>

አንድ ነገር ሹክ ልበላችሁ!!! (ዶክተር ገበየሁ ተፈሪ)

አንድ ነገር ሹክ ልበላችሁ!!!

በዶክተር ገበየሁ ተፈሪ


* ሱቅና የተለያዩ ስቶር ባለቤቶች ኮሮናን ለመከላከል አስፈላጊ ምክር 

ከዚህ ቀደም በድረ ገፁም ሆነ በተለያዩ መገናኛዎች ሰለ ሳርስ ኮቪ ቫይረስ ቁጥር ሁለት (SARS-CoV-2) ፣ ወይም ሰለሚያስከትለው በሽታ ኮቪድ-19 (COVID-19 ኮሮና ቫይረስ ዲዚዝ በ2019)፣ አጠቃላይ ምክርና ትምህርት ለመሥጠት የሚቻለው ተደርጓል፡፡ ምክሩን ሰምተው በቂ ጥንቃቄ ያደረጉ ዜጎች እንዳሉም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ዋናው ነገር፣ በዚህ ጉዳይ ከሚገባው በላይ መሸበርና መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ መሸበር ወይም መጨነቅ የሚመጣው፣ አንደኛ፣ ሰለ ቫይረሱ በቂ ግንዛቤ ወይም ዕወቀት ሳይኖር ሲቀር፤ ሁለተኛ ደግሞ፤ ምን ማድረግ እችላለሁ ወይስ ምን እንናድርግ ለሚለው በቂ ዝግጅት ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡
ይህንን ሁሉ በማየትም፣ በዚህ ፓንደሚክ በኩል በተለያዩ ተቋማት የደረሰውን ወይም እየደረሰ ያለውን ችግር በመመልከት፣ ከአጠቃላይ ምክር ገባ በማለት ዘርዘር ያለና ጠለቅ ያለ ምክር መሥጠት የግድ ነው፡፡
በዚህ ቁጥር አንድ ምክር ርዕሱ በሌሎች የደረሰው እንዳይደርስ የሚል ነው፡፡
ይህ ምክር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የደረሰውን ችግር ከማየት የመነጨ መሆኑንም እንድትገነዘቡ ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ይህንን ፓንደሚክ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ አሳዛኝ የሆኑ የተለያዩ አመለካከትና ሀሳቦቸ ሲሠጡ ከርመዋል፡፡ ያም በሽታውን እንደሌለ ወይም አንደማይመጣ አድርጎ ከሚሠራጨው ሃሳብና ከመጠን በላይ ፍርሃትና ሽብር የሚያስከትሉ ዜናዎች መለቀቅን ጨምሮ ነው፡፡

አንድ ነገር ሹክ ልበላችሁ

በሽታን መከላከል በእንግሊዝኛ (Infection Control) የሚባል ራሱን የቻለ ከህክምናው ጋር በተጓዳኝ የሚተገበር፣ በሳይንስ የተመረኮዘ ሙያ ነው፡፡ ለአመታት፣ ለእያንዳንዱ ተላለፊ በሸታ ምን አይነት መከላከያ ዘዴ ነው መተላለፉን የሚያስጥለው ተብሎ፣ በተግባር ሲፈጸም የኖረ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት አስከፊ ሥርጭት አምብዛም አለመከሰቱ፣ ይህን በጀርባ የሚካሄድ ወሳኝ ሙያ ህዝቡ፣ ባለሥልጣናቱ ቀርቶ፣ መሰል ሌሎች የህክምና ባለሙያኞች በውል ሳያውቁት የከረመ ነገር ነው፡፡

እንድ ሌላ ነገር ልናገር፣ ሆስፓታል ገብተው ታክመው የወጡ ህሙማን፣ ለሌላ ጉዳይ ቢገቡም፣ ሆሰፒታሉ ውስጥ የሚዘዋወር ተላላፊ በሽታ በመኖሩ፣ በገቡበት ምክንያ ሳይሆን በተላላፊ በሽታ ምክንያት ታመው ህይወታቸው ማለፉ የአደባባይ ሚሥጥር ነው፡፡ ሌላው ቢቀር፣ የጤና ባለሙያተኞቹ፣ ከህሙማኑ በሚመጣው በሽታ እንዳይያዙ አስፈላጊ ምክርና፣ አንዳንዴም መደርግ የሚገባቸው የመከላከያ ተግባራት በግድ እንዲደረጉ ሰለሚደረግ፣ የሕክምና ባለሙያተኞች በበሽታ ሳይያዙ፣ ወደ የቤታቸውም ተሸክመው ሳይሄዱ መቆየት ቸለዋል፡፡ የሰነበቱትም ለዚህ ነው፡፡፡ ስንት ነብሰ ገዳይ ባክቴሪያና ቫይረስ ያለ ይመስላችኋል?

