>

“ግሪታዴ” ታሪኩ አበራ ማነው? (ክፍል ፬ ፣፭ ና ፮ ) [ዘመድኩን በቀለ]

 

ታሪኩ አበራ ማነው? [ዘመድኩን በቀለ (ክፍል 1,2,3)]

 

“ግሪታዴ” ታሪኩ አበራ ማነው?

 

ክፍል ፬ 

ዘመድኩን በቀለ

 

አዳሜና ሄዋኔ ሆይ የወሬ ጠኔው ሊደፋችሁ እንደደረሰ በውስጥ መስመር በምትልኩልኝ ውትወታ ተረድቻለሁ። ዕድሜ ለኮሮና መሄጃ አሳጥቶ ከቤትሽ ሰብስቦ አስቀምጦ የሌለ አንባቢ አደረጋችሁ አይደል? በፌስቡክ የዘመዴ ጦማር ሌማሊሞ ነው አያልቅም ዘንዶ የሆነ ጦማሩን አላነብም ይለኝ የነበረ ሁላ፣ ፎቶ አይቶ ኮመንት ይሰጥ የነበረው ሁላ ተመስገን ሁሉም አንባቢ ሆነ።

•••
የግርታዴን ታሪክ ዛሬ እንቋጫለን። የስንዱን ጉዳይ ፋይሉን ከመዝገብ ቤት አውጥተን በነገው ዕለት እናየዋለን። እኔ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሆኜ፣ እሷ ደግሞ ርትዕት ተዋሕዶ ሆና እንሟገታለን። ከዚያ እመቤታችን እንደለመደችው ስንዱ ጋር ሄዳ ስለ እኔ የምትላትን አብረን እንሰማለን። ቀልደኛ ። አሁን ወደ ግሪታዴ። ታሪክ እንሂድ።

• ከመታሰሬ በፊት ከሳምንታት በፊት

“ሃሎ ዘመዴ ነህ?” ይለኛል አንዱ በስልክ።

አዎ እለዋለሁ።

የት ነው ያለኸው? ይለኛል።

ምትኩ ስቱዲዮ እለዋለሁ።

አይ መልካም ቤትህ መስለኸኝ ነው ይለኛል።

አይደለሁም ማን ልበል ግን አንተን እልዋለሁ ደዋዬን።

አታውቀኝም። ፖሊስ ነኝ። በሥራዎችህም አድናቂህ ነኝ። ከግሪሳዎቹ ጋር የምታደርገውንም ጦርነት በመጽሔት እከታተላለሁ። ቤትህ እንዲበረበር ከፍርድቤት የትእዛዝ ወረቀት ወጥቷል። ጓደኞቼ ፖሊሶች ወደ ቤትህ እየመጡ ስለሆነ እንዳትደነግጥ ብዬ ነው ይለኛል።

እኔም “ሃይ ሃጃም ጣጣ የለውም ይሂዱዋ” አልኩት በሐረርኛ።

አይ አስቀድመህ የምትደብቀው፣ የምታሸሸው ነገር ካለ ልንገርህ ብዬ ነው ይለኛል። ቤትህን የሚመራቸውም ከመምህር ምህተአብ ጋር ያለ ልጅ ነው ይለኛል።

እዚህ ጋር ደነገጥኩ። የምህረተአብ ስምሲጠራ ደነገጥኩ። ምህረተአብ ወንድሜ ነው። ከመምህር ምህረተ አብ ጋር የማውቀው ቤቴን የሚያቅ ሰው ደግሞ ታናሽ ወንድሙ መምህር ኤርሚያስ ነው። መምህር አስቻለው ቤቴን አያውቀውም፣ ዶር ዘሪሁንም ቤቴን አያውቀውም። ቢያውቁትስ ከእነ በጋሻው ጋር ምን ያገናኛቸዋል? ዘሪሁን ተጣልቷቸዋል። ማነው መንገድ መሪው ባንዳ?

ስሙን አታውቀውም? አልኩት ፎሊስ ነፍሴን?

አላውቀውም ይለኛል። እኔም በኋላ አውቀው የለ ብዬ ከደወለልኝ ሰው ጋር ተሰነባብተን ስልኩን ዘግቼ ተለያየሁ።

•••
የስቱድዮ ሥራዬን ጨርሼ ማታ ከቤት ስመጣ ቤቱ ምስቅልቅሉ ወጥቶ እያስተካከሉት አገኘሁ። ምንድነው ነገሩ? ፖሊሶቹ ምንደነው የፈለጉት እንዴ አልኳቸው ቤተሰቦቼን።

ፖሊሶቹ እንኳን በጣም ጥሩዎች ናቸው። ያስቸገረው ቤቱን ለመጠቆም ከፖሊሶቹ ጋር አብሮ መጥቶ የነበረው መምህር ታሪኩ አበራ ነው። እሱ ነው ያንንም ፈትሹ፣ ያንንም ገለባብጡ እያለ የቀወጠው። ልጆቹም ህፃናቶቼ ማለት ነው ፖሊሶቹን አይተው ሲያለቅሱ ፖሊሶቹ ሲያረጋጉአቸው ታሪኩ ግን በጣም ነው ያዘንንበት አሉኝ ቤተሰቦቼ። የአርማጌዶን ሲዲን ነበር የፈለጉት። ሰጥተናቸዋል። እሱ ግን ይሄ ብቻ አይደለም ብሎ ፖሊሶቹን አዋከባቸው። መጨረሻ ላይ ከፈለክ ራስህ ፈትሽ ሁላ ብለውት ገለባበጠው። ፖሊሶቹ ራሱ ይፈሩታል። ከዚያ በኋላ ነው አንደኛው ፖሊስ የመጣው ይምጣ ብሎ ነው መሰለኝ ወንድሜ ይበቃል። የምንፈልገውን አግኝተናል። ከዚህ በላይ የሰው መብት አንጋፋም ብሎ ይዞት የወጣው። ታሪኩ አበራ ግን ምንነካው? አሉኝ። እኔም ያልጠበቅኩት ስለሆነ አይዟችሁ ብዬ ዝም አልኩ። አቦይ ስብሐትን ይዞ ድሮስ ሊፈራ ነበር እንዴ አልኩኝ በሆዴ። ወያኔን ከኋላ አስከትሎ ሊፈራ ነበር? የሚገርመው ታሪኩ እንግሊዝ ሄዶ ግንቦት 7ቶችን አጃጅሎ፣ ኢሳቶችን አጃጅሎ ነው ወረቀት ያስገኙለት። ዳያስፖራ ላሜቦራ አይደል? ወያኔን እየተቃወሙ ወያኔን ይቀልባሉ። ዥሎች። የመጨረሻ ረኸጥ እኮ ነው አንዳንዱ ዲያስጶራ። ክፍል 5 ላይ እመለስበታለሁ።

•••
ከዚያ በፊት ደግሞ የሂነ ቀን ስልኬ ላይ ይደወላል። ሃሎ ማነህ አንተ ዘመድኩን ነህ? ፍጹም የስልክ ሥርዓት የሌለው ሰው ድምጽ ነው ደዋዩ። ድብን ባለ የጎዣም አማርኛ ቅላጼ ነው የሚያወራኝ።

አዎ ነኝ ማን ልበል አልኩት?

