>

"ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም! ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም!!!"  (ዶክተር መላኩ በያን) 

ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም! ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም!!!” 

 

ዶክተር መላኩ በያን 
ሳሚ ዮሴፍ
የተወለዱት ሚያዝያ 21 ቀን 1892 ዓ.ም ወሎ ክፍለ ሀገር ነው። አባታቸው ግራዝማች በያን እናታቸው ወይዘሮ ደስታ ይባላሉ። መላኩ በተወለዱ በ6 ወራቸው እናትና አባታቸው ወደ ሐረር ይዘዋቸው ሄደው ሐረር የራስ መኮንን ግቢ ውስጥ የቄስ ትምህርት እየተማሩ አደጉ።
በተወለዱ በ21 ዓመታቸው በ1913 ዓ.ም ለህክምና ትምህርት ወደ ውጭ ሀገር ሄዱ።
ዘ ማርች ኦፍ ብላክ ሜን የሚባለው ጋዜጣ መላኩ በያንን አነጋግሮ ታሪካቸውን ጽፎ ነበር።
“…እኔ ለትምህርት የመጣሁት ፍላጎቴን ለንጉሡ ገልጬ ነው፤ የምፈልገው የህክምና ትምህርት ነው፤ የህክምና ትምህርት ተምሬ ከጨረስኩ ሀገሬ ተመልሼ አንድ የህክምና ድርጅት አቋቁሜ የሀገሬን ህዝብ ለመርዳት ነው ምኞቴ ብዬ ነገሬ ነው የመጣሁት…” ብሏል።
መላኩ ለህክምና ትምህርት ወደ ህንድ ሀገር ተላኩ። ብቻቸውን አልነበሩም  ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት አብረው ነበሩ። መላኩ በህንድ ሀገር ያለው ትምህርት ስላልተስማማቸው ወደ አሜሪካ ለመሄድ አሰቡ። በተለይ አብራቸው ለትምህርት የሄደችው ሴት ልጅ መሞቷ መላኩ የህንድ ኑሮ አላስደሰታቸውም። ሁለት ወንድ ጓደኞቻቸውን ይዘው በ1914 ዓ.ም ሚያዚያ ወር በመርከብ ተሳፍረው ከህንድ ወደ አሜሪካ ተጓዙ። አሜሪካ እንደደረሱም ማሪየታ ኮሌጅ ገቡ። በ1918 ዓ.ም መላኩ የከፍተኛ ትምህርት ዲግሪያቸውን ሲያገኙ አፍሮ አሜሪካ የሚባለው ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በ1925 ባወጣው እትሙ “…በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያዊ ዲግሪ ተሰጠ…” በማለት ጽፎላቸዋል።
መላኩ በያን በ1920 ዓ.ም ኮሎምበስ ውስጥ ኦሃዩ ስቴት ዩኒቨርስቲ ገቡ። ከዚያም አንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ወደ ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው የህክምና ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ዘ ማርች ኦፍ ብላክ ሜን መላኩን ባነጋገራቸው ጊዜ መላኩ እንዲህ አሉ….
“…ሀዋርድ ዩኒቨርስቲን የመረጥኩበት ምክንያት የሀገሬን ሰዎች ለማግኘት የሚያመቸኝ በመሆኑ ነው፤ ዋንኛው ነገር ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልጅ ጋር ልንጋባ ተጫጭተን ስለነበር ያን የጋብቻ ውል ለመሰረዝና ከጥቁሯ አሜሪካዊት (ዶሬቲ ሀድሌይ) ለመጋባት የበቃሁበት መሆኑ ነው” ብለዋል።
በሰኔ ወር 1927 ዓ.ም መላኩ በያን ከሀወርድ ዩኒቨርስቲ በዶክተርነት ተመረቁ። ያ ዘመን ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተችበት ዘመን ስለነበር ዶክተር መላኩ በያን ሀገራቸውን ለመርዳት ወር ሳይሞላቸው ሐምሌ 3 ቀን ሚስታቸውን ወይዘሮ ዶሬቲንና ልጃቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ጉዞአቸውን ጀመሩ። ሐምሌ 25 ቀን አዲስ አበባ ገቡ። አዲስ አበባ እንደገቡ ለጊዜው በአሜሪካ ሚሽን ሆስፒታል ሥራ ቢጀምሩም ጦርነቱ እየተፋፋመ በመሄዱ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ሥር ተመዝግበው ወደ ኦጋዴን ዘመቱ።