አሁን ኮቪድ-19 የሚባል ነገር ሲመጣ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰለሙያው አንዳችም ልምድ የሌላቸው ሰዎች እየወጡ ከመናገራቸው በተጨማሪ፣ ክፋት ያስከተለው ነገር ቢኖር፣ የቁሳቁስና የሰው ሀይል ዕጥረት በመከሰቱ፣ ለአመታት ስንገለገልባቸው የነበሩ የመከላከያ ዘዴዎች፣ ከደረጃ በታች በሆነ መንገድ እየተቀየሩ በመመሪያ መልክ ሲወጡ አስተውለን፣ ተንገሽግሸናል፡፡ የህክምና ባለሙያተኞችም፣ ለዚሁ አደጋ በሚጋለጡበት ደረጃ ሥራ እንዲሠሩ እየተደረገም ነው፡፡ ባለሙያተኞቹ፣ ሰው ለመርዳት ባላቸው፣ የውስጥ፣ ከልብ የመነጨ ሰብአዊነት ምክንየት፣ እያወቁ አደጋ ላይ የወደቁ ህይወታቸውም ያለፈ ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው፣ ቫይረሱንና በሸታውን እንደ አመጣጡ ከማየት ይልቅ፣ ለሚያሰከትለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር ቅድሚያ የተሠጠበት ነገር በገሀድ የታየ ነው፡፡

ምን ለማለት ነው፡፡ ሰለ ቫይረሱና ሰለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካለ፣ ሰለመከላከያና ስለሚደረገው ጥንቃቄ፣ ምክርና መመሪያ ከሚያወጡ ወገኖች ወይም አመራሮቸ ከሚሠጡት በላይ አስፈላጊውን መከላከል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ሰፊ መግቢያ ነው የሆነው ወደ ምክሩ እንሂድ

በሌላ የደረሰው እንዳይደርስ

በዚህ ግብግብ ለአደጋ በጣም ከተጋለጡ ወገኖች መሀል አንዱም በመሆኔ፣ ከአንድ ሁለት ወይም ሶሰት ጊዜ ሊደርስ ከሚችል ችግር በመትረፌ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ተመልከቱ፣ የህክምና ባለሙያተኛቸ (ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ረዳቶች፣ ሌሎችም በኤክስ ሬይ፣ በሌላም ተግባር ከበሸተኛ ጋር የሚሠሩ ባለሙያተኞች በሙሉ) የኮቪድ አደጋ የሚመጣባቸው ከተለያየ አቅጣጫ ነው፡፡

1ኛ. እንደማንም የህብተሰቡ አባል፣ ከቤት፣ ከዘመድ ከጓደኛ በኩል

2ኛ. በሥራ ምክንያት፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ወይም የሚጠረጠሩ ህሙማን

3ኛ. በቫይረሱ መያዛቸው ያልታወቀ፣ ጤናማ የሚመስሉ ግን ለሌላ ህክምና ርዳት ወደ ህክምና ተቋማት የሚዘልቁ ሰዎች

4ኛ. በጣም አሳሳቢ የሆነውው ደግሞ፣ የራሳቸው የሥራ ባልደረቦች፣ የስሜት ምልክት እያላቸው ግን ሳያገናዝቡ ወደ ሥራ የሚመጡ

5ኛ› የሥራ ባልደረቦች፣ ባቫይረሱ ተይዘው ግን ስሜት የሌለባቸው ወደ ሥራ የሚዘልቁ ናቸው፡፡

በቁጥር 4ና 5 ያሉት፣ አደጋውን የሚጨምሩት፣ እነሱ ይያዙ አይያዙ በቂ የቁጥጥር ዘዴ ባለመተግበሩና፣ የለባቸውም ተብሎ ስለሚታሰብም፣ ከውስጥ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ያለ መከላከያ ተቀላቅለው ስለሚሰሩ ነው፡፡ የማካፍላችሁ ነገር፣ የህክምና ባለሙያተኞች በቫይረሱ መያዛቸው፣ የተወሰኑትም ህይወታቸው ማለፉ፣ በሥራ ላይ ያሉትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ጭንቀት የፈጠራባቸው መሁኑን ነው፡፡

እዚህ ላይ ትንሽ ቆም እንበልና እናስብ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ወይም አደጋ ውነት በህክምና ሠራተኞች አካባቢ ብቻ የሚከሰት ነገር ነው ወይ?

