>

እኛም እስኪ እንደ አባቶቻችን...!!!! ሔቨን ዮሐንስ


እኛም እስኪ እንደ አባቶቻችን…!!!!

ሔቨን ዮሐንስ
 
የጠቢባን ምክር:-
ሊቃውንት አባት ደቀመዝሙራቸውን ሲያስተምሩት ሂድና ወደ መቃብሩ ስፍራ ሙታኖችን በደንብ ሰድበህ ና አሉት። ተማሪውም የተባለውን ትዕዛዝ ለመፈፀም እየገሰገሰ ሄዶ መቃብሩ ስፍራ ሲደርስ ሙታኖችን ሙልጭ አድርጎ ሰድቦ ተመለሰ። ሊቃውንት አባቱም ተማሪያቸውን ሰድበህ መጣህ፤ ምን አሉህ? አሉት። ተማሪውም ምንም አላሉኝም አለ። እሺ አሁን ሂድና በደንብ አሞጋግሳቸውና የሚሉህን ትነግረኛለህ አሉት። አሁንም ሲበር ሄዶ ሙታኖችን አሞጋግሶ አሞካሽቶ ተመለሰ። ልጄ ስታሞጋግሳቸው ምን አሉህ? አሉት። እርሱም ምንም አላሉኝም አለ።
ሊቃውንት አባቱም የማሳረጊያውን ትምህርት ሲሰጡት  እይውልህ ልጄ በአለም ላይ  ፍሬ ማፍራት ከፈለግህ የሚሰድቡህንም፣ የሚያሞጋግሱህንም እንደ ሞተ ሰው ቆጥረህ ሳትሰማ ዝም ብለህ ያሰብከውን ስራ ብቻ ስራ። ሙገሳም ከወደድህ ከንቱ ውዳሴ ነውና አላዋቂነትህን እያጎላ ከስራ ውጭ ያደርግሃል። ስድብን ነቄፌታንም ካዳመጥህና ከፈራህ ልፍስፍስ ሆነህ አሁንም ከስራ ውጭ ሆነህ ትወድቃለህ። የሰው ጩኸት ሙገሳም ይሁን ነቄፌታ ካላዳመጥከው እንደ ሞተ ሰው ድምፅ ይሆናልና ዝም ብለህ ስራህን ከሰራህ ፍሬ ያዘለ ዛፍ ትሆናለህ አሉት።
እስኪ እኛም እንደ አባቶቻችን ነን ካልን ባህሪያቸውን እንፈትሽና ከእያንዳንዱ ባህሪ የሁሉንም መውረስ ባንችል የአንዳንዳቸውን እንኳ ለመውረስ እንሞክር!
* መይሳው ካሳ (አጤ ቴዎድሮስ) :-
የዝሆኑም ለታ ጫካ ውድማውን ዋለ ሲያሰኝዎ
የሰይጣንን ለታ ግደለው.. ስደደው ዋለ ሲያሰኝዎ
የመላኩም ለታ አብረው ርቦታል አጠጣው ጠምቶታል ዋለ ሲያሰኝዎ…
የተባለለት ንጉስ አላማውን ለማሳካት ቆፍጠን መረር ያለ አገዛዝ መረጠ። መይሳው እንደ ኮሶ መሮ አልገዛም፣ አልገብርም ያለውን ዳተኛ ህዝብ በሀይል አንበርክኮ ሰጥ ለጥ አድርጎ ገዛ። ህግን ያረቀቀ፤ የማትደፈረውን ቅድስት ቤተክርስቲያን እንኳ ለሀገር ሳንካ አለባት ሲል በአንድ ደብር አምስት መቶና ከዛ በላይና በታች ሳይሰራ የሚቀለብ ውጣ ወደ ስራ ግባ ብሎ እንደ እየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ የገረፈ ቆፍጣና ነው። ሓላም ቀዳሽ ዲያቆንና ቄስ ከአምስት መብለጥ እንደለለበት ያስተካከለ፤ ያለዘመኑ ተፈጥሮ ሩቅ አልሞ ቅርብ የቀረ ጀግና መይሳው ነው። ያልተገራውን ህዝብ የገራ ለአላማው ኖሮ ለአላማው የሞተ ነው። ነቄፌታንም ድጋፍንም ፈፅሞ የማይሻ የልቡን ሃሳብ ብቻ የሚያዳምጥ ጀግና መይሳው ካሳ ነው ብቻ ነው።
