>
5:13 pm - Thursday April 20, 6654

ከቸነፈሩ የከፋ አገዛዝ! (ከይኄይስ እውነቱ)

ከቸነፈሩ የከፋ አገዛዝ!

 

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በልማዳዊ አነጋገር ‹የኢትዮጵያ መንግሥት› እየተባለ ሲነገር ይሰማል፡፡ እውነት መንግሥት አለን? ሕዝብ የፈቀደው፣ ሕዝብ የመረጠው፣ ሕዝብ በተሳተፈበትና ባጸደቀው ርእሰ ሕግጋት እና ቈጥሮ ሠፍሮ በሰጠው ሥልጣን ለሕግ የበላይነት የሚገዛ፣ ከሕግ በታች ሆኖ የሚተዳደርና የሚያስተዳድር፣ አደራውን ሲያጓድል የሚጠየቅ የሚነሳ፣ በማናቸውም ተግባሩ ዜጋውንና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብትን÷ ታሪክንና ባህልን በመዋቅርና በተቋማት÷ በዕውቀትና ጥበብ ላይ መሥርቶ መሠረቱ ሳይናጋ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻሻለ የሚሸጋገር ሥርዓት አለን? ይህንን ነው ከሞላ ጎደል መንግሥት የምለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት የለንም፡፡

አለመታደል ሆኖ እኛ ‹የታደልነው› በአገዛዞች ነው፡፡ ጭቆናን፣ ግፍን፣ በደልን፣ ዝርፊያና ቅሚያን፣ ባጠቃላይ ነውረኛነትን ገንዘብ ያደረጉና በዚሁ የደለቡ ጉልበተኞች ነው አናታችን ላይ የሚጨፍሩት፡፡ በምንዳቤ ወ ዐጸባ ‹ባለጸጎች› ያደረጉን፡፡ ሃይማኖተኛውን ሕዝብ በጉልበታቸው ምድራዊ ሲዖል የፈረዱበት፡፡ በመከራ ወቅት እንኳ ለሕዝብ ዕረፍት የማይሰጡ፡፡ አሁንም በምርጫ ሽፋን (በነፃነትና ዴሞክራሲ ስም እየማሉ) አገዛዝን ለማስቀጠል መጨረሻው የማይታይ ሰልፍ የያዙ አያሌ ናቸው፡፡ አንዳንዱ ሰልፈኛ በምኞት፣ አንዳንዱ በቅዠት፣ ጥቂቱ ጉልበት አበጅቼአለሁ ጊዜዬ አሁን ነው በሚል ተረኝነት፡፡ አይጣል እኮ ነው ወገኖቼ!?

እነዚህ ‹ሰዎች› ምን እያደረጉ ነው? ስለ አገዛዙ ነው የምናገረው፡፡ በጎንደር፣ በወለጋ፣ በከፋ (ሚዛን-ቴፒ)፣ በድሬደዋ፣ በአ.አ. ወዘተ. ሕዝቡን በዚህ መከራ ወቅት ለምን ተጨማሪ ፈተና ይሆኑበታል? እውነተኛ የፀጥታ ችግር ቢኖር እንኳ በየክፍላተ ሀገሩ የምንሰማው ሕዝብን የማመስ ተግባር ምን ይሉታል? መከራ ብቻውን አይመጣም ሠራዊቱን አግተልትሎ ነው እንደሚባለው ሰብሉ በአንበጣ ክፉኛ የተጎዳበትንና ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጠውን ሕዝብ አስበውታል? እውን ለሕዝብ ደኅንነት የሚጨነቅና ኃላፊነት የሚሰማው አገዛዝ ይህን ያደርጋል? ሕዝብ ሕግና ሥርዓት አስከብር ብሎ በሚጮኽበት ጊዜ አገዛዙ የት ነበር? በዚህ አስከፊ ወቅት እንኳን ጥቂት በጎነት ከብዙ ክፋት ጋር እየደባለቀ እንዴት ይታመን? ወገን! ቅጥ አምባሩ የጠፋው ነገር ነው እኮ የገጠመን፡፡