አባ ማርቆስ ነኝ። ነገ ጠዋት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና መምሪያ በአስቸኳይ እንድትመጣ። እንጠብቅሃለን። ረባሽ። ብሎ መልሴን ሳይጠብቅ ስልኩን ጆሮዬ ላይ ይጠረቅመዋል። ማነው አባ ማርቆስ? ለምን ፈለገኝ? ከምር አባማርቆስ የሚባል የማውቀው የደብረ ሊባኖሱን ዘማሪ መክብብ ኋላ አባ ማርቆስ የተባለውን ነው። ይሄን ስም ሰምቼው አላውቅም። እናም ምን ይመጣል እሄዳለሁ ብዬ ወሰንኩ። ከዚያ በፊት አንድ ሰው ጋር ደወልኩና እንዲህ ያለ ሰው ጠርቶኛል ስለው። እ ጳጳሱ ናቸው ይለኛል። የመምሪያው ኃላፊ ናቸው ይለኛል። በተሃድሶዎቹ ጉዳይ ሊያናግሩህ ነውም ይለኛል። ተቆጡኝ እኮ ስለው። አዎ ከነበጋሻው ጋር ነው የሚሠሩት ይለኛል። ነው እንዴ አልኩና ትጥቄን አበጃጅቼ ተዘጋጅቼ በማግስቱ ሄድኩኝ። [ ጳጳሱን ከሆነማ አውቄዋለሁ። ብዙ መረጃ አለኝ። ደግነቱ እዚያው ከእነ በጋሻው ጋር ውለው የሚያድሩ የመረጃ ሰዎች ነበሩኝ። እያንዷንዷን ሂደት እከታተል ነበር። እንዲያውም አንድቀን የማኅበረ ማርያሙ የፊደል ሬስቶራንት ባለቤት አቶ ኤፍሬም ሲወበራብኝ ጊዜ ሰንዱቁን ከፍቼ ፋይሉን ፖሊስ ጣቢያ መጥቶ እንዲወስድ ነው ያደረግኩት። አመዱ ቡን ነበር ያለው። መንፈስ ነበር የሆንኩበት። እኔ ዘመዴ እኮ አስማት የሆንኩ ልጅ ነኝ አርፈህ ተቀመጥ ብዬ አራዳ ፎሊስ ጣቢያ አቅርቤ ሰነዱን በሙሉ ኮፒ አድርጌ አስቀርቼ ነው የሰጠሁት። ( ከፈለጋችሁ ፊደል ሬስቶራንት ሄዳችሁ ጠይቁት። ፊደል ሬስቶራንት ማለት በገዳም ስም በተሰበሰበ ገንዘብ የተሠራ የደም ሀብት ነው ]

•••
እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲገጥመኝ አንድ ልማድ አለኝ። ቀጠሮዬ ከአዲስ ሰው ጋር የሚያገናኘኝ ከሆነ አቋሜን እቀይራላሁ። የማናግረው ሰው ባለሥልጣን ከሆነ በተለይ ፀጉሬ ላይ ዱቄትም ቢሆን በተን በተን አድርጌ ባለኝ ፎሮፎር ላይ ሌላ ፎሮፎራም ጨምሬ ፊቴንም ነጭ የአሸቦ ዕቃ አስመስልና በቅጥነቴ ላይ ሸምበቆ በሚያክለው ጡንቺት ላይ ቲሸርት አድርጌ የማሽላ እርሻ ውስጥ የቆመ ቢል ቢል የሚል የግሪሳ ማባረሪያ አሻንጉሊት በመምሰል፣ የተቀደደ ሱሪ፣ የቆሸሸ ነጠላ ጫማ በመልበስ መከሰት እወዳለሁ። የሚያገኘኝ ሰው መጀመሪያ አፉን በደንብ እንዲከፍትብኝ ስፈልግ እንደዚያ ነው የማደርገው። ብዙ ሰው የሚሸወደው የሰውነት አቋሜንና አለባበሴን አይቶ ነው። እናም ይሄ ደግሞ የብዙ ሰው ችግር ነው። ፍርድ የሚሰጠው አቋም አይቶ ነው።

•••
በማግስቱ ኮንትራት ታክሲዬን ይዤ ቤተ ክህነት ሄድኩኝ። የጥበቃ ኃላፊው ነፍሳቸውን ይማርና አቶ ብርሃኔ ይባላሉ በጣም ነበር የሚወዱኝ። ጥበቃዎቹ ታክሲዋ መግባት አትችልም ወደዚያ አቁማት ይሉኛል። እሺ ብዬ አቁሜ ተፈትሼ ልገባ ስል ኃላፊው ያዩኝና ውይ ዘመዴ አንተው ነህ እንዴ ይሉኛል አዎን ስላቸው በል ታክሲዋም ትግባ ብለው ያስገቡኛል። ሰውነቴንም አይተው ምነው ምንገጠመህ ይሉኛል የሥራ መደራረብ የሚል ምክንያት ሰጥቼ ወደ ተጠራሁበት ቢሮ አቀናሁ።

•••
ከተባለው ቢሮ ስደርስ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የያኔው አባ ኃይለማርያምና መጋቤ ምስጢር ወልደሩፋኤል ፈታሂ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጋር አብረው ጠበቁኝ። አባ ኃይለማርያም እጅግ አክባሪ ወዳጄ ነበሩና ወልደሩፋኤልም እንዲሁ ሞቅ ያለ የአክብሮት ሰላምታ ሰጥተውኝ ተቀመጥኩ። አባ ኃይለማርያም በዚያ መልኩ አይተውኝ ስለማያውቁ ደንግጠዋል። ምነው ዘመዴ? ይሉኛል። ጥያቄአቸው ስለገባኝ በኋላ አጫውቶታለሁ ብዬ ወደተጠራሁበት ጉዳይ ገባን። አባ ኃይለማርያም ዘመድኩን የምባለው እኔ መሆኔን ለሊቀጳጳሱ ይነግሯቸውና ውይይቱ እንዲጀመር መንገድ ይከፍታሉ። እስከዚያች ሰዓት ድረስ ከቁብ ያልቆጠሩኝ ሊቀጳጳስ አባ ማርቆስ ሁሉን ነገር ጣጥለው ከላይ እስከታች ጎበኙኝ። የሆነ ቦርኮ መስዬም ታየኋቸው። ከዚያማ ምኑ ይጠየቃል አበዱብኝ። ወረዱቡኝ። አበሻቀጡኝ። አንተነህ እንዴ ሃገር የምታምሰው? ምንአግብቶህ ነው አንተ እነበጋሻውን የምትናገረው? እኮ መንቆርጦህ። አወረዱብኝ። ከፊታቸው ጭብጥብጥ ብዬ ሲያዩኝ ጊዜ ወረዱብኝ። እኔ ዝም፣ ጭጭ።

