>

ንዜኑ ሞተከ ወትንሣኤከ (ሞትህን ትንሣኤህንም እናስተምራለን)  መምህር ጌቱ አያሌው

ንዜኑ ሞተከ ወትንሣኤከ

(ሞትህን ትንሣኤህንም እናስተምራለን)

 መምህር ጌቱ አያሌው
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 ቤተ ክርስቲያን የምሥጢር ግምጃ ቤት በመሆንዋ በውስጧ ያለው ሥርዓት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለም፡፡ ይህንንም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከወን በትሑት ሰብዕና፣ በፈሪሐ እግዚአብሔር ለሚቀርብ የሚሰጥ ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ ይህም ለዘላለም ጸንቶ የሚቆይ እንጂ ጊዜያዊ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በርዕሳችን ሞትህን ትንሣኤህንም እናስተምራለን በማለት የጀመርነው፡፡
.
ይህ አዋጅ የሚገኘው ዘወትር በምናመሰግንበት በሥርዓተ ቅዳሴ ሲሆን፤ ለእኛ ለምእመናን ሁሉ በአንድነት ሆነን “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ነአምን ዕርገተከ ወዳግመ ምጽአተከ (አቤቱ ሞትህን ቅድስት ትንሣኤህንም እናስተምራለን ዕርገትህን ዳግመኛም መምጣትህን እናምናለን” እንድንል በቅዱሳን አባቶቻችን የተቀመጠልን ምስክርነት ነው፡፡
.
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ መሞቱ፣ ለአፍታም ቢሆን በሕሊናችን ሊዘነጋ ስለማይገባ፣ ቅዱሳን አባቶቻችንን ሥጋ ወደሙን በምንቀበልበት በቅዳሴው ወቅት ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው፣ እንዲሁም ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽዓቱ፣ እየመሰከርን እንድናወድሰው ይህንን የምስጋና ሥርዓት አቆይተውልናል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋ ወደሙን በተቀበልን ቁጥር ልንናገርና፣ ልንመሰክረው እንደሚገባ ሲያዝዝ “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ” ብሎናል (1ኛ ቆሮ11፡26)፡፡
.
አበው ይህንን ውለታ በማስታወስ ከትንሣኤው በኋላ ባሉት በበዓለ ሃምሳ ቀናት፣ ሰላምታ ሲለዋወጡ ትንሣኤውን በሚያውጅና በሚመሰክር ቃላት መለዋወጥ እንዲገባ ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡
ይህንን የሰላምታ ቃል አስተውለን ብናየው፣ የአምላካችንን ውለታ፣ ድል አድራጊነቱን፣….ወዘተ ያስተውሰናል፡፡
.
 ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን (ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ) 
ይኸውም – የክርስቶስን ከሞት በድል አድራጊነት እንደተነሣ ማብሠር ሲሆን፣
 በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን (በታላቅ ኃይልና ሥልጣን)
– የአምላካችንን ታላቅ ሥልጣንና ኃይል እንድንመሰክር ያደርጋል፡፡
 ዐሠሮ ለሰይጣን (ሰይጣንን አሠረው)
ኃይለኛ የተባለው ሰይጣን በእርሱ ዘንድ የሚታሰር ደካማ መሆኑን ያሳውቃል
 አግኣዞ ለአዳም (አዳምን ነፃ አወጣው) –
ነፃ አውጪ ንጉሥ እንዳለንና ሲያስገነዝብ፤
 ሰላም – እምይእዜሰ (ከእንግዲሀ ሰላም ሆነ) – ከሞቱና ከትንሣኤው ጀምሮ ሰላም እንደሰጠን እንዲሁም
 ኮነ-ፍስሐ ወሰላም (ሰላምና ደስታ ሆነ) – ሰላምና መረጋጋት እንደተደረገልን የምናስተምርበት የሰላምታ ሥርዓት መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡
.
ይህንን ለማለት የምናፍር፣ ወይም የምንዘነጋ ከሆንን፤ ቅዱስ ጳውሎስ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” እንዳላቸው ተወቃሾች እንሆናለን (ገላ 3፡1)፡፡ ሞቱንና ትንሣኤውን የማንናገር ወይም የማናስተምር ከሆንን፣ እውነትም አዚም ተደርጎብናል ማለት ነው፡፡
.
