>

"አሜሪካ ባሳየችው መዘናጋት በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ እየተጎዳች ነው!" (አምባሳደር ፍጹም አረጋ)

“አሜሪካ ባሳየችው መዘናጋት በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ እየተጎዳች ነው!”

አምባሳደር ፍጹም አረጋ 
  አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ባሳየችው መዘናጋት እየደረሰባት ካለው ቀውስ በመማር ኢትዮጵያውያኑ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አምባሳደር ፍጹም አረጋ መከሩ፡፡
መጀመሪ ላይ ቫይረሱ ቻይና ላይ ብቻ ተወስኖ ይቀራል የሚለው አስተሳሰብ መዘናጋት ፈጥሯል ብለው እንደሚምኑ የተናገሩት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ አሁን ላይ ወረርሽኙ በመላው ዓለም መዳረሱን ተናግረዋል፡፡ አሜሪካም ባሳየችው ቸልተኝነት አሁን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንደደረሰችም ነው የተናገሩት፡፡
ቀጥሎ የታየው ውጤት በጣም አስጨናቂ እንደሆነ ያነሱት አምባሳደር ፍጹም ኢትዮጵያውን ከዚህ መማር እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ አሁን ባለው መረጃ በአሜሪካ 614 ሺህ 246 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፤ 26 ሺህ 64 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ 38 ሺህ 820 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡
ኢትዮጵያውኑ በጤና ባለሙዎች እየተሰጡ ያሉ ምክሮችን በመተግበር ራሳቸውንና ወገናቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁም አምባሳደሩ መክረዋል፡፡ ቸልተኝነት በአሜሪካ እና በሌሎችም ሀገራት ያደረሰውን አስከፊ እልቂት በማስታወስ ከሌሎች መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
አምባሳደር ፍጹም አረጋ በሰጡት ማብራሪያ ሐኪሞች ከወረርሽኑ ራሳቸውን የሚጠብቁባቸው እና ለሕሙማን የሚሆኑ የሕክምና ቁሳቁስ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ገቢ እየተሰባሰባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዓይነትም ከ160 በላይ እሽግ ካርቱን ቁሳቁስ ከዲያስፖራ አባላት በማግኘት ማስረከባቸውን ነው የገለጹት፡፡ አሁንም በዓይነትም ይሁን በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደር ፍጹም ሥራ በተቀዛቀዘበት በዚህ ወቅት ለሀገራቸው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ የዲያሰፖራ አባላትንም አመሥግነዋል፡፡
በዚህ ወቅት ወደ ሀገር ቤት ለመሄድ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ያሉ የዲያስፖራ አባላት እንዳሉ ጥቆማ እንደሚደርሳቸው በመግለጽም በዚህ ወቅት ለእረፍትም ይሁን ለሌላ ጉዳይ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ ሳይሆን በቤት ሆኖ ይህን ጊዜ ማሳለፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዘገባው የ አብመድ ነው
Filed in: Amharic