>

የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ 159ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ (አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ 159ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ

አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል

ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ – ‹‹ባይተዋሩ መስፍን››

 

 

የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ልጅ የሆነው ‹‹ባይተዋሩ መስፍን›› ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የተወለደው ከዛሬ 159 ዓመታት በፊት (ሚያዚያ 5 ቀን 1853 ዓ.ም) ነበር፡፡ 
የልዑል ዓለማየሁ እናት ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ) ደረስጌ ላይ ያሸነፏቸው የደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ልጅ የሆኑት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ናቸው፡፡
ሚያዚያ 5 ቀን 1853 ዓ.ም ልዑል ዓለማየሁ ደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ በተወለደ ጊዜ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ደስ ተሰኝተው ጠመንጃ አስተኩሰዋል፤ 500 እስረኞችን ፈትተዋል፡፡ ከልዑሉ ጋር ሲጫወቱ መዋል ያስደስታቸዋል፡፡ ተናደውና ተበሳጭተው በሚመለሱበት ጊዜ እንኳ ልዑል ዓለማየሁን ታቅፈው ሲስሙ ንዴታቸውና ብስጭታቸው ይጠፋላቸው ነበር ይባላል፡፡
ልዑል ዓለማየሁ በተወለደ ሰሞን ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ከመኳንንቶቻቸው ጋር ተሰብስባው ሳለ ‹‹ለመሆኑ በዓለም ላይ ደስ የሚል ጠረን ያለው ምንድን ነው?›› ብለው ጠየቁ፡፡ ሁሉም ሰዎች የሚያውቋቸውን ሽቶዎች፣ የዱር አበባዎች … እየዘረዘረ ተናገረ፡፡ መልሱ እንዳልተመለሰ ንጉሱ ተናገሩ፡፡ ‹‹አባ ታጠቅ፣ በቃ አንተው መልሱን ንገረን›› አሏቸው። እርሳቸውም፣ ‹‹በዓለም ላይ እጅግ ደስ የሚል ጠረን ያለው አራስ ልጅ ነው›› አሉ።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ኢትዮጵያና ለራሳቸውም ክብር ብለው ራሳቸውን መስዋዕት ሊያደርጉ በተዘጋጁ ጊዜ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተለምነው ነበር። በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎችም፣ ‹‹እባክዎ በሚወዱት በልዑል ዓለማየሁ ይሁንብዎ፤ በራስዎ ላይ አይጨክኑ!›› እያሉ ተማፀኗቸው። አይበገሬው ቴዎድሮስ ቆም ብለው ለአፍታ አሰቡ። ወዲያውም እንዲህ አሉ …‹‹ለዓለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገር የለም። ሲያድግ ግን አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በዓይኑ እንደዞረች ሞተ በሉት›› አሉ።
‹‹ዘመናዊ መሳሪያዎችን የሚሰሩ ባለሙያዎችን ላኩልኝ›› ብለው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተጣሉት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ አውሮፓውያን ተሰብስበው እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡ የእንግሊዝ መንግሥትም እስረኞቹን ለማስፈታት በጀኔራል ናፒየር የሚመራ ጦር አዘጋጅቶ ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ ቀድሞ ከጎናቸው የነበረው ሰው ሁሉ ሲከዳቸው ተስፋ የቆረጡት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስም በጠላት እጅ ከመማረክ ይልቅ ራሳቸውን ማጥፋት ምርጫቸው አደረጉ፡፡
የእንግሊዝ ወታደሮችም መቅደላን እንዳልነበር አደረጓት! ቅጥሯን አቃጠሉት፤ ንብረቶቿን ሙልጭ አድርገው ዘረፉ፡፡ መቅደላን በማጥፋትና በመዝረፍ ዘመቻ ወቅት ተደብቀው የነበሩት የዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ እና ልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ተገኙና ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ፡፡ እቴጌ ጥሩወርቅ በጉዞ ላይ ሳሉ መንገድ ላይ ታመው ከሃገራቸው ሳይወጡ አረፉና ተቀበሩ፡፡
አባቱንም እናቱንም ያጣው ባይተዋሩ ልዑል፣ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጦር ጋር ተጉዞ ከሞግዚቱ ሻለቃ ስፒዲ (‹‹ባሻ ፈለቀ››) ጋር ለንደን ደረሱ፡፡
ልዑል ዓለማየሁ ለንደን ከገባ በኋላ ሻለቃ ስፒዲ ንግሥት ቪክቶሪያ ወደነበሩበት ዊንድሶር ቤተ-መንግሥት ይዞት ሔዶ ንግሥት ቪክቶሪያም የስድስት ዓመቱን ልዑል ዕንዳዩት ወደውት እንደነበር በወቅቱ ባሰፈሩት ማስታወሻቸው ላይ ገልፀዋል፡፡
ከዚያ በኋላም፣ ሻለቃ ስፒዲ ስለልዑል ዓለማየሁ ሁኔታ በየጊዜው ለንግስቲቱ ሪፖርት ያቀርብ ነበር፡፡ ስፒዲ ወደ ሕንድ ሀገር በስራ ተቀይሮ ሲሔድ አብረው ሄዱ። በኋላም ልዑል ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ እንዲመለስ ተደረገና ብራይተን ወደሚገኘው የቻርልተን ኮሌጅ ተዘዋወረ። እዚያም ለአራት ዓመታት ቆየ፡፡
ፈረንሳይንና ሌሎች ሀገራትን ከጎበኘ በኋላ ግን መታመሙ ተሰማ። ‹‹ይሻለዋል›› ተብሎ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ሕመሙ እየጠናበት ሄዶ ኅዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ በ19 ዓመቱ፣ (በሳንባ በሽታ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
የመረጃው ምንጮች
፩. አጤ ቴዎድሮስ – ጳውሎስ ኞኞ
፪. ልዩ ልዩ ድረ-ገፆች
Filed in: Amharic