አዚም የሰው ልጆችን እንዳያስተውሉ፣ እንዲፈዝዙ የሚያደርግ የተንኮል አሠራር ነው፡፡ ይህ አዚም አእምሮን በያዘ ጊዜ፤ የሚጠቅመንን የምስክርነት ቃል ከማስተዉም አልፎ፤ የክርስቶስን ሞትና መከራ፤ ትንሣኤና ዕርገት ከአእምሮአችን እንዳይቀመጥ ሥዕሉ እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡
የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ውለታ፣ እንዴት ሊዘነጋ ይችላል?፤ ስለሆነም ሞቱን በማሰብ ሐዘንተኞች፣ ትንሣኤውን በማሰብ ባለተስፋዎች መሆናችንን አውቀን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት፣ ከትንሣኤው እስከ በዓለ ሃምሣው ድረስ “ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን፤ በዐቢየ ኃይል ወሥልጣን” እያልን ስለ ድል አድራጊው ጌታ ልንመስከርና ልናስተምር ይገባናል፣ ይህን በእፍረትም ሆነ በመዘንጋት የማንመሰክር ከሆነ በአዚም እንደተያዝን እንወቅ፡፡
.
አዚም አእምሮን ስለሚይዝ አንደበትንም ለምስጋና እንዳይከፈት የማድረግ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ነአምን ዕርገተከ ወዳግመ ምጽአተከ (አቤቱ ሞትህን ቅድስት ትንሣኤህንም እናስተምራለን ዕርገትህን ዳግመኛም መምጣትህን እናምናለን)” ከምንልበት ቅዳሴ እንድንቀር፣ ጠላት ሰይጣን ባዘናጋን ጊዜ፣ አዚም እያደረገብን መሆኑን በማወቅ በፍጥነት ስመ እግዚአብሔር ጠርተን አማትበን፣ ተነሥተን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለምስጋና  ልንመጣ ይገባናል፡፡
.
በዘመናችን በአዚም የተጠቁ ብዙ ሰዎች፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ ምስክርነት ሳይሰጡ ይከርሙና፣ ጠላት ዲያብሎስ በሜዳ አግኝቶ ወደ ክህደት ሲወስዳቸው፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወንጌል አይሰበክባትም በማለት እንዲሳደቡ ያደርጋቸዋል፤ ጥንትም አዚሙ ስለ ክርስቶስ እንዳይናገሩ ስለያዛቸው በኋላ ሃይማኖታቸውን በካዱ ጊዜ በስሙ የመጣውን ሐሰተኛውን ክርስቶስን ማምለክ ሲጀምሩ (ማቴ 24፡5)፤ አሁን ገና ክርስቶስን አገኘሁ ክርስቶስ ተሰበከልኝ ማለት ይጀምራሉ፡፡
.
ይህ ደግሞ አስቀድሞ የተተነበየው ይፈጸም ዘንድ የመደንዘዛቸው ምልክት ነው፡፡ “መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው” ያለው ከዚህ የተነሣ ነው (1ኛ ጢሞ 4፡1-2)፡፡ እነዚህ ሃይማኖትን የሚክዱ ሰዎች ባደነዘዛቸው ዲያብሎስ ተምረው እንደሆነ ሲያመለክት “የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል”፡፡
ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ነአምን ዕርገተከ ወዳግመ ምጽአተከ” እያለች ስትመሰክር ኖሯለች፤ ትኖራለችም፡፡ አምላኳን መድኃኒቷን ኢየሱስ ክርስቶስን ያላሰበችበት ወቅት በፍጹም አልኖረም አይኖርምም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ” (2ኛ ጢሞ 2፡8) እንዳለው እርሱን በማሰብ ሥጋውን ደሙን በፈተተችበት ወቅትም ጭምር ክርስቶስን ታስበዋለች፡፡
.
ስለሆነም ምእመናን ጉባኤ በሚሰጥባቸው ቦታዎች ሁሉ በመገኘት ስለ ክርስቶስ አምላክነት፣ ስለ እኛ ብሎ መሞቱንና መነሣቱን ብንማር ለሐዋርያት እንዳስተማራቸው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር የሚኖረው ጌታ አሁንም ከእኛ ጋር ሆኖ ሰሚ ጆሮ፣ አስተዋይ አእምሮ ያድለናል፤ የምንድንበትንም መንገድ አሳይቶ መልካምን ነገር ሁሉ ይሰጠናል፡፡ እርሱ ለሐዋርያት “በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው” (ሉቃ 24፡45) እንዲል፣ ለእኛም ማስተዋሉን ጥበቡን ሰጥቶን ስለሞቱና ትንሣኤው እንድንመሰክርና እንድንጠቀም ያደርገናል፡፡
ስለ ሞቱ መናገር
.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብዛኛዎቹ ንዋየ ቅድሳት ስለ ክርስቶስ መከራ ሞት የሚሰብኩ ተደርገው በምሥጢር ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ከበሮ ከሩቅ ሲታይ ማንገቻው የክርስቶስን ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት የተገረፈበትን ጅራፍ፤ ጠፍሩም የግርፋቱን ሰንበርን የሚያስታውስ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከግራ ከቀኝ ያሉት ጠባብና ሰፊውን ክፍል መመታቱ፣ ዓለምን የሞላው አምላክ በሰው አካል ተወስኖ፣ ስለ እኛ ብሎ በጥፊ መመታቱን ያስታውሰናል፤ መቋሚያ መሸከማችን መስቀል ይዞ መውጣት መውረዱን ያዘክራል፡፡ ቤተ ክርስቲየን የሕንጻዋ ጉልላት ጎርበብ ተደርጎ መሠራቱ፣ ቀራንዮን ሲያመለክት፣ በመሐሉ መስቀል መተከሉ የተሰቀለውን ክርስቶስን፣ ጮክ ብለን መስበክ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ (ማር14፡43-48፣ ዮሐ 19፡1፣ 1ኛ ቆሮ 1፡23)፡፡
.
