>

ኮሮና (ወረርሽኝ) የዘመናችን ክስተት!!!  (ዲ/ን ሕሊና በለጠ)

ኮሮና (ወረርሽኝ) የዘመናችን ክስተት!!! 

 

ዲ/ን ሕሊና በለጠ
የኮሮና በ “severe acute respiratory syndrome corona virus- 2” የሚከሠት በሽታ ነው። በዓለም ላይ የብዙኃንን ሕይወት እየቀጠፈ ያለ አደገኛ ወረርሽኝ ነው፡፡ በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሠተው በዚሁ ዓመት በታኅሣሥ ወር ሁቤይ በተባለች የቻይና ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሁዋን ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በሽታው በጣም በፍጥነት የሚዛመት እንደ መሆኑ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ከ200 በላይ ወደ ሆኑ አገራት ተዛምቶ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎችንም ገድሏል፡፡ በአገራችንም የተጠቂዎች ቁጥር 65 መድረሱ ተነግሯል፡፡ ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው የተዛመተ ስለሆነ በሳይንሱ Zoonotic ተብሎ ይጠራል፡፡ ወደ ሰው የተዛመተውም ከሌሊት ወፍና ፓንጎሊን ከተባለ እንስሳ እንደ ሆነ ይታመናል፡፡
ኮሮና ቫይረሶች ተብለው በዓለም ላይ የሚታወቁት ተሕዋስያን በአጥቢ እንስሳትና በወፎች ላይ በሽታን የሚያመጡና የሚገድሉ ናቸው፡፡ የመተንፈሻ አካል ልክፍትን የሚያስከትሉ ሲሆኑ ቀላል ከሆኑት መካከል ጉንፋንን አደገኛ ከሆኑት መካከል ደግሞ በፈረንጆቹ በ2003 ዓ.ም. አካባቢ ከዚሁ ከቻይና የተነሣው ሳርስ ይጠቀሳሉ፡፡ የኮሮና ቫይረሶች ለመጀመሪያ ጊዜ በተመራማሪዎች የታወቁት ከ90 ዓመታት አካባቢ በፊት ሲሆን፣ ሰውን የሚያጠቁት በምርምር የተደረሰባቸው በ1950ዎቹ እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ የኮሮና ቫይረሶች ክትባትም ሆነ መድኃኒት የላቸውም፡፡ በሕክምና የሚመከረው ብቸኛ አማራጭ አስቀድሞ መከላከል እና የሰውነትን የመከላከል አቅም ማዳበር ነው፡፡
1.መቅሰፍት፣ ረሀብ፣ ቸነፈርና የመሳሰሉት መነሻቸው ምንድን ነው?
ባለፉት መቶ ዓመታት ዓለማችን እንዲህ ዓይነት አደገኛ ወረርሽኝ ባይገጥማትም፡ ከመቶ ዓመት በፊት ተከሥቶ የነበረውን የስፓኒሽ ፍሉ በሽታን ማንሣት እንችላለን፡፡ ይህ ወረርሽኝ ከ17 ሚሊዮን እስከ 50 ሚሊዮን ሰዎችን እንደ ገደለ ይታመናል፡፡ ይህም በዘመኑ 2 ቢሊዮን ከማይሞላው የዓለም ሕዝብ ከ1% እስከ 3% የሚደርስ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም የሞተውን 100 ሚሊዮን ያደርሱታል፡፡ ከዚህኛው ወረርሽኝም በፊት ከ20 በላይ ወረርሽኞች ዓለማችንን አስጨንቀዋታል፡፡ ብዙ ሰውንም ጨርሰዋል፡፡ ቢጫ ወባ፣ ፈንጣጣ፣ ፖሊዮ በቅርብ ጊዜ ከተከሠቱትም ኤች.አይ.ቪ ኤድስንና ኢቦላንም ማንሣት እንችላለን፡፡ ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኝ ያልሆኑ ነገር ግን የተወሰነ ቦታን በወረርሽኝነት ያጠቁትንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተከሥተው በተደጋጋሚ ስማቸውን በሚዲያ የምንሰማቸውን ዚካ ቫይረስን፣ ስዋይን ፍሉና ሳርስንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
