>
5:13 pm - Friday April 20, 5257

አበዳሪና ተበዳሪ ፤ ወጊና ተወጊ ፤ እኩል ጩኾ አያውቅም!! ! [ቅዱስ መሃሉ]

አበዳሪና ተበዳሪ ፤ ወጊና ተወጊ ፤ እኩል ጩኾ አያውቅም!! !

ቅዱስ መሃሉ
* አሜሪካ ባለፉት 24 ሰአታት ውስጥ 6037 የሚሆኑ ዜጎቿን በCovid19 ምክንያት በሞት አጥታለች። ጠቅላላው የሟቾች ቁጥር 33,405 የደረሰ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙት ዜጎቿ ደግሞ 653,397 ደርሷል ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን ድጋፍ በመከልከሉ በትዊተር ኢትዮጵያዊያን ፒቲሽን ሲቀባበሉ ተመለከትኩ። ፒቲሽኑ ትራምፕ ውሳኔውን እንዲቀለብስ ተጽእኖ ለመፍጠር ነው። ፒቲሽኑ አንደኛ የትራምፕን ባህሪ ሁለተኛ አሜሪካ ያለችበትን ሁኔታ ሶስተኛ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ በህግ ያለውን ስልጣን ካለመረዳት እና ካለማገናዘብ የሚደረግ ዘመቻ ነው። አሜሪካ በኢመረጀነሲ ስር ስትሆን ፕሬዝዳንቱ የሃገሪቱ ኮንግረስ እና የህግ መወሰኛ ምክርቤት(ሴኔት) ይሁንታ ሳያስፈልገው ማንኛውንም ውሳኔ ማሳለፍ ይችላል።
ቀደም ሲል የወጡ አንዳንድ ህጎችንም ሳይቀር ስራ ላይ እንዳይውሉ ለጊዜው ማገድ ይችላል። ፕሬዝዳንቱ ማድረግ የማይችለው ህገመንግስቱን መጣስ ብቻ ነው።ፕሬዝዳንቱ በውሳኔዎቹ የህገ መንግስት አንቀጽ ጥሶ ከተገኘ የሚያስቆሙት የፍርድ ቤት ዳኛዎች ብቻ ናቸው። ፕሬዝዳንቱ በፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ምንም ስልጣን የለውም።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ህገመንግስቱ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ዳኞቹ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማገድ ይችላሉ። ዳኞቹ ከማገዳቸው በፊት ወይም እስካላገዱ ድረስ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል። ማንኛውም ባለስልጣን በራሱ አስተያየት ወይም የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ የማያምንበት ከሆነ ስልጣኑን ይለቃል እንጅ ትእዛዝ ካልፈጸመ በህግ ይጠየቃል። ህገ መንግስት መጣሱን ለፕሬዝዳንቱ የሚነግሩት ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የፍርድ ቤት ዳኞች ብቻ ናቸው።
እርዳታ ድሮም ቢሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፖለቲካ ጅራፍ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የአሜሪካ እንጅ አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ጥገኛ አለመሆኗን ማስያ እና ማስተማሪያ ነው። ለሃገራትም ቢሆን እንዲሁ ነው።
አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅትWHO የከለከለችው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍም ጭምር ነው። አሜሪካ በክልከላዋ ከዘለቀች ብዙ የአሜሪካ አጋሮችም የሷን ፈለግ ይከተላሉ። ጃፓን የአሜሪካን ውሳኔ አድንቃለች። ነገ እሷም ድጎማዋን እንደማታቆም ማረጋገጫ የለም። ከአሜሪካ ቀጥሎ የዓለም ጤና ድርጅትን በሁለተኛ ደረጃ ብዙ ገንዘብ በመስጠት የምትረዳው እንግሊዝም የአሜሪካን ፈለግ ልትከተል ትችላለች። እንዲያውም ገንዘብ ከማገድ በተጨማሪ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፎርም የማያደርግ ከሆነ በሌላ ይተካ የሚሉ ድምጾች ከወደ እንግሊዝ እየተደመጡ ነው።
የፊፋ መሪዎችን የአሜሪካ ፌደራል ምርመራ ቢሮ(FBI) ከያሉበት ሆቴል እና ሃገራት እየለቀመ ለምርመራ ብሎ ሲወስድ ዓለም ተቃውሞ ነበር። ግን አላዳናቸውም። ከዚያም በኋላ ወደ ስልጣን አልተመለሱም። በፊፋ ላይ የሆነው በWHOም ላይ ሊሆን ይችላል። ላይሆንም ይችላል። ይህ የሚወሰነው አሜሪካ ጉዳዩን በምትገፋበት ርቀት ልክ እንጅ በእኛ ፒቲሽን እና የዓለም የተቃውሞ ድምጽ አይደለም። ሊግ ኦፍ ኔሽንን በዊድሮው ዊልሰን ሃሳብ ያቋቋመችው አሜሪካ ጊዜው ሲደርስ እና አስፈላጊነቱ ሲያበቃ ድጋፍ ነስታ በራሱ ጊዜ ትርጉም እንዲያጣ እና እንዲፈርስ ማድረጓም ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ይህ እጣ ይገጥመው አይገጥመው እንደሁ የምናየው ነገ እና ከነግ ወዲያ ነው። ዛሬ ላይ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር አይቻልም።
Filed in: Amharic