ሌላው ከዐረብ አገራት ጋር ያለን የውጭ ግንኙነት እንዴት ቢያዝ ነው ወገኖቻችንም ሆነ አገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ለወረርሽኙ በእጅጉ ሊያጋልጥ በሚችል ሁናቴ እየተላኩ ያሉት? በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ሽፋን በእምነት በተለይም በኢኦተቤክ ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት የሚመስል አዝማሚያም አላማረኝም፡፡ በባለሙያዎች የሚሰጠውን የምክር ጥንቃቄ እሺ አልን፡፡ ስንዝር ሲፈቀድ ክንድ የሚጠይቀው አገዛዝ ተልእኮው ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀዳሚ መደገፊያው እምነቱ እንጂ ከቸነፈር በከፋ ሁናቴ ፈተና ሆነውበት የቈዩ አገዛዞች አይደሉም፡፡

ቸነፈር (ወረርሽኝ) ይመጣል ይሄዳል፡፡ የመጣበትን/የታዘዘበትን ዓላማ ፈጽሞ እንደ እምነት ወይም የተፈጥሮ ዑደት ካለው ዑደቱን ጨርሶ፡፡ ወይም ፍቱን መድኃኒት ተገኝቶለት ሊያቆም ይችላል፡፡ 

ቸነፈር ዘር/ጐሣ/መንደር አይመርጥም፡፡ እንደ ጀዋር ባሉ ሽብርተኞች አይደናገጥም፡፡ የጀዋር ቄሮን ዓይነት ፈሪ መንጋ በማሠማራት አይገታም፡፡ ሰባበርነው በሚሉ መንደርተኞች አይሰበርም፡፡ እንደ ኦ ኤም ኤን ባሉ መርዘኛ ሚዲያዎችም አይሸበርም፡፡ እንደ ኦነግ ባሉ ፈሪና ጨካኝ ሽፍቶች አይፈታም፡፡ መከራን ሽፋን አድርጎ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፣ በጠላት ሳይሆን በሕዝብ ላይ ሠራዊት ከሚያሠማራና የነውረኛነት ጥግ ገንዘቡ በሆነ አገዛዝ ኃይልም አይንበረከክም፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ጠላት አድርጎ ለ27 ዓመታት የፈጠረው ምስቅልቅል ሳያንስ የትግራይን ሕዝብ መያዣ አድርጎ በዘረፈው ሀብትና የጦር መሣሪያ ተመክቶ ለዳግም ጥፋት እየተሰናዳ ያለውን ሥጋ የለበሰ የአጋንንት ስብስብ – ወያኔን – ከቁብ አይቈጥረውም፡፡ ከነዚህ ልቅ መረኖች በተቃራኒው ለጥብቅ ሥነ ሥርዓት ሊገዛ ይችላል፡፡ ወገን የምትሰማ ከሆነ ስማ!!! ንዝኅላልነትህን አቁመህ ሰብሰብ በል፡፡ እንኳን ለገዳይ ወረርሽኝ ለተራ ደዌ ታክመህ የምትድንበት አገር ውስጥ አይደለም ያለኽው:: 

የዘር ልክፍት ከያዘው አገዛዝ አንዳች ሳትጠብቅ እንደ ቤተ እምነትህ በእምነትህ ጽና! እስላምም ሆንህ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ነውና ራስህን በሥነሥርዓት ሸክፍ! አትዝረክረክ! አምላክህን በከንቱ አትገዳደር! ቸርነትና ምሕረቱን የምትሻ ከሆነ የራስህን ድርሻ ተወጣ፡፡ ከዚህም ጋር የማንንም አርቲ ቡርቲ ሳይሆን የሕክምና ባለሙያዎችን የጥንቃቄ ምክር አድምጠህ ከሥራ ላይ አውል፡፡ ይህን በማድረግህ ራስህንም ወገንህንም ትታደጋለህ፡፡