አይደለም፡፡ ማንኛውም፣ ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት የሚሠጥ ድርጅት ወይም ተቋም ከዚህ ወገን በምንም መንገድ አይለይም፡፡ የመለየው ነገር ቢኖር፣ የታወቁ ታማሚዎች ጋር አለመጋለጥ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በጣም በፀና ከታመሙት ይበልጥ፣ በጣም ያልታመሙ፣ እንዲያውም የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፈ ሰዎች ናቸው ሥርጭቱን ያባባሱት፡

በዚህ ሁኔታ ባላቸው የሥራ ፀባይ ልክ እንደ ጤና ተቋሙ ሊጋለጡ የሚችሉ ወገኖች፣ ሰፊም ሆነ መጠነኛ ሱቆች፣ ወይም ሌላ አገልግሎት የሚሠጡ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ነው፣ ሱቆች ያላችሁ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ የንግድ ሥራ ያላችሁ ሰዎች በጥሞና ማንበብ የሚገባችሁ፡፡ እንደ ህክምና ባለሙያተኞቹ ሁሉ፣ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ፣ ለአግልግሎት የሚገባውን ደንበኛ ለይቶ ማወቅ አለመቻሉና፣ እንደ ህክምና ባለሙያተኞቹ በቫይረሱ ላላመያዝ ሙሉ ትጥቅ መልበስ አለመቻሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥል፡፡

ምክሩ በተራ ቁጥር የሚከተለው ነው፡፡

1ኛ. እንደ ማንኛውም የህብረተሰቡ አባል መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ማድረግ

2ኛ፡ በሥራ ቦታችሁ፣ ደንበኛው በቂ ርቀት አንዲኖረው (ስድስት ጫማ) አድርጎ መገበያየት፣ ይሉኝታ አይሠራም

3ኛ. ቢቻል፣ ወደ ሱቅ የሚገባው ደንበኛ፣ ሳልና ማስነጠስ ካለው፣ ማስክ ሊለበስ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡ ይህም ከውጭ በኩል በበቂ ማስታወቂያ በማሳየት ወደ ሱቅ ከመግባቱ በፊት፡፡ ችግሩ የማስክ ዕጥረት ነው፡፡ አሁን ግን፣ ይሀ አሠራር፣ በተለይ፣ ሁሉም ሰው ማስክ ማድረግ እንዳለበት ሰለተነገረ ችግር አይፈጥርም፡፡

4ኛ. ደንበኛው በእጆቹ ያመላለሳቸውን ዕቃዎች ደጋግሞ ከመንካት መቆጠብ፣ ከነኩም (ለሽያጭ ሲባል) በአልኮል መወልወል፡፡ ዋናው ግን፣ ሠራተኛው፣ እጁን ካልታጠበ ወይም በአልኮል ካልወለወለ በስተቀር፣ አፍንጫ፣ አፍና አይን እንዳይነካ ወይም እንዳትነካ ማድረግ

5ኛ. ዋናው ደጋግመን ማስታወስ የሚገባን ነገር፣ የዚህ ቫይረስ መተላለፊያ መንገድ፣ ዋነኛው በመተንፈሻ አካል የወጣው በአይን የማይታይ ቫይረሱን የተሸከመው ጠብታ፣ ወደ ሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ አይን ሲዘልቅ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ተገልጋዩ ደንበኛ ማስክ ካደረገ፣ ከፍተኛው አደጋ ቀነሰ ማለት ነው፡፡