•••
አባ ኃይለማርያም ኧረ አባታችን ልጁ እንኳ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ነው። የሁላችንም ወዳጅ ነው። ብለው ሊያቀዘቅዟቸው ቢሞክሩም ኧረ ንሺ እቴ እሳቸው ባሰባቸው። አባው ከመስመር የወጣ ስድብ መሳደብ ሲጀምሩ ወልደሩፋኤል ቆጣ ብለው። አይ አባታችን እኔ መናገር አልፈልግም ነበር ነገር ግን ይሄ ልጅ እውነት አለው። እኛ ያልሠራነውን ሥራ የሠራ ልጅ ነው። እናም ብናዳምጠው መልካም ነው ብሎ ቆጣ ብሎ ይናገራቸዋል። የእሳቸውን ምላሽ እየጠበቅን የቢሮው በር ይንኳኳል። አንድ የምንጣፍ ማጽጃ ማሽን የያዘ ወጣት ይገባና ያስረክባቸዋል።

•••
ወጣቱ ተልኮ የመጣው ከፊደል ሬስቶራንት ባለቤት ከማኅበረ ማርያሙ ሊቀመንበር ከአዝማሪ ፕሮሞተሩ ከአቶ ኤፍሬም ዘንድ መሆኑን ሁላችንም እየሰማን ይነግራቸዋል። የሚሊኒየሙን ዝግጅት ገንዘብ እነ ኤፍሬም ከበሉት በኋላ ኤፍሬም ከብሮበታል። ሆቴሉን አደራጅቶበታል። በገዳማት ስም የተሰበሰበውን ገንዘብ ለእነ አቡነ ማርቆስ የቤት ዕቃ፣ አሁን ደግሞ ማሽን፣ የአሜሪካ ደርሶ መልስ ትኬት ገዝተው ተጎዝጉዘውባቸዋል። ለዚያ ነው አቡነ ማርቆስ የጎጃሙ ቅባቴ፣ አሁን ነኒዮርክ ኮሮና እስረኛ አድርጎ ከቤት እንዳይወጡ ያደረጋቸው ጳጳስ ለእነ በጋሻው ጥብቅና የቆሙት።

•••
እስከ መጨረሻው እንደ ዱዳ ዝም አልኩ። ኋላ ሁለቱ ታዛቢዎች እስቲ አባታችን የእሱን ደግሞ እንስማ አሉና ለእኔ መድረኩ ተሰጠኝ። እኔ እንዴት እንደምጀምር ስቁነጠነጥ ቀልባቸውን ገፍፌ እንዴት መጀመር እንዳለብኝ አምሮኝ ሳዛጋ ሳፋሽክ ስለነበር ጊዜዬ ሲደርስ የጭቃ ጅራፌን ፈትቼ ማጮህ ጀመርኩ። የጵጵስና ቆብ አስኬማውን ባያደርጉም ጳጳስ እንደሆኑ ገብቶኛል ግን እኔ እንደ አንድ መነኩሴ መቁጠር ፈለኩና ባላወቀ ሙድ ገተታዬን ጀመርኩ። ልጀምር ነው። ጀመርኩ።

•••
ሲጀመር እኔ አንተን አላውቅህም። አባ ማርቆስ የሚባል ሰው ስም ሰምቼም አላውቅ ብዬ “ አንተ” ብዬ ስጀምር የሁሉም ዕጢ ዱብ ሲል ይሰማኛል። እኔም ሆን ብዬ ነው። ( ስናውቅ በድፍረት፣ ሳናውቅ በስህተት እንዲል መጽሐፉ) በድፍረቱ ቀጠልኩና አከታትዬም እንኳን መንፈሳዊ ኮሌጇ ገብቼ ወጥቼ ይቅርና ተራ ምእመን እንኳ ብሆን ለሃይማኖቴ ለመመስከር የእናንተ ፈቃድ አያስፈልገኝም። አቡነ ማርቆስ የሚባሉ አባት ከእነ በጋሻው ጋር እንደሚሠሩ በወሬ ደረጃ እሰማ ነበር። እነ በጋሻው በጥቅም እንደያዙዋቸው እዚያው ከነበጋሻው ጋር ያሉ የመረጃ ምንጮቼ ነግረውኛል። ይኸው ዛሬም የበጋሻው አለቃ ጉቦ እጅ መንሻ ለአንተም ሲሰጥህ እጅ ከፍንጅ ተጋልጧል። አባ ማርቆስ ማለት ጳጳሱ እርስዎ ከሆኑ ( ሪትሙን ቀየርኩት ከአንተ ወደ አንቱ ) የመጨረሻ የሌባ ተቀባይ ሌባ ነዎት። ውጊያዬ ከእርስዎም ጋር ይሆናል። የእምነቴ የበላይ ሃላፊ ሆነው እንዲባርኩኝ ተሾሙ እንጂ ከሌባ ጋር እንዲሰርቁ፣ ከመናፍቅ ጋር ተባብረው ሃይማኖቴን እንዲያፈርሱ አይደለም። ይሰሙኛል አልኩ ደንፋ እያልኩ ይሰሙኛል ጎፍታው እኔም እርስዎም በሃይማኖቷ የባለቤትነት ጉዳይ ድርሻችን እኩል ነው። የምንለያየው በሥራ ድርሻ ነው። እርሶ ባራኪ እኔ ተባራኪ። ከኑማጋዱቢን አልኩላችኋ።

