>

ቸነፈር ቸርቻሪው ? (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

ቸነፈር ቸርቻሪው ?

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጎበዝ ! ዜግነት ፣ ጥቁርነት … በሚሉ ግርድፍ ቃላቶች አንሸነጋገላ ! ካርል ቦንዝም ሆነ ካትሪን ሀምሊን ከጎንድርም ከጉደርም አይደሉም!!!

***
የውዝግቡ ሥረ-ምክንያት ዶ/ር ቴዎድሮስ ” በሽታውን በእንጭጩ እንዳይቀጭ ከቻይና ተመሳጥረው መረጃ አሳክረዋል ” ነው። በዚህም መቶ ሺዎች ተቀጥፈዋል፤ ለህመም ተዳርገዋል ፤ገና ይቀጥላልም ። የቫይረሱ ባህሪ አዲስነትና ተለዋዋጭነት እንደተጠበቀ ፤ ከሳምንታት በኋላ ፣ ዳይሪክተሩ አቃልለው በማቅረባቸው ጢምቢራ ለሚያዞር ወቀሳ አቀባብሏቸዋል።
የThe New York Time ጻሓፊ Denise Grady በ23/1/2020 ዓ.ም (እኤአ) ” Coronavirus is Spreading, but W.H.O Says it’s Not a Global Emergency ” በተሰኘ ርዕስ ባስነበበው ዘገባ፣ የW.H.O የቴክኒክ ኮሚቴ “ቫይረሱ ዐለም አቀፍ ወረርሽኝ ነው – አይደለም በሚል ለሁለት መከፈሉን አስታውሶ ፤ ዋና አለቃው “አይደለም ” የሚለውን ቡድን እንደመሩ ገልጿል ። ይህም ለእልቂቱ መባባስ ፣ በሳይንሳዊ ትንታኔ ተደግፎ የሰውየውን ኅጢአት አግዝፎታል ።
እናት ድርጅታቸው ወደ መቀሌ በማባረሩ ረገድ የተባበሩ የአሜሪካ ሴናተሮች ፣ የዶክተሩን ሥልጣን ሲነቀንቁ ፤ ጋዜጠኞች ደግሞ አሳ-ጎርጓሪ ሆነዋል ። ተዋቂዎቹ ሚዲያዎች ከኮሮና የማይተናነስ ‘ከቬሬጅ’ ሰጥተውት አብጠልጥለዋቸዋል ። የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት የፈፀሟቸው ጥፋቶች (በእርግጥ ‘ስህተት’ ለማለት ይቸግራል ) አደባባይ በማስጣት አዘናብለዋቸዋል ። Peter Hasson በ23/3/2020 “China Helped Put This Man In Charge Of the World Health Organization -Is It Paying Off ? ” በሚል ርዕስ “The National Interest ” ድኅረ-ገጽ ላይ ባቀረበው ዳሰሳ፣ ከቴዎድሮስ አዳህኖም በቀር አንድም የህክምና ዶክተር ያልሆነ ሰው በዐለም ጤና ድርጅት ዳይሪክተርነት ተሾሞ አለማወቁን ጠቅሶ ሲያበቃ ፦ ” የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስተር እያሉ ሦስት አይነት የኮሌራ ወረርሽኞችን በመደበቅ ይወነጀላሉ ፤ ” ሲል በእንዲህ አይነቱ ‘ሙያ’ የዳበረ የሥራ-ልምድ እንዳላቸው አስርግጧል ።
ቫይረሱ በቻይና ያደረሰውን የከፋ ጉዳት ለመሸሸግ ስሁት-ትርክት በማስተላለፍ ፣ ችግሩን ዐለም አቀፍ ማድረጋቸውን አግሎቶ ተችቷል ። ቻይና በሽታውን የተቀሰቀሰበትን ውሃን ግዛት እስከዘጋችበት ጊዜ ድረስ ፣ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወደ ተለያዩ አገራት መጓዛቸውንና ቫይረሱን ማሰራጨታቸውን የዘገበው ደግሞ ኒዮርክ ታይምስ ነው።