የቸነፈር ቅዝምዝሙን እንደ አሓያ ዛፍ ጎንበስ ብለህ አሳልፈው፡፡ ያኔ በአገዛዞች ፍርርቅ የተሽመደመደች አገርህን ቀና ሊያደርጋት የምታመልከው አምላክህ የታመነ ነው፡፡ በጎውን ቀን ለማየት ትናፍቃለህ? በብላሽ አይገኝም፡፡ ወገብህን ጠበቅ አድርገህ ከደዌያት ሁሉ በከፋ የጐሠኝነት ደዌ የተያዘውን ኢሕአዴግ የሚባል አገዛዝ እስከነ ፈጣሪው ወያኔ ከዚህች የተቀደሰች ምድር በ‹ሰላማዊ ጦርነት› ማስወገድ ከፊትህ የሚጠበቅህ ፈተና ነው፡፡ ቅድሚያ ግን ለቸነፈሩ፡፡ እንዳትሳሳት ኢሕአዴግ የተባለው ‹ቫይረስ› እንደ ሌላ ቸነፈር ከላይ የታዘዘ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ኢትዮጵያን ለማጥፋት በሕወሓት ቤተ ሙከራ የተሠራ ደዌ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ትግል አንድነትንና ኅብረትን ይጠይቃል፡፡ ዐባይ ሀገር ኢትዮጵያን ይዘህ ለምን በመንደር ትርመጠመጣለህ? መንደርተኞቹን እምቢ! በላቸው፡፡ መላው ምድር የእግዚአብሔር ነው፡፡ አንተ ጠፍጥፈህ የፈጠርካት/የሠራኻት ይመስል የገዛ ወገንህን አታሳድድ! አታፈናቅል! ለጐሠኞች አድረህ ወይም በከንቱ ተረታቸው ተታልለህ ወገንህን አትበድል! ከላይ ሆኖ የሚመለከት የዓለማት ፈጣሪ፣ የማይሾሙት የባህርይ ንጉሥ፣ ፍርድ አደላዳይ አምላክ መኖሩን አትዘንጋ፡፡ በገዛ ፈቃድህ ተጨማሪ መዓትና ቁጣን አትጥራ፡፡ ሥነፍጥረት ሁሉ ለሱ ይታዘዛል፡፡ የማያቱ፣ የነፋሳቱ፣ የእሳቱ መዛግብት በእጆቹ የተያዙ ናቸው፡፡ እነዚህን የምሕረትም ሆነ የመዓት ማድረግ ሥልጣን የባለቤቱ ቢሆንም የእኛ በጎነት ወይም ክፋት ውጤቶች እንደሆኑ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በወገንህ ላይ ግፍና ዓመፃ መሥራቱን ከቀጠልክበት፣ አትድረስብኝ ብለህ በወንድምህ ላይ አጥር ያጠርክበትን ምድር በርዕደ መሬት ከሥር መሠረቱ ይገለባብጠዋል፡፡ በመከራ መመከሩ እንደማያዋጣ ከዚህ ቸነፈር ተማር፡፡

እግዚአብሔር ላንተ፣ ላባቶችህ፣ ለቅም ቅም ቅም…አያቶችህ እንድትኖርባት በፈቀደልህ ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቀው ምድር አእላፋት ኢትዮጵያውያን አልፈዋል፡፡ አንተም ነገ ከነሱ ዘንድ ትከማቻለህ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነህ እንጂ እንደ አዲሱ መምዕላይ በዘር/በጐሣ ተቈጥረህ አይደለም፡፡ (ስንሞት ኢትዮጵያ ያለው ሰውዬ፣ ተረኛ ዘመዶቹ በአሰቃቂ ሁናቴ የገደሏቸውን 86 ዜጎች ነውር ለመሸፈን ጐሣ ሲቈጥር ኢትዮጵያውያን ታዝበናል)  በአንድ አፍ ሁለት ምላስ፡፡ እስከዛው አኗኗራችንን እናሳምረው፡፡ ኢትዮጵያን በነፃነት፣ በሰላም የምንዘዋወርባት፣ ለፍተን ጥረን የምንኖርባት አገር ካደረግን የምድሪቱ ፍሬ ለሁላችን ከበቂ በላይ ነው፡፡ 

በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ፡፡ 

አምባ መጠጊያችን መድኃኔ ዓለም ነውና ስለ ምርጦቹ ብሎ ትድግናው አይለየን፡፡ አሜን፡፡

Filed in: Amharic