ሞቱን ስቅለቱን የምንናገረው፤ ጥቅሙ ለእርሱ ሳይሆን፤ የእርሱ ሞት ለእኛ ጥቅም የተደረገ መሆኑን ስለምናምን ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ይህንን ሲመሰክር “እነሆ የመዳኔን ምሥጢራዊ ተአምር ሊነጻጸር የሚችል አንዳችም ነገር የለም፡፡ ጥቂት የደመ መለኮት ጠብታዎች መላውን ዓለም ዳግመኛ በአዲስ ተፈጥሮ ፈጥረዋልና” በማለት ያደነቀው፡፡
.
ምንም በሔዋን ምክንያት ሞት ቢመጣብንም፣ በፈቃዱ ሞታችንን በሞቱ ሊሽር የመስቀልን ሞት ታገሶ ነጻአውጥቶናል፡፡ ለዚህም ነው አባታችን ቅዱስ ሄሬኔዎስ “ባለመታዘዝ የእንጨት ፍሬን በመብላት ምክንያት የመጣውን ሞት፣ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመታዘዝ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን አስወግዶ ሕይወትን ሰጠን” ያለው፡፡
ስለሆነም በቅዳሴ አባታችን ቄርሎስ በደረሰው ምስጋና “ለቤተ ክርስቲያን ስትል በአደባባይ በጥፊ የተመታህ አቤቱ ይህን ማድረግህ እርስዋን በከበረ ደምህ ትቀድሳት ዘንድ ነው፡፡ ለእርስዋ ሲል ታሥሮ መጎተት የቻለ የበደለውም በደል ሳይኖር፣ ርኩስ ምራቅን ሲተፋበት የታገሠ መድኃኔ ዓለም በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ”  ብሏል፡፡ በዚህም ውለታውን እናስታውሳለን፡፡
.
ሞት የማይገባው ሞቶአል፤ የሞተው ደግሞ ኃጢአታችንን በከበረ ደሙ ሊያነጻ እንደሆነ ቅዱስ ፖሊካርፐስ “ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአት ያልፈጸመ በአንደበቱም ሐሰት ያልተገኘበት በመስቀል ላይ መከራን በመቀበል ኃጢአታችንን ተሸከመ ነገር ግን እኛ በእርሱ እንኖር ዘንድ በመስቀል ላይ መከራን በመቀበል ኃጢአታችንን ተሸከመ” ብሏል፡፡
.
ክርስቶስ ሞተ ብለን ስናምን ትንሣኤውንም ጭምር በሚያውጅ ቃል “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ” እንላለን፡፡ እርሱን ሞት አላስቀረውምና፤ “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና” (ሮሜ 6፡9) በዚህም የክርስቶስን ትንሣኤ የምንመሰክረውም የእኛ ትንሣኤ በእርሱ ጅማሮ ስለተበሰረ ነው፡፡
ስለ ትንሣኤው መናገር
.
በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ወደ መቃብር የወረደው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መግነዝ ፍቱልኝ፤ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሕቱም መቃብር ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እንመሰክራለን፡፡ ይህ ስብከት በመላእክት “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም” ተብሎ ቅድሚያ የታወጀ ነው (ማቴ 28፡6)፡፡
.