•••
አባ ሃይለማርያም አቋረጡኝ። ዘመዴ ቀስ በል። እኛ እናውቅሃለን። ብፁዕነታቸው ስለማያውቁህ ነው። ቀስብለህ አስረዳቸው አሉ። ወልደሩፋኤል ግን ፈንዲሻ መስሏል። በህይወት ዘመኑ እንደዚህ አይነት ሙጢ የሆነ ቀውጢ የሀረር ቆቱ ገጥሞት ያውቅ አይመስለኝም። አቡኑ ጭብጦ አክለዋል። ዝም ጭጭ ከማለት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም። መጀመሪያ ነው የሸወድኳቸው። ሱፍ ለብሼ ብመጣ ኖሮ ልብሴን አይተው የሆድ የሆዳቸውን አይነግሩኝም ነበረ። ቦርኮ መስዬ መሄዴ ነው የጠቀመኝ። እንዲህ ሆኜ እየሄድኩ ስንቱን ጉድ አደረኩት መሰላችሁ። ወዲያው አቡነ ማርቆስ በሉ ሁለታችሁ ውጡና ከእሱ ጋር አንደዜ ላውራ አሉ። ሁለቱም ወጡ። እኔና እሳቸው የልብ የልባችንን አወራን። ብዙም መረጃ ነገርኳቸው። መመሪያም ሰጠኋቸው። [ ተከባበርን ] አከተመ።

•••
ከዚያ በኋላ ነው እኔ በሰጠሁት ጥቆማ እነ በጋሻውና መንጋ ሠራዊቱ በሙሉ ቤተ ክህነት ተጠርቶ፣ ፎርም ተዘጋጅቶ። ዲያቆን ነኝ፣ ቄስ ነኝ ሲል የነበረውን ሁላ ዲቁና የሰጠህ ማነው? ክህነት የሰጠህ ማነው? ብለው ፎርሙ ሙሉ ሲባሉ አይን ፍጥጥ ጥርስ ግጥጥ የመጣው። በጋሻው ተነስቶ በአቶ ስብሐት ነጋ፣ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በአምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተመክቶ “ የማንም ነጋዴ በሚያዛችሁ እየተመራችሁ ከእናንተ ጋር አንስማም ” በማለት ጣጥለዋቸው የወጡት። ኤትአባታቸው። እሳትና ጭድ አደረግኳቸው። እነሱ ኢህአደግን፣ እኔ ደግሞ ድንግል ማርያምን ይዤ ውጊያችን ቀጠለ። የአባ ማርቆስ በሌላ አንቀጽ ይቀጥላል።

•••
ፈተናው ቀላል አልነበረም። ከእኔም አልነበረም ኃይልና አሸናፊነቱ። ከላይ ከአርያም ነበር። ለዚያ ነው በ52 ኪሎው ዘመዴ 96 ኪሎው የሐረር ሰንጋው በጋሻው ተወግቶ የወደቀው። ጠቅ እኮ ነው ያደረጉት። ኩንታሉ በእኔ በመርፌዋ ተነፈሰ። ተተረተረ።

•••
ከዚያ ነው እነ በጋሻው ወሮ እጅጋየሁን። እነ ፋንታሁን ሙጬን፣ ከሊቃውንት ጉባኤ ዛሬ ተወግዞ የጴንጤ ሃይማኖት የመሰረተው አእመረ አሸብርን ይዘው አባ ጳውሎስን፣ አቡነ ሳዊሮስን፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን ይዘው ፎገሉ። ከውጭ እነ አቦይ ስብሐትን ከውስጥ አሁን የዋሽንግተን ዲሲውን እነ አቡነ ፋኑኤልን በእጃቸው ስር አስገቡ። አቡነ ፋንኤል ጭራሽ አዋሳ ገብርኤል ሺዎች በተሰበሰቡበት “ መጋቤ ሀዲስ“ የሚል የማዕረግ ስም ሰጥተው አፎገሉት። ኋላ ላይ ቢቆጫቸውም፣ ቢጸጸቱም ያኔ ግን ደግ አልሠሩም ነበር።

•••
ታሪኩ አበራ ዮሴፍ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ። አብሮት ናሁሰናይ የሚባል የራበው ልጅ ተመደበ። ናሁሰናይን ብሔረ ጽጌ ማርያምን እኔ ዘመዴ ስመሰርት፣ ስቆረቁራት ደጅ ሲጠና አይቼ ( እነ ዲን ሐጎስ ከሚባል ልጅ ጋር) ራሴው የቀጠርኩት ልጅ የነበረ ነው። የራበው ስለሆነ ለምንፍቅናቸው መረጡት። ሀብታምም አደረጉት። በስንት ተጋድሎ ተሃድሶ ከዮሴፍ ተመነገለ። ታሪኩም ቀኑ ጨለመበት።

•••
ታሪኩ እንዴት እንግሊዝ ሄደ? እዚያስ ምን አባቱንስና ነው የሚያደርገው? ወደ በኋላ እመለስበታለሁ። ዛሬ ታሪኩን ታሪክ አድርገን ለዛሬ ቀጥሪያት የነበረውን የስንዱን ጉዳይ በነገው ዕለት ስንወያይበት እንውላለን። በስንዱ ጉዳይ ግን ( መንግሥትም፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፣ የአዲስ አበባ የኮልፌና የመርካቶ ወጣቶችና ህዝበ ክርስቲያኖችም እንድትሰሙኝ ግድ ይላል) የነገ ሰው ይበለን።

•••

 

“ግሪታዴ” ታሪኩ አበራ !!

[ ክፍል ፭ ]

~ ዘና፣ ፈታ፣ ብላችሁ አንብቡት።

•••
ዓመተ ምህረቱን አላስታውሰውም። ትዝም አይለኝኝም። ዕለቱ ጥር 21 ቀን ነው። የአስተርእዮ ማርያም ምሽት። ሰዓቱ ከምሽቱ 1:30 ይሆናል። በድንገት የመቅደላ መንፈሳዊ መዝሙር ቤት ባለቤት የአቶ ታዬ ልጅ ኢየሩሳሌም ታዬ ( ጄሪ) እና የኤመርሰን ማተሚያ ቤት ባለቤት አቶ መስፍን በዚያ ምሽት ከሱቄ መጡ። ቅድስተ ማርያም ተሳልመው መስፍኔ ጄሪን ሊሸኛት መምጣቱን ነገረኝና እንደቀልድ ጨዋታ ጀመርን። ሱቅ የምትሠራዋን ሠራተኛዬን ወደ ቤቷ እንደትሄድ አደረግኩና ከመስፍኔና ከጄሪ ጋር ወሬዬን መሰለቅ ቀጠልኩ።

