ሕይወት ባሸጋገረን በክርስቶስ ኃይል ታላቁን መከራ ማለፍ እንደምንችል በአጽንኦት እያሳሰብሁ በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ብሎም በሀገራችን የተከሰተውን የ ኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ እንደ ሰደድ እሳት  እየተጣደፈ የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ ያለበት ወቅት ቢሆንም፡-
 ከጨለማ በኋላ ብርሃን፤
 ከመከራና ከሐዘን በኋላ ደስታ፤
 ከህመም በኋላ ፈውስ፤
 ከሞት በኋላ ሕይወት፤
 በጨለማ ውስጥ የብርሃን ተስፋ አለ..
 ስለሆነም ሊነጋ ሲል ይጨልማል እና በድንግዝግዙ ጨለማ ውስጥ ብርሃንን ተስፋ ማድረግ መልካም ነውና ከትንሳኤው በኋላ መርገም ተወግዶ፣ በደል ተደምስሶ ፣ክስ ተሰርዞና የመከራው ድንጋይ ተነስቶ የክርስቶስን ትንሣኤ ማየት ችለናል፡፡
ስለሆነም የመጣብን ወረርሽኝ በሽታ ከባድ መስሎ ቢታየንም የማያልፍ መከራ የለምና ወረርሽኙ እንዲወገድልን ፈጣሪያችንን በጸሎት እየጠየቅን በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ፤ከመንግሥትና ከሃይማኖት አባቶች የሚተላለፈውን መመሪያ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ፤የተጎዱ ወገኖቻችንን በመርዳት፣ያለንን በማካፈል፣በመታዘዝ፣ ድሆችን በማሰብ እና በመርዳት የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላት እንዲሁም በመከባበር፣ በመደማመጥ፣ በመታዘዝ፣ በፍቅር ፣በአንድነትና በመደጋገፍ በዓሉን ልናሳልፈው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከል ሁሉም ሰው በጋራ በመረባረብ አካላዊ እርቀትን በመጠበቅ ፣ እጅን በመታጠብ፣ ከቤት ባለመውጣት እና ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ልንከላከለው ይገባል፡፡
በመጨረሻም የፍቅር ባለቤት የሰላም አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችን ቅድስት ኢትዮጵያን በቸርነቱ ይጠብቅልን ፤ በሽታውንም ከዓለማችን ያስወግድልን ፣የታመሙ ወገኖቻችንን ይፈውስልን፣ የሞቱ ወገኖቻችን ነፍሣቸውን በአጸደ ገነት ያሣርፍልን ፤ለሕዝባችንም ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ እንድነቱን ይስጥልን በዓሉን የሰላም የፍቅር የአንድነት የመተሳሰብ በዓል ያድርግልን፡፡
Filed in: Amharic