ለ”Fox News ” አስተያየታቸውን የሰጡት የራፖብሊካን አባልና ሴናተር Martha Mcsally “ዶ/ር ቴዎድሮስ ዐለምን አታልሏል ” ወርፈዋቸዋል ። ከተራራ -የገዘፉ ማስረጃዎች እየታዩ ቻይና በሚገባ እንደተቆጣጠረችው አስመስለው ማወደሳቸውንም በማስታወስ ኮንነዋል።
አንድ ጥናት ፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ ሦስት ሳምንት በፊት ይፋ ሆኖ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥ ኖሮ እስከ 95 በመቶ ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል የጠቆመው ላይ ፤ ቻይናውያን አክቲቪስቶች በውሃን ግዛት ኮሮና የፈጃቸው ሰዎች ቁጥር እነ ቴዎድሮስ እንደራገቡት 3300 ሳይሆን 42 ሺ ማለፉን መዘገባቸው ተደምሮ ሥርየት-የለሽ ጥፋተኛ አድርጓቸዋል ።
በእናቱ ስሙ ያልተጠቀሰ ቻይናዊ ሐኪም “kyo-do News ” ለተባለ የጃፓን ሚዲያ ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከቻይና መንግስት ጋር ያለው ቁርኝነት ሥር-ሰደድ እንጂ አዲስ አይደለም ማለቱ ፤ ለእኛም አዲስ ባይሆንም ጥቂት ነገሮችን ለመጨማመረ ወደ አገር ቤት እንመለስ ።
ምክንያቱም ፦ ሥልጣን የያዙ ተረኞች በሕዝባቸው ላይ የቱንም ያህል በደል ፈጽመው ፣ ጅምላ ጨፍጭፈው ፣ በገፍ መዝብረው ….ዐለም-አቀፍ መድረክ ‘በአንቀልባ ይቀበለናል ‘ በሚል እንዳይቀናጡ ቀይ መብራት ይሆናቸዋል።በርግጥም የዶክተሩ ኅፀፆች መዘርዘሩ ማን ያውቃል ? ነገ ደግሞ ‘ጌታቸው አሰፋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደህንነት አማካሪ ሆኖ ተሾመ ¡ ” ከሚል ዜና ሊታደግ ይችላል ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ፈተናውን ገና አላለፈም ። ነፃ ተቋማትን የማዋለዱ ስትራቴጄዎች ፣ ለትራጄድ ቀርቧል ። ምናልባት ከሽሽግር ይልቅ ፣ በሽግሽግ አሽተውን ሲያበቁ ፤ ( የሴጣን ጆሮ አይስማና ! ) ኖቤሉን ቀብድ አሲይዘው አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ለመተካት ቢንደረደሩስ ? ….ለእንዲህ አይነቱ ክብር የሚመጥን ሥራ ዛሬ እንጂ ፣ ነገ አለ-መሆኑን ለማስታወስ የቀደሞ ጤና ጥበቃ ‘ትሩፋቶች’ ን ፋይል ማገላበጡ ‘ የብዳ መድኃኒት ‘ ነው።
ተው ተው ! ከኢትዮጵያዊነት ጋርማ አታያይዘው !! እንዲያማ ቢሆን ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ በሥራ- አስፈፃሚነት የመሩት ኢሕአዴግ ለኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ከአዳኝ ስኳድ ይልቅ ፣ አገናኝ ሃውልት ባቆመ ነበር ። እንደ አበበ ቢቂላ በትጋትና ፍጋት የመጡ አታስመስለዋ ?!