ከላይ በህክምና ባለሙያተኞች ካስተዋላችሁ፣ አብዛኛው አደጋ የተከሰተው፣ ካልጠረጠሯቸው ከራሳቸው የሥራ ጓደኞች ነው፡፡ በተለይም በተመላላሽ ህክምና ከፍል ለሚሠሩ ባለሙያኞች በስፋት መጋለጥ የመጣው ከስራ ባልደረቦቻቸው ነው፡፡ የታመሙ አሉ፣ በብዛት ግን፣ መጋለጣቸው ሲታወቅ፣ ገለል ብለው እንዲሰነብቱ ስለሚደረግ፣ ለአስራ አራት ቀናት፣ የሠራተኛ ዕጥረት መፈጠሩም ሌላው ችግር ነው፡፡ የሥራ ጓደኞቻቸው ደግሞ፣ በቫይረሱ የተያዙት ከሥራ ቦታ ሳይሆነ፣ ከቤታቸው ወይም ከህብረተሰቡ መሆኑ ነው፡፡

ሰለዚህ፣ በሱቆችና በሌሎች ለደንበኞቸ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ከልምድ እንዳየነው፣ የበሸታ ስሜት ምልክት እየተሰማቸው፣ ነገር ግነ፣ ገቢውንና ሥራዬን አጣለሁ በሚል ፍራቻ ዝም ብለው ወደ ሥራ ቦታ የዘለቁ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባለሙያተኞች ማየት ችለናል፡፡

ስለዚህ በዚህ በኩል የሚጣውን አደጋ ለመቀነስ

1ኛ. ከቤትም ሆነ ከህብረተሰቡ ለቫይረሱ ተጋልጦ መጠነኛ ሰሜት ያለው ሰው፡፡ ከሥራ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ ወደ ሥራ አለመዝለቅ

2ኛ› ድንገት ከዘለቀም፣ የዚሀህ ሰው ቫይረስ ወደ ሌላ እንዳይሻገር በከፍተኛ ደረጃ ሊከልክል የሚችለው ማስክ ሰለሆነ፣ ወደ ሥራው ከመግባቱ በፊት ማስክ ማድረግ

3ኛ. ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች የበሽታ ስሜት ሳያሳዩ፣ ቫይረሱን ማስተላለፍ መቻላቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፣ ሁሉም ወደ ሥራ የሚመጣ ሰው ማስክ እንዲያደርግ ማድረግ

4ኛ. ማስኩ፣ ካለቆሸሸ በሰተቀር፣ ለረዥም ጊዜ መደረግ ይችላል፡፡ ሰለዚህ ማስኩ መውለቅ የሚገባው፣ ወይም ከሱቁ ወይም ከሥራ ቦታው ወጣ ተብሎ መሆን አለበት፡፡ ማስኩ በውጩ በኩል ሊጋለጥ ሰለሚችል (ለመጋለጡ ጥናት አለ) ማስኩን በየጊዜው መነካካት አያስፈልግም፡፡ ከነኩ ግን እጅን ለሀያ ሰክንድ በሳሙናና በውሀ መታጠብ፣ አለዚያም 60 ፐረስንት አልኮል ባለው እጅቻውን መወልወል ነው፡፡ ይህ አሰራር፣ ሁለተኛውን የመተላለፊያ መንገድ መቀነስ ይችላል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከአሰሪ ጀምሮ እስከ ሠራተኛ፣ ሙሉውን ገዜ ማስክ መልበስ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ደንበኛው፣ ማን እንደያዘው ማን እንዳልያዘው ስለማይታወቅም ነው፡፡ በዛው ልክም የሥራ ባለደረባም ቢሆን ማን እንዳለው ወይም እንደሌለው አይታወቅም፡፡

5ኛ. ሠራተኞች፣ ለእረፍት ሲወጡና ምግብም የሚበሉ ከሆነ ብቻቸውን እንዲቀመጡ ማድረግ፣ ከፊት ለፊት፣ ሌላ ባልደረባ አብሮ እንዳይቀመጥ ማድረግ፡፡ ምግብ ሲበሉ ማስክ ሰለሚያወልቁ፣ በሥራ ቦታው ውስጥ ለምግብ በቂ ቦታ ሰለማይኖር፣ መኪኖቻቸው ውስጥ ተመግበው ቢመለሱ፣ ለነሱም ሆነ ለሌላው ሠራተኛ ጥሩ ነው፡፡