•••
ወሬው ያው በእነበጋሻው ዙራያ ነው። አይዞህ እያሉ የማጀገኛ ሐሸሺ የሆነውን የአባሻ ማበረታቻ ይወጉኛል። ዘመዴ እኮ ወንድ ነህ፣ አንጫጫሃቸው፣ ይሉኛል። የሚገርመው ግን እንደዚያ እያሉኝም መስፍኔም ለእነ በጋሻው ከቨር ማተሙን፣ ጄሪም ካሴታቸውን መሸጧን አለማቆማቸው ነበር። እኔን ያስጀመሩኝ እነሱ ይመስል አይዞህ፣ በርታ እያሉ እነሱ ከጀርባ ይሸቅላሉ። ያልገባኝ በመምሰል እሺ እላቸዋለሁ። ሰዓቱ ገፋ 3:30 ሆነ። በሉ ይመሽብናል እንሂድ ተባብለን ተነሣን። መስፍኔ ልሸኝህ ሲለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ማድረግ አለብኝ ብዬው ግብዣውን ሳልቀበለው ቀረሁ። ሁለቱ ሄዱ።

•••
አዲስ ስልክ ነበረችኝ። ከገዛኋት ሳምንት አይሆናትም። የእነበጋሻው ቲፎዞዎች ደውለው ሲሰድቡኝ እየቀረጽኩ እዝናናባቸው ነበር። እና እሷን ስልኬን ጆሮዬ ላይ ሰክቼ ወደ ጊዮርጊስ ልሻገር ስል አንድ የሹራብ ቱታ ከነኮፍያው ያደረገ ልጅ ስልኬን እንደ ጭልፊት ቀምቶኝ ወደ ጊዮርጊስ መቃብር ቤቱ ጋር በሩጫ ነካው። እኔም አብሬው ነካሁት። ስደርስበት ይፈጥናል። የማውቀውም ሰው መሰለኝ። ስሏኳ ወደ 3 ሺ ብር ያወጣሁባት ስለሆነች ብሩም ቆጭቶኛል። ይውሰዳት የማልላትም ብዙ መረጃም የያዘች ነበረች። እናም ተከተልኩት። የሆነች አይጥማ ከለር ያላት ወያኔ ዲኤክስ መኪና ጋር ቆመ። ስደርስበት መኪናዋን ይሸከረከራል። ከመኪናዋ ውስጥ አንድ የሰማይ ስባሪ የሚያክል ሰውዬ ወጥቶ ሌባዬን ያዘልኝ።

•••
ኤት’ አባቱ ብዬ ወደ ተያዘው ሌባ ስሄድ ጎልያዱ ሰውዬ እኔኑ ማጅራቴን ጨምድዶ መኪናው ውስጥ እንድገበሰ አስገደደኝ። መኪናው የኋላ ወንበር ውስጥ ስገባ እኔ ነኝ ያለ ፊልም ላይ ብቻ አይቼ የማውቀው መጋዝ የመሰለ ጩቤ ጭኑ ላይ ያስቀመጠ ሌላ ጥርብ የሰማይ ስባሪ የሚያክል ሰው ተቀምጧል። ጨምድዶ ከመኪናው ያስገባኝ ጎልያድ የሚያክለው ሰውዬም ከጎኔ ተቀመጠ። ስልኬን የቀማኝ ሯጩን ሁሴን ቦልትን የሚመስለው ልጅ ከፊት ከጋቢናው ገባ። ይሄ ጨምዳጄ ሽጉጥ አውጥቶ መመሪያ መስጠት ጀመረ። ሁላቸውም መንጽርና ኮፍያ አድርገዋል።

ቢመሽም ሰዎች በአካባቢው ይታዩኛል። አንዳቸውም ግን ምንተፈጠረ ብለው ወደ መኪናዋ የቀረበ ሰው ባለማየቴ ጨነቀኝ። ሰው ግን እንዴት ጨካኝ ነው። እያዩኝ ዝም። እንዳልጮህ እንኳ ድምፄን ማን እደሰረቀኝ መድኃኔዓለም ይወቅ። እንኳን ለጩኸት ትንፋሽም ራሱ እያጠረኝ ነው።

መመሪያ አንድ፦ ወደ እኛ እንዳታይ።

መመሪየ ሁለት፦ ምንም ዓይነት ንግግር አይፈቀድልህም።

መመሪያ ሦስት፦ አንገትህን በፊት ወንበር መሃል ድፋ ብሎ
ጨምዳጄ አዳፍቶ አሳየኝ። እኔም አንገቴን ደፋሁ። በድንጋጤ ሽንቴ ጭርቅ ብሎ ሲያመልጠኝ ይታወቀኛል። እንዴት እንደሚገድሉኝ እያሰብኩ ሳልጭርስ መኪናው መንቀሳቀስ ጀመረ። ከፊት ያለው ስልኬን የቀማኝ ልጅ ስልኬ ሲጠራ እያነሳ ይነግራቸዋል። ማሚ ናት፣ ታዬ ነው፣ አብርሃም ዳልሻ ነው እያለ ይነግራቸዋል። ቆይቶ ጨምዳጄ ስልኩን ባትሪውን ንቀለው ተባለ እሱም ነቀለ። የስልክ ጥሪዬ ቆመ።

•••
መኪናው አይቆምም ዝም ብሎ ይሄዳል። ደብረ ብርሃን የደረስን መሰለኝ። ወይም ናዝሬት። ብቻ ይነዳዋል። እኔ በአንገቴ ተደፍቼ የሌለ ነገር አስባለሁ። ምንአለ ቢቀርብኝ? ምነው ዝም ብል? ስንት ጀግና እያለ ዝም ብዬ እንደመቀመጥ ምን አንቀዠቀዠኝ። በቃ ወይ ሊያርዱኝ። ወይ በጥይት ይገሉኛል። እያልኩ አስባለሁ። አስከሬኔ ከሆነ ጥሻውስጥ ሲገኝ፣ ቤተ ሰቦቼ፣ ጓደኞቼ ሲያለቅሱ። ጋዜጦች ሲዘግቡት፣ የፖሊስ ፕሮግራም ምርመራው እንደቀጠለ ነው ሲል። ግማሹ ወያኔ ሌላው ደግሞ እነበጋሻው ናቸው ያስገደሉት እያለ ሲጨቃጨቅ ይታየኛል። መኪናው ይሄዳል።

•••
አንድ ጊዜ ነዳጅ ሲቀዱ አስታውሳለሁ። አንድጊዜ ደግሞ የሆነ ሰካራም ድንገት ገብቶባቸው ፍሬን እንቅ ሲያደርግ ከፊት ለፊት በውስጥ በኩል የቤተ መንግስቱን መንገድ አይቼዋለሁ። የሚያሽከረክሩኝ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ እንደሆነ ገብቶኛል። ግን መኪናው አይቆምም። በመጨረሻ ለሹፌሩ ስልክ ተደወለለት። በትግርኛ አወራ። ይዘውኝ መጣን፣ መጣን እሺ ሲል ይሰማኛል። ይዘውኝ ነጎዱ። ኮሮኮንችም፣ የኬር ድንጋይም አስፋልትም መኪናዋ እየረገጠች ወደ አንድ ግቢ ጋር ቀርበው የሚካና ጥሩንባ አሰሙ። ተከፈተላቸውና ወደ ውስጥ ገባን። እኔ እንዳቀረቀርኩ ነው።