በርግጥ የጭፍጨፋ ሚዛን በሰለባ እንጂ ፣ በተራፊ ሳፋ ሆኖ አያውቅም ። “ሊገሉኝ ነው ” ፣ ” በጥቁርነቴ ተሳለቁ ” ..ለቅሷቸውንም እንደማቅለያ ይዘን “እንለፋቸው ” ብንል ፤ “ለአራት ኪሎ መጥፎ ምልኪ ይሆናል ” አይነቱ ንቃቃት መሰንቀሩ አይቀሬ ነው ።
ወደ ጉዳይችን …..
የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የአመራር አባል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ፣የጤና ጥበቃ ሚንስተር ዶ/ር ከበደ ታደሰ ምክትል ተደርገው ረዘም ላለ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ፤ በ1997 ዓ.ም ግድም ዋናውን ጨብጠዋል ። በወቅቱ በጎንደር ጎጃም ብዙ ሺዎችን የቀጠፈውን የወባ ወረርሽኝ መደበቅ የሥራ ማሟሺያ ማድረጋቸውን አስታውሳለሁ ። ግንባር ቀደም የመድኃኒት አቅራቢነትም የኢፈርቱ አዲግራት መድኃኒት ፋብራካ የሆነበት አድሏዊነት እዚህ ሠፈረ የተበጀ ነው፤ (አስደንጋጩ ነገር የፋብሪካው ምርት አልተማረም በምትለው አርሶ አድር ጭምር ፣ ፈውስ-የለሽ እየተባለ መተቸቱ ነው ። ከሕንድ ርካሽ መድኃኒቶች እንዲገቡ በማመቻቸትም ገና ያልተጠኑ የጤና መቃወስ በብዙዎች ላይ እንዲከሰት መግፍኤ ይደረጋሉ ። የፓስተር ኢንስቲትዮት ዘመናዊ ላብራቶሪ ግንባታ ፕሮጀክትን በመሳብ ይኮነናሉ ።
ጠበቅ ያለው የፀረ-ኤድስ ዘመቻ በእሳቸው ዘመን በመደብዘዙ ፤ዛሬ እንደ አዲስ ማገርሸቱን ይዘህ የቪኦኤን ዘገባ ተከታተል ፤ 2011 ዓ.ም ነው (በእነሱ) “Africa AIDA Conference Opens in Ethiopia “ርዕስ -ሥር የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የመሩት “President’s Emergency Plan For AIDS Relief ‘PEPFAR’ ” ኢንሽቲቭ 1.6 ቢሊዮን (ሚሊዮን አይደለም)  ዶላር ፣ የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢሮ በድፍን ኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪን ፣ ቲቢና ማላሪያን እንዲከላከል መሰጠቱን ታገኛለ ። መቼም ‘ሳቢውን’ ከቃሙ በኋላ ዘመቻውን ማቋረጣው ከዘር ማጥፋት ባይመደብም ፣ አንዳች ጥርጣሬ አይጫርም አትለኝም ?! (ግዴለም ፣ በ140 ሆስፒታሎች እንዲከፋፈል እንደተሰጠ የሚያትተው የቪኦኤ ዘገባ ጠቅስህ ፣ ኦዲት እንዲደረግ ጠይቀ ፤ ያኔ ” ዘንዶው ካላውጣ ፣ ከምላሴ ፀጉር )
አልጨረስንም ፤
ግዘፍ-የሚነሳው የመድኃኒት አስመጪነት ቢዝነስ በአብዛኛው በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲያዝ ኔትወርኩን የዘረጋው ማን ነው ?! ወይስ እየደጋገመ የተመላለሰውን የኮሌራ ወረርሽኝ “አተት” በሚል የብዕር ስም ደብቆ ፣ የብዙሃኑን እልቂት ማንበር ለአቅመ-ወንጀል አልደረሰም ?! የዶክተሮች ፍልሰትም ጣራ የነካው በ” ሲብስቴ ነጋሢ ” ጊዜ አይደለም ፤ (በክልሎች እንጃ እንጂ ፣ በሸገር ያሰሩት አንድ ሆስፒታል ካለ ስለ-አቡነ አረጋይ አድራሻውን ስጡኝ ። )