የኢጣልያ ፋሺስት መንግሥት አዲስ አበባን ሲይዝ መላኩ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዱ። ከዚያም ወደ አሜሪካ በመሄድ የኢትዮጵያን በግፍ መወረር እየሰበኩ እርዳታ መለመን ጀመሩ።  በፎክላንድ ፓላስ ሁለት ሺ ሰዎች ሰብስበው መስከረም 2 ቀን 1929 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር “…ሀገራችንን የምንለቅ ሕዝቦች አይደለንም፤ ጠላቶቻችን የያዙትን መሬት ለቀው እስቲወጡ ድረስ ወታደሮቻችን ተኩስ አያቆሙም፤ ጥቀር ያሸንፋል…” በማለት የተሰበሰበውን ሕዝብ እንዴት እንደቀሰቀሱ ዘ ማርች ኦፍ ብላክ ሜን የተባለው ጋዜጣ ጽፎታል።
ፕሮፌሰር ሀሮልድ ኢስሐቅ ስለ መላኩ በያን ሲመሰክሩ ኒው ወርልድ ኦፍ ኔግሮ አሜሪካንስ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል “…በስደት ያሉት የኢትዮጵያ ንጉሥና መኳንንት ባላቸው ንቀት ምክንያት ከጥቁሮች ጋር አንነጋገርም እያሉ የመላኩን ስብከት ባያደናቅፉ ኖሩ ኢትዮጵያን ለመርዳት የተነሳው ጥቁር አሜሪካዊ ታምር በሠራ  ነበር…”
መላኩ በግብፅ፣ በጅቡቲ፣ በኬንያ፣ በሱዳንና በሌላም ቦታ ያሉትን ስደተኞች ለመርዳት “ምኒልክ ክበብ” ስለሚባለው ድርጅታቸው፣ የኢትዮጵያ ድምፅ (Voice of Ethiopia) ስለተባለው ጋዜጣቸው፣ በእያንዳንዱ ቤት እየዞሩ ስለሚያደርጉት ልመና፣ ዩናይትድ ኤድ ፎር ኢትዮጵያ በማለት ስላቋቋሙት ድርጅት፣ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የኢትዮጵያን ምስል አሳትመው ስለሸጧቸው ቴምብሮች፣ ሁሉ ዘርዝሬ ማውራት አልችልም።
መላኩ በያን እያሳተሙ ስለሚሸጧቸው ቴምብሮች አምስተርዳም ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ወኪል ጠይቋቸው ሲመልሱ “…ነፃነት ያላቸው ስለባርነት አያስቡም፤ ሆዳቸው የሞላም ስለረሃብ አይነጋገሩም…” ብለው መልስ መስጠታቸውን እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2 ቀን 1937 ዓ.ም ባወጣው እትሙ ገልጾታል። ዶክተር መላኩ በያን ቀላል ሰው አልነበሩም በላቲን አሜሪካና በዌስት ኢንዲስ የማህበሩን 22 ቅርንጫፎች አቋቁመው ስለ ኢትዮጵያ የለፉ ወጣት ነበሩ። በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ የነበሩ አባሎች በሺ የሚቆጠሩ ነበሩ።
ዶክተር መላኩ በነሐሴ ወር 1931 ዓ.ም ታመሙ። ነሐሴ ሲያልቅ ተሻላቸውና ያንኑ የእርዳታ ሥራቸውን ጀመሩ። እንደገና በመጋቢት ወር 1932 ዓ.ም ቤት ለቤት እየዞሩ እርዳታ ሲለምኑ በኒሞኒያ በሽታ ተለከፉ። በጠና ስለታመሙ ሮክላንድ ‘ስቴት ሆስፒታል ገቡ። ሚያዚያ 26 ቀን 1932 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በአሜሪካም ሆነ በሌላ ሀገር የሚገኙ ታላላቅ ጋዜጦች የመላኩን መሞት በታላቅ ሀዘን ጻፉ። ያቋቋሙት ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋዜጣም እ.ኤ.አ. ሜይ 11/1940 በወጣው ዕትሙ “#ወጣቱና #ታላቁ #መሪ #ሞተ” በሚል ርዕስ ጻፈላቸው።
ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያ በአርባ ዓመት ዕድሜያቸው ተቀጩ።
የኢትዮጵያና የኢጣልያ #ጦርነት
ጳውሎስ ኞኞ
Filed in: Amharic