>

የጅራፍ ንቅሳት....!!!! (በኤፍሬም ስዩም)

የጅራፍ ንቅሳት….!!!!

 

 

በኤፍሬም ስዩም
ከጀርባህ ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት
እኛን የመውደድህ የዘላለም ምትራት
የፋሬስ የሳዶቅ ያለማመን ደባ
የጲላጦስ ግርፊያ የሔሮድስ ካባ
ከፊትህ የወጣው የደም ጎርፍና እንባ
ላንተ ስቃይ ናቸው ለእኛ ግን ደስታ
መከራህ ነውና የመዳን አለኝታ።
ጅራፍና ቡጢ ምራቅና ሃሞት
ለዓይን ደስ የማይል የስቃይ ደም ግባት
 በደም የተረጩ ቅዱሳት አልባሳት
እኒህ ናቸው ውበት የጌታ ደም ግባት
የመዳን አለኝታ የዘላለም ምትራት።
ውዴን ያላያችሁ እኔ ልንገራችሁ!
ፍቅሩን ላሳያችሁ
ድምጹን ላሰማችሁ
ምራቅ ተቀብቷል
ቡጢ ተቀብሏል
ኃጥያት ተሸክሟል
በቁንዳላው መሃል የደም ጎርፍ ይፈሳል
የፍቅር ንጉስ ነው የእሾህ አክሊል ደፍቷል!
 ውዴን ያላያችሁ – እኔ ልንገራችሁ!
ፍቅሩን ላሳያችሁ
ድምጹን ላሰማችሁ
ዓይኑ ፍቅር ያለቅሳል
ጎኑ ደም ይረጫል
ጽህሙ ተነጭቷል
ልብሱ ሜዳ ወድቋል
በቃሉም ቅዱስ ነው ይቅርታን ይሰዋል
ከፍቅር ትከሻው ያለም ደዌን አዝሏል!
ውዴን ያላያችሁ – እኔ ልንገራችሁ!
ከጀርባው ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት
እኛን የመውደዱ የዘላለም ምትራት
ለርሱ ስቃይ ናቸው ለኛ ግን ደስታ
መከራው ነውና የመዳን አለኝታ
ይህ ሁሉ ቢሆንም
የሰው ልጆች ድፈረት ክብሩን አይቀንስም
 ስለሰው መድከሙ ሃይሉን አያወርድም
ስሙ እግዚአብሔር ነው
ስሙ ይቅርታ ነው
ስሙ መሃሪ ነው::
የፈረሱን ጉልበት ብቃቴ ነው የሚል
ብዛቱን ተማምኖ የሚታበይ ልኡል
በርሱ ስም ይወድቃል በስሙ ይጣላል::
ስሙ ሁሉን ቻይ ነው ሁሉንም አድራጊ
ታላቁን የሚጥል ለታናሽ ተዋጊ!
 
ውዴን ያላያችሁ – እኔ ልንገራችሁ!
ፍቅሩን ላሳያችሁ
ድምጹን ላሰማችሁ
ከጀርባው ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት
እኛን የመውደዱ የዘላለም ምትራት
ለርሱ ስቃይ ናቸው ለኛ ግን ደስታ
መከራው ነውና የመዳን አለኝታ
እናም ጌታችን ሆይ
ያመኑት ይጽናኑ፣ የወጉህም ይዩህ
በደም የተረጩ ልብሶችህን ለብሰህ
አሜን ጌታችን ሆይ
ናልን ተመልሰህ።
~~~እንኳን ለብርሃነ ስቅለቱ አደረሳችሁ
Filed in: Amharic