* አጤ ምኒልክ (እምዬ) የሀሳብና የስሌት ሰው ናቸው። ያም መጣ ያም ሄደ አይሞቃቸው አይበርዳቸው ቸርና ለጋስ አዳማጭም ናቸው። በሀገራቸው ድርድር የማያውቁ የሚወዳቸውንም፣ የሚጠላቸውንም እኩል የሚወዱ ልዩ ሰው ናቸው። እነ ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ እነ አባጅፋር በጠላትነት ቀርበው ተማርከው እንኳ እንደ ጠላት ሳያዩ አክመው አስተምረው መልሰው ወደሚወዱት ቦታ ያመቻቹ ድንቅ ድፕሎማት ስራ የሚሰሩ ልብ ሰርሳሪ አዋቂ ናቸው። እምየም ያላቸው ንጉስ ተክለ ኃይማኖት ያደረጉለትን ደግነት አይቶ ነው። ከእምየ ታሪክ ከሚያስደንቀኝና ፈገግ ከሚያደርገኝ አንዱን ጀባ ልበላችሁ
እቴጌ ጣይቱ ወሎ ወልዲያ ተወልዳ ደቡብ ጎንደር አድጋ እዛው አግብታ ነበር። ሆኖም ከባለቤቷ ጋር ተለያይታ ከባላባት ቤተሰብና ቤተዘመዶቿ ጋር ደንቦል ደንቦል ስትል አጤ ምኒልክ ስልጣን ሳይዙ በፊት ሰራዊታቸውን ይዘው ወደ ጎንደር መተማ አሰሳ ወጥተው ሲመለሱ እራት ግብዣ ግብር በዘመዶቿ ቤተሰቦቿ ቤት ተደርጎላቸው ነበርና እቴጌ ጣይቱ አጋፋሪ ሆና ስትገማሸር እምየ ያዩዋትና ምንም ሳይተነፍሱ ይመለሳሉ። የእቴጌን ጥበብና ብልሃት የተረዱት ዝምተኛው መሪ ሂዱና ጠሃይቱን አምጡልኝ ብለው ላኩ። ጠሃይቱም መጣች በአንድ ጣሪያ ስር ነግሰው መኖር ጀመሩ።
የእቴጌ ጣይቱ የቀደመ ባሏ እቴጌ ናፍቃው ማየት ፈልጎ ለእምየ ምኒልክ ደብዳቤ ፃፈ። ንጉስ ሆይ የመጀመሪያ ሚስቴ ናፍቃኛለችና ማየት እሻለሁና ይፍቀዱልኝ የሚል ነበር። ደጋግሞ ደጋግሞ ሲልክ እምየ ምኒልክ እንዴት ይሄ ይሆናል ጠሃይቱንማ ማንም እንዳይብኝ አልፈልግም ሲሉ ከርመው በመጨረሻም ፈቀዱለት።
የእቴጌዋ የመጀመሪያ ባል ሲከንፋ መጥቶ መጀመሪያ እምየን ዘይሮ እቴጌን እንዲያይ ተፈቀደለትና አጋፋሪዎቹ ወደ እምየ እልፍኝ  ወሰዱት። የእቴጌ የመጀመሪያ ባል እጅግ መልከ ጥፋ ወታደር ነበርና እምየ ሲያዩት ፈገግ ብለው አንተ ነህ እኮ የጠሃይቱ ባል የነበርህ አሉት፤ አወ እኔ ነኝ አለ፤ አሁንም ገርሟቸው ፈገግ አሉና እኮ አንተ ነህ የጠሃይቱ ባል አሉት እርሱም ከአፋቸው ነጠቅ አድርጎ ይገርምዎታል ንጉስነትዎ ጠሃይቱ ሲሰራት ባል አይወጣላትም አላቸው። እምየም ያፈኑትን ሳቅ በደንብ ለቀቅ አድርገው ሳቁ። እምየን እርስዎም መልከ ጥፋ ነዎት ብሎ በግልፅ የተሳደበው የጠሃይቱ የመጀመሪያ ባል እጅግ ሲበዛ ቀልድ አዋቂ ነበርና እስከ እለት ሞታቸው በዛ ቤት እንድኖር ፈቅደውለት ይኖር ነበር።