•••
ታፋዬና ወገቤ ተንቀጥቅጧል። ጉልበቴ ዝሏል። ጫፌን ግን አልነኩኝም። እስከአሁን ድረስ አልሰደቡኝም። ስልኬን የቀማኝ ልጅና ሹፌሩ ወረዱ። ቆይቶ ስልኬን የቀማኝ ልጅ የሆነ የጅንስ ሸሚዝ የመሰለ ነገር አምጦ ለጨምዳጄ ሰጠው። ውረድ ቀና ግን እንዳትል አሉኝ። ወረድኩ። ግዙፍ ዋርካ የመሰለ ዛፍ አይቻለሁ። ከዚያ ግን ያን የጅንስ ሸሚዝ የመሰለ ነገር ራሴ ላይ ጣል አድርገው ጨምዳጄ ወደ መሬት አስጎንብሶ በሆነ የድሮ ቪላ በመሰለ አሮጌ ቤት በጀርባ በኩል ይዘውኝ ገቡ። ወስደውም ከሳሎኑ አስቀመጡኝ። ሸሚዙንም አነሱልኝ። ሳሎኑ የድሮ ነው። አሮጌ ነው። ኦና ነው። ሽሮ ከለር የተፈቀፈቀ ቀለም አለው። አንድ ወንበር ብቻ ነው ያለበት። መሬቱም ተወልውሎ የማያውቅ አሮጌ ሳንቃ ነው። አንዲት 60 ሻማ አምፖል ይታየኛል። አበቃ።

•••
ጨምዳጆቼ ስፖርተኛ ይመስላሉ። ለምን ከጫማቸው እስከመነጽራቸውና ኮፍያቸው ድረስ ጥቁር በጥቁር እንደለበሱ ግን አላውቅም። አስቀምጠውኝ ወጡ። ብጠብቅ፣ ብጠብቅ አይመጡም። ጭንቀቱ ሊገለኝ ደርሷል። ያ ሁሉ ፉከራዬ ገደል ገብቷል። ከእነ ታሪኩ አበራ ጋር የተሳፈጥኩበትን ቀን እየረገምኩ ነው። አርፌ ካሴቴን እየቸረቸርኩ እንደመቀመጥ ምን አቅብጦኝ ነው በዚያ የተረገመ ቀን ከተሃድሶ ጋር የተጣላሁት እያልኩ ከራሴ ጋር እሞግታለሁ። በማሃል በርታ አይዞህ አትንቦቅቦቅ የሚል መንፈስ ቢመጣብኝ። ኧረ ተው ጌታዬ በዚያ ሰዓት አልሰማውም። አይጣል እኮ ነው። አባዬ አሁን እንደምትለፈልፈው አይደለም። ሞት ሲዘገይ ይጨንቃል። በአፍ እየፎከሩ ተግባር ላይ ዜሮ የሚሆኑት ወደው አይምሰልህ። ማንም መሞት አይፈልግም ይጨንቃል።

•••
ከውጭ በስልክ ሲጨቃጨቁ ይሰማኛል። ከስልኩ በኋላ ደግሞ ሁለቱ ሰዎች የጦፈ ጭቅጭቅ ውስጥ ናቸው። እኔን ግን አባከና የሚለኝ ጠፍቷል። ሱሪዬ ላይ በድንጋጤ የለቀቅኩት ጭርቅ ያደረከት ሽንቴም ደርቋል። ረሃብ የለም። ከመደንገጤ የተነሳ ምላሴ ምራቅ ማምረት ስለተወ ውኃጥም ብቻ ሊደፋኝ ይመስላል። ቆይተው፣ ቆይተው እነዚያ ቦዲጋርድ የሚመስሉት የጎልያድ ወንድሞች ወደኔ ገቡ። ገቡናም እንዲህ አሉኝ… …

 

 

•• ይቀጥላል

“ግሪታዴ” ታሪኩ አበራ !!

[ ክፍል ፮ ]

 

••• ይቀጥላል … ብዬ ነበር ያቆሙት እንቀጥላለን።

አፋኞቼ ገቡና አንዱ በሩ ላይ ቆመ። አንዱ ደግሞ ከእኔ በቅርብ ርቀት ቆሞ ያወራኝ ጀመር። አንተ ለምን አባህ ነው የማታርፈው? ምን ያንቀዠቅዥሃል? አለኝ። ቀጠለናም በየመጽሔቱ እየወጣህ ያለልክ አፍህን ትከፍታለህ። ምንአባህ ብትተማመን ነው እንዲህ የምትተረተረው? ከአንተ ጀርባ ያሉት እነማን ናቸው? ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያለህን ግኑኝነት እናውቃለን። ግንቦት 7፣ መከረኛው ሻአቢያ እንደየማዕረጋቸው ተጠሩ። በትንሹ ፍርሃት ሲለቀኝ ይሰማኛል። ቀጠለ ለዚህ ጩኸትህ ይሄ የደርግ ስብስብ፣ የደርግ ወታደር ትራፊ የሆነ ማኅበር 30 ሺ ብር እንደከፈለህ እናውቃለን። ደርሰንበታልም። እና ለምንድነው የማታርፈው? እያለ ደነፋብኝ። ፍርሃቴ በልቤ ውስጥ እንዳለ ነው። በጥፊም በካልቾም ግን አላሉኝም። የሚታፈን ሰው ይደርስበታል የሚባለው ነገር ይደርስብኛል እያልኩ ብጠብቅም ከወሬ በቀር ዘገየብኝ። ልቤ እንደተንቦቀቦቀ እያወቅኩ አፌ ግን አምልጦ ጉድ ሠራኝ። ከምር ለምን እንደዚያ እንዳልኩ እስካሁን መልስ አላገኘሁለትም።