ቀጥሎም ከእርሱ ጋር ከዋለበት ውለው ካደረበት የሚያድሩ ሐዋርያት መቃብሩን ሄደው አይተው፣ መነሣቱን አምነዋል፣ ምስክር ስለመሆናቸውም “ባደረገው  ነገር  ሁሉ  ምስክሮች  ነን፤  እርሱንም  በእንጨት  ላይ  ሰቅለው  ገደሉት  እርሱን  እግዚአብሔር  በሦስተኛው  ቀን  አስነሣው  ይገለጥም  ዘንድ  ሰጠው … በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን” ብለዋል (ሐዋ 10፡41)፡፡
ለዚህም ነው የዚህ የትንሣኤ ምስክር ለመሆን ተመርጦ ከነበሩት መካከል አንዱ ይሁዳ ሲጎድል በዕጣ ለምስክርነት ቅዱስ ማትያስ እንዲገባ የተደረገው፡፡ የዚህም መመረጥ ዋና ምክንያት “ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል” በሚለው መስፈርት መሆኑን ይነግረናል (ሐዋ 1፡21-22)፡፡ ከዚህ በኋላ ሐዋርያት የስብከታቸው ዋና ዓላማ “ንዜኑ ሞተከ…ወትንሣኤከ” በማለት እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን መጽሐፍ “ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው” በማለት ያረጋግጥልናል (ሐዋ 4፡33)፡፡
.
እኛም የሐዋርያት ተከታዮች፤ የጌታችን ሞትና ትንሣኤ የድኅነታችን ዓርማ በመሆኑ እርሱ ሞት ሳይገባው የአማልክት አምላከ፣ የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ ስለ እኛ ሞቶ እንደተነሣ አምነን ብንመሰክር ድኅነታችንን ከእኛ ጋር እንደሚዘልቅ ሐዋርያው ሲነግረን “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና” (ሮሜ 10፡9) ብሏል፡፡
የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጥቅም
.
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጥቅሙ ለሰው ልጆች ሁሉ ነው፡፡ እርሱ ስለወደደን ሞተለን “ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” (ሮሜ 5፡8) የእንጨት ፍሬ በመብላት የመጣውን ሞት ሊሽር እርሱ በእንጨት ተሰቀለልን፡፡ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን እርግማን በመሸከሙ ከኦሪት እርግማን ዋጅቶናል (ገላ 3፡13)፡፡ ይህ ፍቅር በልባችን ተቀርጾ ስንመሰክረው እንኖራለን “እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል” (1ኛ ዮሐ 3፡16)፡፡
.
በተመሳሳይም የእርሱ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ለእኛ መንገድ መጥረግ ነው፡፡ ሞት የመጣው ባጠፋነው ጥፋት ነው፡፡ በቀዳማዊው አዳም ሞት ብንሞትም በኋለኛው አዳም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ  ክርስቶስ በተጀመረው ትንሣኤ ደግሞ ሁላችንን በሚመጣበት ቀን እንነሣለንና ጥቅሙ ለእኛ እንደሆነ በማመን እንመሰክራለን፡፡ “እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው” (ቆላስ 1፡18) ከሞትና ከመቃብር እንደ እርሱ ላይሞት አስቀድሞ የተነሣ ማንም የለምና፤ የትንሣኤችን በኩር ሆኖልናል “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1ኛ ቆሮ 15፡20) እንዲል፡፡
.
ከእኛ የሚጠበቀው በእርሱ ሞት የዘላለም ሞት ጠፍቶአል፤ በትንሣኤው በሕይወት እንድንኖር ቃል ገብቶልናል ብሎ መመስከር ነው፡፡ ያለን ተስፋም እንዲህ ነው፡፡ “ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና” (1ኛ ተሰ 4፡14)፡፡
ባጠቃላይ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የምናውጅ ሁሉ አዲስ ተስፋ እንዳለን በማመን፣ በደስታ “ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን” ልንል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ በእምነት ሆነን የተጠመቅነው  በክብር ትንሣኤ እንድንነሣ ነው፡፡ “ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ይላል (ሮሜ 6፡4)፡፡
.
ስለሆነም ሁላችንም የክርስቶስን ትንሣኤ ስንመሰክር፣ የገባልን ተስፋ ስላለን ተዘጋጅተን መምጣቱን ልንጠባበቅ ይገባናል፡፡ ይህም ትንሣኤ ከኃጢአት እንቅልፍ በመንቃት ነው፡፡ “ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል” (ኤፌ 5፡14) በተጨማሪም “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” (ራእይ 20፡6) ያለው ንስሐን ነውና፤ ሁላችንም ንስሐ ገብተን ዕድላችንን ሳያመልጠን በመዳን ቀን ውስጥ በፍጥነት በመነሣት፤ ንዜኑ ሞተከ ወትንሣኤከ የሚለውን የክርስቶስን ሞቱንና ትንሣኤውን በመመስከር ለክብር ትንሣኤ እንድንዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡
.
የፊተኛውን ትንሣኤ የተባለውን ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን በመንግሥቱ እንድንኖር፣ የእርሱ ፈቃድ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ የመላእክት ተራዳኢነት ከሁላችንም ጋር ይሁን፡፡ አሜን!
.
ለሁላችንም ከበረከተ ትንሣኤው ይክፈለን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Filed in: Amharic