እንደ ኢሕአዴግ የአመራር አባልነታቸው በውል ከሚጠየቁበት ወንጀሎች ደግሞ ጥቂቱን እንጥቀስ ፦ የ97ቱን ጨምሮ ከአራት ያለነሰ ምርጫ ማጭበርበር ፣ በአያሌ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም ፣ ዘር ተኮር ማፈናቀል ፣ በተለያዩ አካባቢ ዘግናኝ የዘር ማጥፋትና መሰል ጉዳዮች መድረሳቸው.. … ግድግዳው ላይ የተቸከቸኩ እውነታወች ናቸው ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስተር በነበሩበት ጊዜም የዲያስፖራ ተቃዋሚ አባላትን ከመሰለልና የኢትዮጵያን ኮሚኒቲ ከመከፋፍል በቀር የፈየዱት ካለ ወዲህ በል ? በየኢምባሲዎቹ አቶ ስዩም መስፍን በዘር-ያስተሳሰሩትን ኔትዎርክ አጠናክረው በማስቀጠል የሕውሓትን ” አቃፊነት “ማስረገጣቸውን በትምህርተ -ስላቅ እለፈው ። በአውስትራልያ የምትኖር አንዲት የ14 ዐመት ህፃንም በትምህርት ቤት ውድድር ሃያ ሚሊዮን ዶላር ማሸነፏንና በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ለማሰራት እንደምትፈልግ መቀለዷን አምነው በመቀበል በፕሮፓጋዳ ካጨሱን በኋላ ውሸት መሆኑ ሲጋለጥ ” ህፃናቶች የውሃ ናቸው…” በሚል ለማስተባበል መሞከራቸው ፤ ተስፋዬ ካሳ በየት ዞሮ መጣ ? ያሰኛል ። እንደው በአባ-ጃሌው ! በዚህ ዐውድ ህፃን ማን ነው ?!
ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደ አባዱላ ገመዳ ፣ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ…. ያልተወራረደ ዕዳ አለባቸው ። እንደ ዐባይ ፀሀዬ ፣ አዲሱ ለገሠ ፣ ሽፈራው ሹጉጤ እጃቸው ላይ ደም አለ ። ሆኖም ዐለም ቲያትር ናት እንዲሉ ፤ ከፍርግርጉ ሾልከው የWHO ዳይሪክተርነትን ጠቅልለዋል ። መቼም የታመሙ እናቶች በቃሬዛና በሰው ትከሻ ረዥም መንገድ ሲኳትኑ ከመዋል ያልታደገ ፣ የሕብረተሰብ ጤናን የመጠበቅ ሥራን አጓለማውታ ያደረገ ተቋም መሪን ፣ ” ስኬታማ ” ተብሎ እዚህ መድረሱ ትንግርት ነው ። የምርጫ ቅስቀሳው ከሎጂክ ፣ በሎጅስቲክ መሳለጡን አልዘነጋሁትም ፤ ( የካምቤኑ ዋና መሪ ፣ ከድሉ በኋላ ዋና አማካሪ ዶ/ር ሰናይት ፍስሃ በጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ተጽኗቸው ምንድን ነው ? ጥያቄ ነው ። የተሻረውን ዶ/ር አሚር አማንን “Su-san Thompson Buffect Foundation ” ሲያስቀጥሩ ፤ የተሾሙትን ዶ/ር ሊያ ገ/መድህንን ደግሞ ‘ ፕሮሞት ‘ አድርገዋል ። በሚካኤል ሥዑልኛ ተረዳው ። )
ጎበዝ ! ዜግነት ፣ ጥቁርነት … በሚሉ ግርድፍ ቃላቶች አንሸነጋገላ ! ካርል ቦንዝም ሆነ ካትሪን ሀምሊን ከጎንድርም ከጉደርም አይደሉም ።
Filed in: Amharic