>

73 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ በመንግስት ጥያቄ ወደ ሀገር እየገቡ ነው!!! (ነቢዩ ሲራክ)

73 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ በመንግስት ጥያቄ ወደ ሀገር እየገቡ ነው!!!

ነቢዩ ሲራክ
 ” የኢትዮጵያውያን መባረር ስጋት ላይ ጥሎናል ” 
የጤና ሚኒስትሯ ዶር ሊያ ታደሰ
ከእስር ቤት በምህረት ተለቀው ከሳውዲ የገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ70 ሽህ በላይ ነው ። ይህ ቁጥር እስከ ያዝነው ሳምንት የገቡትን ከ3,000 የሚደርሱ ዜጎች አይጨምርም
*  ክቡራንና ክቡራት እባካችሁ ተናባችሁ ስሩ እላለሁ  ! 
የጤና ሚኒስትሯ ዶር ሊያ ታደሰ ” ከዱባይና ከሳውዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን መባረር ስጋት ላይ ጥሎናል ። ” ብለዋል ። ዶር ሊያ ይህን ያሉት ትናንት ከወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ነው ። ሚኒስትሯ ” እየተባረሩ ” ስላሏቸው ዜጎች  የማውቀውን አይጠፋምና ጥቂት ማለት ፈለግኩ ።
ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት በሳውዲ ተመላሾች ዙሪያ ተደጋጋሚ መረጃ በየቀኑ አቅርቤያለሁ። የመረጃየ ቅበላዬ ዋና አላማ ዜጎችና መንግስት ያለውን እውነታ ተከትሎ ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማሳሰብ ነው። ግልጽ ለማድረግ ያህል ባሳለፍናቸው   ሁለት ሳምንታት የገቡት ከ2,000 በላይ እስከ 3,000 ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መሰረት አዲስ አበባ እንደገቡ እርግጠኝነት  የምናገረው በበቂ መረጃና ማስረጃ ነው።
ዘርዘር ያለ መረጃ ካስፈለገ ከእስር ቤት በምህረት ተለቀው ከሳውዲ የገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ70 ሽህ በላይ ነው ። ይህ ቁጥር እስከ ያዝነው ሳምንት የገቡትን ከ3,000 የሚደርሱ ዜጎች አይጨምርም። እውነተኛው መረጃ ይህ ሁኖ ሳለ አሁን ” ከሳውዲ እየገቡ ያሉት ዜጎች ተባረው የገቡ ናቸው”  የሚለው በሰሞነኛ ስራቸው የማደንቅ የማከብራቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዶር ሊያን መረጃ ከእውነት የራቀ ነው እላለሁ ።
ዶር ሊያ ተባረሩ የሚሏቸው ዜጎች በመንግስት ጥያቄ ከሳውዲ መንግስት እስር ቤት በምህረት ተለቀው የሚመጡ እንደሆነ አውቃለሁ። የሳውዲ አረቢያ መንግስት አዲስ ባወጣው ህግ ሳውዲ ውስጥ በህጋዊ ስራ ፈቃድ የሚኖሩት ዜጎች ወደ ሀገር የሚመለሱበት እድል ተመቻችቷል።
ዜጎች ከኩባንያዎቻቸው ጋር በሚደረግ ስምምነት ረዥም አስገዳጅ እረፍት ወስደው ከስድስት ወራት ላላነሰ ወደ ሀገር ይገባሉ። በቅርቡ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአዲስ ህግ ሲገቡ  እንደጠቆምኩት ተባረው ሳይሆን በአስገዳጅ እረፍት መሆኑን ደግሜ ላሳስብ እወዳለሁ።
ከቃለ ምልልሱ የተረዳሁት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶር ሊያና መ/ቤታቸው በተመላሽ ዜጎች ዙሪያ በቂ መረጃ የላቸውም ። በአንጻሩ ስለ ተመላሾች በቂ መረጃ ያለው መሆኑን የማውቀው የውጭ ጉዳይ የሚኒስትር ያለውን ተጨባጭ መረጃ  ለጤና ጥበቃ አላጋራም። ያና ይህ ሲደመር ሁለቱ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ተናበው አለመስራታቸውን ተረድቻለሁ።
ክቡራንና ክቡራት እባካችሁ ተናባችሁ ስሩ እያልኩ የጤና ጥበቃ ምኒስትሯን ቃለ ምልልስ ላስከትል! 
***
  – በ2 ሳምንት ውስጥ ከሳውዲ የተባረሩ ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገባሉ
– እስካሁን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግማሽ ያህሉ ከዱባይ የገቡ ናቸው
– ትናንት በኮሮና ቫይረስ 1 ተጨማሪ ሰው ሲሞት፤ ከፍተኛው በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል
***
ከዱባይና ከሳኡዲ አረቢያ፣ በርካታ ሺ ኢትዮጵያውያን ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ እየተባረሩ መሆናቸው፤ ከባድ ስጋት ላይ ጥሎናል ሲሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ከበደ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ከሳዑዲ በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ አገራቸው የሚገቡ ከ3 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ለበሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ናቸው ሲሉ  ሁኔታው ክፉኛ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል – ዶ/ር ሊያ፡፡ ያለ ምንም የጤና ምርመራ የሚመጡ መሆናቸው ደግሞ አደጋውን እንደሚያከብደው ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ  ተለይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ከሳውድ አረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱት ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት የጤና ምርመራ ሳያደርግላቸው የሚመለሱና የቆይታቸው ጊዜም ጥንቃቄ የተሞላበት ባለመሆኑ ትልቅ ስጋት ላይ ጥሎናል ብለዋል፡፡ እነዚህን ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለአስራ አራት ቀናት ለይቶ ማቆየት የሚቻልባቸውን ቦታዎች የማዘጋጀቱ ሥራ መጠናቀቁን የገለፁት ዶ/ር ሊያ፤ ተመላሽ ዜጎቹ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንድ ክፍል ለአንድ ሰው ብቻ እንዲሆን ለማድረግና የምግብ አቅርቦትና የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር፣ ከሰላምና ከሳይንስ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር እንደሚሰራም ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ትናንት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው 442 ሰዎች መካከል ዘጠኝ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ 3232 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን 65 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል የትላንቱን ጨምሮ በበሽታው ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ሁለት ጃፓናውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ አንድ ታማሚ በጽኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አራት ያህሉ ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸው ተገልጿል፡፡ በቫይረሱ መያዛቸው ከተገለፀው 65 ሰዎች መካከል 48 ያህሉ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ 27 የሚሆኑት ዱባይን አልፈው ወይም ከዱባይ ተነስተው የመጡ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ገቢ መንገደኞቹ ቆይታቸው በዱባይ የነበረ ይሁን ወይም በዱባይ አየር መንገድ ትራንዚት አድርገው የገቡ ይሁኑ ለጊዜው የተገለፀ ነገር ባይኖርም፤ በርካታ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የጉዞ ታሪክ ዱባይ ላይ ያተኮረ መሆኑ ግራ መጋባትን ፈጥሯል፡፡ በዚሁ መሰረትም በተለይ ከዱባይ የሚገቡ መንገደኞችን ለብቻ ለይቶ ለማቆየት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ስለመታሰቡ ለጤና ሚኒስትሯ ለዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥያቄ አቅርበን፤ የተለየ ማቆያ ለዱባይ ገቢ መንገደኞች ለማድረግ አለመታሰቡንና ቀደም ሲል በተዘጋጁት ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ገቢ መንገደኞችን የቅርብ ክትትል እንዲሁም አስተማማኝ ጥበቃና ምርመራ በማድረግ፣ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከሳውዲ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁትን ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ለመቀበል እየተደረገ ያለው ዝግጅት፣ ምናልባት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ዜጎች ቢኖሩ እርስ በርስም  ሆነ ከቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰቡ ጋር በመገናኘት የበሽታውን ስርጭት እንዳያስፋፋ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከሳውዲ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ3ሺ ሊበልጥ እንደሚችል ያመለከቱት የጤና ሚኒስትሯ፤ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ 200 ያህል እንዲገቡ በማድረግ በመጪዎቹ 2 ሳምንታት ውስጥ ተጠናቀው የሚገቡ ይሆናል ብለዋል፡፡
Filed in: Amharic