•••
ድንገት ኤፕ ብዬ ከመሬት ተነሥቼ “ባክህ ምንም አታመጡም፣ አንድ ነፍስ እኮ ነው ያለኝ። እንኳን እነ በጋሻው ራሱ ዲያብሎስ ለምን አይመጣም። እኔ አመዴ አልፈራም” ብዬ የሌለ ደነፋሁ። የመድኃኔዓለም ያለህ ምን መሆኔ ነው ግን? ቅድም በድንጋጤ ሽንቴ ጭርቅ ብሎ አምልጦኝ ጉድ እንደሆንኩ እያወቅኪ አሁን ተለማምጦ ሁለተኛ አይለምደኝም ብሎ ከዚህ ሲኦል እንደመውጣት የሌለ ጉራዬን በባዶ ሜዳ እቸረችራለሁ። ልቤ ተው ይለኛል። አፌና ምላሴ ግን የሌለ ይቀባጥራሉ። አፋኜ ሲቆጣኝ እቆጣዋለሁ። ሲጮህብኝ እጮህበታለሁ። ዝም ሲል ደግሞ ይጨንቀኛል። ወበራሁ። ቀላል ወበራሁ።

•••
መልሶ ጠየቀኝ። እነበጋሻው ምን አደረጉህ? ምንስ በደሉ? ምንድነው ጥፋታቸው። በቤተ ክርስቲያን ያለውን የደብተራ ትብታብ በወንጌል ብርሃን የገለጡ ወንጌላውያን ልጆች ናቸው። እነ ዘርአያእቆብ ያመጡትን ትብታብ የበጠሱ ናቸው። ህዝቡን ከሸዋና ከጎጃም ደብተራ ትብታብ በገላገሉ ምን ይሁኑ ነው የምትለው? አለኝ።

•••
መለስኩለታ ስማ የበጋሻው እናት እኮ ባለዛር ጠንቋይ ናቸው። እስከ አሁን ድረስ ጫት ይቅማሉ። ማእከላዊ በጋሻው ታስሮ ሊጠይቁት መጥተው በነበረ ጊዜ እኔ ፊት እኮ ነው ኒያላ ሲጋራቸውን ሲያንደቀድቁ የነበሩት። የጠንቋይ ልጅ፣ የባለዛር የመተታም ልጅ ነው። የገዛ ወላጅ እናቱን ከመንደር ጥንቆላ ያላወጣ ሶዬ ምን ሆኖ በምን አቅሙ ነው ህዝብን ከሰይጣን እስራት የሚፈታው? ተው እንጂ ምን ማለትህ ነው። ዘማሪ ህጻን ዕዝራ እኮ ባሳደገው ሰው ተደፍሮ ሉጢ የሆነ ነው። ሐዋዝ ሚጢጢ ፓስተር ነው። አሰግድም ጴንጤ ነው። ዘርፌ ሴተኛ አዳሪ ናት። ራሳቸው ሳይድኑ ማንን ነው የሚያድኑት? ትዝታው እኮ ወንድኛ አዳሪ ነው። እና እነሱ ናቸው ህዝብ የሚያድኑት በል አትቀልድ። ሃይ ምንድ ነው ሳ ! ደግሞም መንግሥት ለምን እነሱን ይደግፋል? ይዋጣልን። እነሱ ቴሌቭዥን አላቸው። እኔ ደግሞ ምንም የለኝም። ፌስቡክ ነው የምጠቀመው። ለምን አይዋጣልንም ህዝቡ ፍርዱን ይስጥ፣ እናንተ ተዉን አልኩት። መልሼም እኔ ማኀበረ ቅዱሳን አይደለሁም። ካስፈለገ ስልኬንም ጠልፋችሁ ውሎዬንም መከታተል እየተቻለ የምን ከመሬት ተነስቶ መፈረጅ ነው ብዬ እምቧ ከረዩ አልኩ።

•••
ቆይ ቆይ አለኝ አፋኜ። ቀይ የበጋሻው እናት ጠንቋይ ናቸው፣ ሲጋራም ያጨሳሉ፣ ጫትም ይቅማሉ ነው የምትለው? አለኝ አዎ በሚገባ አልኩት። አዎ የጠንቋይ ልጅ ነው አልኩት። ባለዛር ናት እናቱ አልኩት ግግም ፍርጥም ብዬ። ቆይ አንድ ጊዜ አለና ተመልሰው ሄዱ። ሄደው በጣም ቆዩ። የበለጠ እየጨነቀኝ መጣ። የበጋሻውን እናት ከዲላ ሊያመጣት የሄዱ ነው የሚመስለው። ሰዓቱ ከሌሊቱ 6 ሰዓት እየሆነ ነው። ራሱ በጋሻውን ጠርተው ሊያስጠፈጥፉኝ ይሆን እንዴ ብዬም አሰብኩኝ። ፍርሃቴ ግን አይጣል። ደግሞ ስንቆራጠጥ በድብቅ ካሜራ እያዩኝ የፈራሁ እንዳይመስላቸው በማለት ምንም የፈራሁ ላለመምሰል እታሻለሁ። ይሞታል እንዴ?

•••
ቆይቶ መጣ። ተነስ አለኝ ጨምዳጄ። ተነሳሁ። ያን የተለመደ የጅንስ ሸሚዝ የመሰለ ነገር በእጁ ይዟል። እሷን ነገር ሳይ አሁን ደግሞ የት ሊወስዱኝ ይሆን ብዬ ማሰብ መጨነቅ ጀመርኩኝ። ጭንቀቴን በትንፋሽ መልክ ማስወጣት ስፈልግ በአክሽን የቁጭት እያስመሰልኩ ፍርሃቴን በረጅም ትንፋሽ እገላገለዋለሁ። እነሱ ሲያዩኝ የፈራሁ እንዳይመስላቸው እኮ ነው። ሽንቴ ወጥሮኛል። ሽንቴ መጣ ብዬ ከጠየኩ ፈርቷል ይሉኛል ብዬ ዋጥ። ቀጥል እንሄዳለን ውጣ አለኝ። የት ነው የምንሄደው ልለው ፈለኩና እስከአሁን እዚህ ድረስ እንደበግ ሲነዱኝ ያልጠየኩ አሁን ምን ብዬ ነው የምጠይቀው ብዬ ከአፌ መለስኩት። መድኃኔዓለም ነው የጠበቀኝ። ሸሚዟን ጣል አድርጎ እየመራኝ መንገድ ስንጀምር ይቅርታ አልኩት ጨምዳጄን። ይቅርታ የበጋሻው እናት ውቃቢያም አይደለችምን አልኩት። እኔ ምናገባኝ ለምን ዘንዶ አትሆንም። አፍህን ዝጋና ዝም ብለህ ሂድ አለኝ። ምን አማራጭ አለ? እንደ ቄራ በሬ ወደ ቄራ እየተነዳሁ ወደ መኪናዋ ነካሁት። እንደቅድሙ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን።

