>
5:13 pm - Monday April 18, 1312

" የጢያራ እርግማን " (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

” የጢያራ እርግማን “

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
እየተስፋፋ ላለው የኮሮና ወረርሽኝ የአየር መንገዱ እንደ ጋኔን መክለፍለፉ ገፊ-ምክንያት ነው ። እስካሁን ሦስት ሰው ሞቷል ።መአቱ ገና እያንዣበበ ነው። ለተጠያቂነቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የድርሻቸውን እንደሚወስዱ ሳይዘነጋ ፤ የተቋቋመ የሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም እና የቦርድ ሊቀመንበር ፣ የጠቅላዩ ገራ-እጅ (የአፋሪካ ፖለቲከኛ <ቀኝ> የለውም በሚለው) አቶ አባዱላ ቀዳሚ ናቸው።
በነገራችን ላይ የአየር መንገዱ ችግር ከኮሮና በላይ ካልበረርኩ የማለት ቅብጠት ብቻ አይደለም ። ለዐመታት አስተዳደራዊ ብልሹነት መገለጫው ሆኑ መቆየቱና በዕዳ መዘፈቁም ነው። ከአውሮፕላኖቹ አብዛኛዎቹ የኪራይ እንጂ የራሱ አለ-መሆኑም ጉድ ነው ፤ ከ123ቱ አውሮፕላኖች 65ቱ በኪራይ መምጣታቸውን ሰምቻለሁ ፤ ግራ-ያጋባኝ የሸጠውን አውሮፕላን መልሶ የሚከራይበት የ”ቢዝነስ ህልዮት” ከየት እንደተቀደ አለማወቄ ነው። በርግጥ በሸጠ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደገና ራሱኑ የተከራየበት ኹነት ከሌሎች ” ዶቶች ” ጋር ሲቀጣጠል ፤ < ኮሚሽን > የለመደ እጅ መገኘቱን አይቀሬ ያደርገዋል።
በአናቱም የሠራተኞች ፍልሰት ፣ የፍትሕ እጦት ፣አልቦ-ግልፅነት ፣ የተቆጣጣሪው ባለ-ሥልጣን መስሪያ ቤት ድክመት፣የሀብት ብክነት ፣የምዝበራና መሰል ችግሮች ሥር-ሰደድ ሆነው መቀጠላቸው ነገሩ በእነ ተወልደ ብቻ እንደማይቆም ያረዳል። በሙስና ከሚታሙ ኢሕአዴጋውያን ዋንኛው አብዱላ ገመዳ ወደ አስር ዐመት ለሚጠጋ ጊዜ የቦርድ ሊቀ-መንበር ( አሁንም ጭምር) መሆናቸው ደግሞ የበሽታው < ሲፕተም> ነው ።
ዓለምን ያሰገው ወረርሽኝ ከተስፋፋ በኋላም ፣አየር መንገዱ በቫይረሱ ወደተጠቁ አገራት በመብረር ጦሰኛ መሆኑ አያከራክርም ። ሰሞኑን “የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ” ለአቬሽን ባለ ስልጣን በጻፈው ደብዳቤ ፤ በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስከሬን ወደዚህ እንዳያመጡ ለሁሉም የአየር መንገድ ኦፕሬተሮች እንዲያሳውቅ ያዘዘበት ዐውድም ብዙ ይናገራል ። መቶ ሚሊዮን ሕዝብን ለአደጋ አጋልጦ የሚያስገበገብበት ዓላማም ሰው ማጓጓዝ ይሁን ፣ ኮሮናን ማጋዝ አዳናጋሪ እንደሆነ በ”ኮርጎ” ስም ቀጥሏል።
አቶ ተወልደ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው “እኛ ብቻ አይደለንም ፤ሲንጋፖር ይበራል ፣ ብርትሺ ኤርዌይስ ይሄዳል ፣ ኤምሬት ይከንፋል” ….ያሉበትን ከንቱ ንፅፅር እንኳ “ትንኮሳ ነው ” ብለን እንለፈው ¡¡¡
Filed in: Amharic