* ንጉስ ሚካኤል :- ንጉሱ ደግሞ ድሃ ሃብታም፣ አዋቂ፣ አላዋቂ፣ ጤነኛ በሽተኛ፣ ካህን፣ ሸህ፣ እምነት የሌለው ብቻ የሰው ዘር ሁሉ በአንድ ማዕድ እንድቋደስ አይጠየፍን አስገንብተው ሁሉን እኩል እያዩ የሚያስተዳድሩ ነበሩ። ለጦረኝነት ደግሞ ማንም የማይገዳደራቸው የወሎም የትግራይም ንጉስ ሞገደኛ ነበሩ። እምየ ምኒልክን ትግራይም ወሎንም አላስገብርልህም እያሉ ሸዋ ድረስ ራስ ይመርን ይዘው ምድር ቁና ሲያደርጉ እምየ ብልህ ናቸውና ልጃቸውን ዳሩላቸው። ንጉስ ሚካኤልም የይቅርታ ሰው ናቸውና ሁሉን ይቅር ብለው ታርቀው በፍቅር ኖሩ። ወደ መጨረሻም ልጃቸው ልጅ እያሱ በራስ ተፈሪ (ጃኖሆይ) ሲታሰር ቁጡና ግንፍልተኛም ናቸውና ጦራቸውን ሰብቀው ወደ ሸዋ ገሰገሱ። የንጉስ ሚካኤል ጦር ሰገሌ ላይ የጃኖሆይን ጦር ጊዜ ሳይፈጅባቸው አደባዩት። ይህንን ያዩት ብልሃትኛው ፊታውራሪ ሀብቴ ንጉስ ሚካኤልን ታቦት አሸክመው ተማፀኗቸው። ንጉስ ሚካኤል የይቅርታና የእምነት ልብ ስላላቸው ሁሉን እርግፍ አድርገው ተቀበሉ። ጀግንነትና የይቅርታ ልብ ከአባታችን ከንጉስ ሚካኤል እንውረስ
* ንጉስ ተክለኃይማኖት :- እኒህ መኳንንት ለእምየ ምኒልክ አልገብርም ወዳ ክላልኝ ብለው ሲሟገቱ ሲፋለሙ በመጨረሻም እምየ ምኒልክ ማርከው ወደ እልፍኛቸው አስገባቸው። ቅቤውን ማሩን ጮማውን እየመገቡ፣ ጠላውን፣ ዝልሉን፣ ኮረፌውንና ጠጁን እያጠጡ፤ የንጉስ ተክለኃይማኖት ቁስል እምየ በእጃቸው በባህላዊ መንገድ እያከሙ እንድድኑ አደረጋቸው። ሲድኑም እምየ ንጉስ ተክለኃይማኖትን ተሽሎሃል ወደ ሃገርህ ሄደህ ህዝብህን ምራ፣ የማዝህን በስርዓት አድርግ፣ የወንድምና ወንድም ጠብ ለማንም አይበጅም አላቸው። ንጉስ ተክለኃይማኖት የተደረገላቸውን ሁሉ አስገርሟቸው አብዝተው አመሰገኑ። እምየ ምኒልክም ደስታቸውን አይተው አንተ ብትሆን የማረከኝ ምን ታደርግ ነበር አሉት። ንጉስ ተክለኃይማኖትም ማርያምን አለቅህም ነበር አሉ። ተመልከቱ የእውነትና የእምነት ሰው ማለት እንድህ ነው። ለመኖርና ለማደር ሲሉ አላስተባበሉም እውነቷን ቁጭ አደረጉ። እስኪ እንደ አባታችን ንጉስ ተክለኃይማኖት የእምነትና የእውነት ሰው እንሁን፤ አስመሳይና ሸንጋይ ከንፈር እንፀየፍ።
 
  ከንጉሱ ይቅርታንና የህዝብ አስተዳደርን የተማሩ ንጉስ:-
 እምየ ምኒልክም በአጤ ቴዎድሮስ ተማርከው ተወስደው በይቅርታ በጥበብ መይሳው ካሳ ስላሳደጋቸው እሳቸው እነ ባልቻን በይቅርታ አሳድገዋል። እነ ንጉስ ተክለኃይማኖትንና አባ ጅፋርን በይቅርታ አልፈዋል። በጥበብ አስተምረዋል። እኛም የሚያስፈልገን መሪ በይቅርታ የሚያልፍ፣ በጥበብ የሚያስተምር፣ በፍቅር የሚገዛ መሆን አለበት። አልገራም ካሉ እንደ ንጉስ ሚካኤል፣ እንደ አጤ ቴዎድሮስ ኃይልን መስበቅም ሀገርን እስከጠቀመ ድረስ ጥሩ ነው። እኛስ የአባቶቻችን ልጆች ነን የምንል የትኛው የአባቶቻችን ባህሪ  በእኛ ላይ ረቦ ይታያል??
ማስተዋልና ጥበቡን እርሱ ያድለን!
Filed in: Amharic