6ኛ. በሥራ ቦታው እያሉ፣ በየትኛውም ቦታ ማስኩን ማውለቅ የለባቸውም፡፡ በተለይም መፀዳጃ ቤቶች ወይም ሌሎች ጠበብ ያሉ የሥራ  ክፍሎች፡፡ ለዚህም፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ እንደተቀመጠው፣ ከመተንፈሻ አካል በእንጥሻ የሚወጣው ቫይረስ፣ ጠበብ ባለ ወይም በተዘጋ ክፍል፣ ለሶስት ሰአታት በአየር ላይ ይቆያል፡፡ ሰለዚህ ተጠቃሚዎቸ፣ ከነሱ በፊት መፀዳጃ ቤቱን ማን እንደተጠቀመ ሰለማያውቁ፣ ማስካቸውን ሳያወልቁ መገልገል አለባቸው፡፡ እነሱም ድንገት ቢኖራቸው፣ ከማስነጠስና ክፍሉን በቫይረስ ከማጋለጥ ይቆጠባሉ ማለት ነው፡፡

7ኛ. ሥራቸውን ጨርሰው ሲወጡ፣ ማስኩ መውለቅ የሚገባው ከመሥሪያ ቦታው ወጣ ወይም ራቅ ብለው መሆን አለበት፡፡ በር አካባቢ ምን እንዳንዣበበ ማወቅም ሰለማይቻል ነወ፡፡ ነገር ግን ከቤት ውጭ ማስክ መልበሱም ሰለሚደገፍ፣ ማውለቁ ተገቢም አይደለም፡፡

8ኛ› ሲገቡም ሆነ፣ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት እጅ መታጠብ በዛው ልክም ሥራ ጨርሰው ሲወጡ እጅ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም፣ መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች፣ ወደ መኪናቸው ምንም ነገር ይዘው ላለማስገባት መጣር አለባቸው፡፡ መኪናቸውን በ70 ፐርስንት አልኮል መወልወል፡፡ በተለይም በእጅ አዘውትውረው የሚነኩ ነገሮችን ማለት ነው፡፡

9ኛ. ወጭ በዛ ካላላችሁ፣ የቀረው ነገር ልብስ ነው፡፡ በኛ ሙያ ልብሳችን በጣም ተጠንቀቀን ነው የምንይዘው፡፡ አብዛኛው የህክምና ባለሙያ የለበሰውን ለብሶ ወደ ቤት፣ ወደ ውስጥ አይገባም፡፡ የህክምና ባሙያኞች የሚለብሱትን አይታችኋል፡፡ ታዲያ፣ ያንን ልበሱ ሳይሆን፣ በሥራ በታ ብቻ የሚለበስ እንደ ካፖርት የመሰለ፣ ወይም ሀኪሞች የሚለብሱት አይነት ጋወን ማዘጋጅትና በሥራ ቦታው እሰካሉ ድረስ አሱን መልበስ፣ ከሥራ ሲወጡ ማውለቅ ይረዳል፡፡ ለአእምሮም እረፍት ነው፡፡ ነጭ የሀኪም ኮት እኮ ለመለያ ብቻ አይደለም የሚለበስው፡፡ መከለያም ነው፡፡

10ኛ› ይህ ሁሉ ሆኖ፣ ድንገት የተጋለጡ ከመሰለዎት፣ ራስዎን አዳምጡ፣ የበሸታ ስሜት ካለብዎት፣ ወደ ሥራ አይሂዱ፣ ርግጠኛ ነኝ፣ አሠሪዎ ያመሰግንዎታል፡፡ ከሄዱ ግን፣ ጓደኛም ይጋለጣል፡፡ ሱቅም ይዘጋና ሥራዎን መልሰው ያጣሉ ማለት ነው፡፡ ድንገት ከተገኘብዎት ደግሞ፣ ሥራ ጓዶችዎን ደውሎ መንገር ጥሩ ነው፡፡ መቼም እነሱ ተጋልጠው ቢሆን እንኳን፣ ወደሌላ የቤተሰብ አባል፣ በቫይረሱ ከተያዘ አደጋ ላይ ሊወድቅ ወደሚችል ሰው እንዳያዳሻግሩት ነው፡፡ በአሜሪካ ከሆነ፣ የምትኖሩበት ሰቴት፣ ይህንን ነገር አጣርቶ መጠየቁ አይቀርም፡፡ የመንግሥት ህግም ነው፡፡

Filed in: Amharic