>

ኪራይና መስፍን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

ኪራይና መስፍን

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

 

 

ሰሞኑን ስሜን ከቤት ኪራይ ጋር አንሥተው ነበር፤ እርግጥ ቤት የለኝም፤ ነገር ግን አግዚአብሔር ይመስገን አልተጎዳሁም፤ ልጆች የሚባሉት አድገው ራሳቸውን ችለዋል፤ ብርግጥም ጡረታዬ በዛሬው ጊዜ አያኖርም፤ በዚህም በኩል እግዚአብሔር ይመስገንና ጥቂት ሰዎች ሥራቸው አድርገውት በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ይረዱኛል፤ የእነዚህ ሰዎች ውለታ በጣም ይከብደኛል፤ እግዚአብሔር ጤንነትና ዕድሜ፣ ሰላምና በረከቱን ይስጣቸው፤ የቤት ኪራዬንም ደርግ ምስጋና ይድረሰውና ጎምዶልኛል፤ ለሁላችንም ማለቴ ነው፤ እነዚህ አሥር የማይሞሉ ሰዎች ባይኖሩ ምን እንደሚደርስብኝና የት እንደምወድቅ አላውቅም፤ ስደትን ግን ጭራሽ አላስበውም! እኔን የሚያሳዝኑኝ ግን የኔን ዕድል ያላገኙ ስንትና ስንት ኢትዮጵያን ያገለገሉ ሰዎች በችግር ሲቆሉ ሳይ ነው፤ የምንችል ሰዎች በወር አንድ ብር ብናዋጣ ብዙ ሰዎችን መርዳት እንችል ነበር፡፡

በቤት ኪራይ በኩል ያለውን ሙስና ሲያስቡት ያንገሸግሻል! ቤታቸውን በብዙ መቶ ሺዎች ብር እያከራዩ በመንግሥት ዝቅተኛ ኪራይ የሚከፍሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ ሞልተዋል፤ አይከነክናቸውም፤ ስንቱ ዳያስፖራ በብዙ ሺህ ብር እያከራየ እዚያ ደግሞ እንደደሀ በምጽዋት ይኖራል፤ የባሰም አለ፤ ሌላ ቀርቶ የኢጣልያን ባንዳዎችም እንደምንረዳ አውቃለሁ፤ የቱ ባለሥልጣን ነው ይህንን የሙስና ምንጭ በሰይፍና በሕግ ሊያጠፋው የሚችል?

Filed in: Amharic