•••
ለአንድ 30 ደቂቃ ያህል እንደተጓዝን መኪናዋ ቆመች። ሸሚዟን ከላዬ ላይ ሳያነሱ መመሪያ ሰጠኝ ጨምዳጄ። ስልኩን ስጠው ተባለ ሁሴን ቦልት። ስልኬን ሰጠኝ። በዚያ በኩል ውረድ አለኝ። በጎልያድ በኩል ወረድኩ። ሸሚዟን ከላዬ ላይ አንስቶ ከመኪናዋ ኋላ አቆመኝ። ታርጋው ባለበት ጋር ታርጋዋን ሸፍኖ ቆመ። መኪናዋ የቆመችው ራስ መኮንን ሃውሉት ፊት ለፊት ጨለማው ውስጥ ነው። አይ አልኩኝ። እዚህ ጠብሰው ወንዙ ውስጥ ሊጥሉኝ ነው ብዬ ተብረከረኩ። ነገር ግን ነገርየው ሌላ ሆነ።

•••
ጎልያድ እንዲህ አለኝ። ዘመዴ ዛሬ እግዚአብሔር አውጥቶሃል። እዚህ ሚሽን ላይ እኔ ሹፌሩና ስልኩን የቀማህ ልጅ መሳተፋችን ጠቅሞሃል። ባይሆን እንደ ብዙዎች ሟች ነበርክ። እስከ አሁን የምንጨቃጨቀው በአንተ የተነሣ ነው። ጨርሱት ነበር የተባልነው። እኔ ግን አንተ ለጅማ ገዳማት በስብሰባ ማእከል አቡነ እስጢፋኖስ ጋብዘውህ ያስተማርክ ቀን እኔ ለደኅንነት ሥራ ተልኬ እዚያው ነበርኩ። እናም ያኔ ስታስተምር ያለቀስኩት ለቅሶ እስከአሁን አስታውሳለሁ። እናም ዛሬ ይሄ ነገር ሲመጣ እኔ ከሚሽኑ መውጣት ያልፈለኩት በተቻለ መጠን የማተርፍህን ነገር ለመፈለግ ብዬ ነው። ሁለት ነገር እነግርሃለሁ ከእነ ፊደል ሬስቶራንት ባለቤት ከእነ ኤርትራዊው ኤፍሬም ጋር አትሳፈጥ። ከነበጋሻው ፊት ቢቻልህ ዞር በል። እንዳየንህ ግን ሞትም የምትፈራ አይደለህም። ሌላው እባክህ አታምሽ። ከቻልክ ወደ ቤትህ ስትሄድ አንድ ሰው አብሮህ ይኑር አለኝ። ገረመኝ። አምላኬንም አመሰገንኩ። እነበጋሻው እነ ታሪኩ አበራ ግን ከጀርባቸው ያለውን ኃይል አሰብኩት። ይሄኛው ልጅ ብቻ ነው የማያውቅህ አላኝ ጨምዳጄን መሆኑ ነው። የደቡብ ልጅ ነው። ሾፌሩ ግን የትግራይ ልጅ ነው። ክርስቲያን ነው። ሁሴን ቦልት የአዲስ አበባ ልጅ ነው። እኔም የናዝሬት ልጅ ነኝ። የመኪናዋን ታርጋ እንዳትመለከት አዝሃለሁ። ለፖሊስ ብትከስም ዋጋ የለውም። ግን መክሰስ ትችላለህ። ወደ ኋላ ሳትዞር ቀጥ ብለህ እያየሁህ ሂድ አለኝ።

•••
ላመስግነው ወይስ ዝም ልበለው። ጨነቀኝ። ካመሰገንኩት ለካስ ጨንቆት ነበር ብሎ ቢታዘበኝስ። ቅድም ያመሰገነኝና ሞት አትፈራም ያለኝ እኮ ውስጤ እየፈራ እትት የሚለውን ምላሴን አይቶ ነው። አዎ ጨነቀኝ። እንዲህ ተፋልጦ ከሞት አድኖኝ ደግሞ ዝም ብሎ መሄዱም ጨነቀኝ። ከዚያ ምስጋናውን ትቼ ጀብዱ ጀብዱ መጫወት አማረኝ። እናም ከምክሮቹ ሁሉ አታምሽ ብቻህንም አትሂድ ያለኝን ሀረግ መዝዤ አወጣሁና “ እኔ በነፃነት እሄዳለሁ። ሀገሬ ነው ምናምን ብዬ ገና ተበጥርቄ ሳልጨርስ ከአፌ ነጠቀኝና በል አትዘባዘብብኝ። የራስህ ጉዳይ አሁን ወደ ቤትህ ሂድ አለኝ። ይሻለኛል። ቢያንስ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ፈሪ ያለመሆኔን አሳይቻለሁ። ቀኝ ኋላ ዞሬ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ያለውን መስመር ይዤ ቆምኩ። አንድ ላዳ ሲበር መጣ አስቆምኩት። ሰፈሬን ነግሬው ገባሁ።

•••
የታክሲ ሹፌሬ ዘመዴ ከየት ነው አለኝ። ከየት ልበለው። አይ ከዚህ ነው አልኩና መንገድ ጀመርን። የጊዮርጊስን ዳገት መውጣት እንደጀመርን ያ ሽንቴ የት ተደብቆ እንደቆየ አላውቅለትም ድንገት መጣ። አንዴ አቁምልኝ ብዬ ጫፉ ላይ ቱቦው ላይ ቆሜ ለቀቅኩት። ሽንቴ ልክ እንደዘማሪ ታዲዮስ ግርማ ሽንት አላልቅ አለኝ። ( የታዲን ገጠመኝማ ሌላ ቀን ዓመት ያህል ነው የማስቃችሁ። ኤት‘አባቱንስና። ምርጥ አብሮአደግ ወንድሜ ነው። እንደጉድ እቀልድበታለሁ። ምንዳዬ፣ ቴዲ ዮሴፍ አይቀሩኝም) ልክ ታክሲው ውስጥ ገብቼ ስሄድ የአፋኞቼ መኪና አልፋኝ ሄደች። ታርጋዋንም ያዝኳት። አከተመ።

•••
ከዚያ እቤት ስሄድ ሃገር ቀውጢ ሆኗል። መላ ቤተሰቡ ፖሊስጣቢያ አምሽቶ ነው የመጣው። የደረሰብኝን ሁሉ አንድም ሳላስቀር ተረኩላቸው። እነዚያ ያዳኑኝን ገዳዮቼን ማንነት ሳላውቅ ከአገር ተሰድጄ ወጣሁ።

 

 

ሻሎም ! ሰላም !

ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ሚያዝያ 3/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።

Filed in: Amharic