የቅዱስ ቆጵርያኖስ ወረርሽኝ የሚባል ወረርሽኝም ነበር፡፡ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የካርቴጅ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ቆጵርያኖስ “On the Plague” በተሰኘው ጽሑፉ የበሽታውን አስከፊነት ገልጾ ነበር፡፡ ስለወረርሽኝ የሚያጠኑ ባለሙያዎች በዘመኑ በሮም ግዛት ውስጥ በቀን እስከ 5 ሺሕ ሰው በበሽታ ይሞት እንደ ነበር ገልጸዋል፡፡ ወረርሽኙ በአባታችን በቅዱስ ቆጵርያኖስ የተሰየመው ስለ በሽታው ብዙ መረጃ ማግኘት የተቻለው ከእርሱ ጽሑፍ በመሆኑ ይመስላል፡፡ ይህም አባቶቻችን ስለሰው ሕይወት የሚገዳቸው መሆኑን ያሳያል፡፡
በጊዜው የዓለምን ዐሥር በመቶ ሕዝብ የጨረሰው የዮስጢኖሳውያን ወረርሽኝ የሚባልም ነበር፡፡ ዮስጢኖስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቢዛንታይን ንጉሥ የነበረና በጥንቷ ቍስጥንጥንያ በአሁኗ ኢስታንቡል ከተማ ባሠራው የቅድስት ሶፊያ (ሐጊያ ሶፊያ) ቤተ ክርስቲያን የሚታወቅ ነው፡፡ እርሱም ራሱ በወረርሽኙ ተጠቅቶ ድኗል፡፡
እግዚአብሔር በግብፃያን መቅሰፍት አምጥቶባቸው እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የምናገኘው ነው፡፡ የመቅሰፍቱ ምክንያትም የግብፃውያን እንቢተኝነት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ወረርሽኝ መከሠት መነሻው እንደ ግብፃውያኑ እምቢተኛ ሆነን ወይም እንደ ኢዮብ የፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ በጋራ ለመጣብን መከራ መፍትሔው በጋራ ንስሐ መግባት ነው፡፡ ብሔራዊ ንስሐ፡፡ በዘመናችን የሚፈጸመው ኃጢአት በኤልያስ ዘመን ከነበረውም፣ ከፈርዖንም፣ ከሰብኣ ነነዌም ቢብስ እንጂ አያንሥም፡፡ ችግሩ የተወገደውም ሕዝቡ ንስሐ ስለገባ ነው፡፡
የማይወድቁና የማይሰበሩ የሚመስሉን እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ ልዕለ ኃያላን መሥራት የማችሉት እንደሌለ እናስብ ነበር፡፡ ትዕቢታችን እንደ ባቢሎን ሰዎች ቢሆንም የሰው አቅም እስከ ምን ድረስ እንደሆነ እያሳየን ነው፡፡ አሁን “ኃያላን እንዴት ወደቁ” የምንልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ (፪.ሳሙ.፩፣፲፱)፡፡ እንዴት እንደ ወደቁ ባናውቅም የማይወድቁ የመሰሉት እንደሚወድቁ እያየን ነው፡፡
2.ወረርሽኙ ከእግዚአብሔር የታዘዘ እንደሆነ ማሰብ
ወረርሽኝ ከእግዚአብሔር ሊታዘዝ ይችላል፡፡ አዳም በራሱ ላይ ሞትን እንዳመጣ ሁሉ እኛም የጥፋት እጃችንን ወደ ቫይረሱ ዘርግተን ሊሆን ይችላል፡፡ በኦሪት እንዳንበላቸው የታዘዙ እንስሳት አሉ፡፡ እንስሳቱ እንዳይበሉ መጽሐፍ ቅዱስ መከልከሉ ከጤና አንጻር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ እንዳይበሉ የታዘዙትን እንስሳት የሰው ልጅ ቢበላ ለተላላፊ በሽታ እንደሚጋለጥ ሳይንስም ደርሶበታል፡፡ ስለዚህ እጃችንን አትብሉ ወደ ተባልነው ዕፀ በለስ ዘርግተን በራሳችን ላይ ያመጣነው ሞት ሊሆንም ይችላል፡፡
3.የበሽታው ስርጭትና ጉዳት ከሞያም ከሃይማኖትም አንጻር
በሽታው በፍጥነት የሚሰራጭ አደገኛ በሽታ ነው፡፡ የሀብት፣ የሃይማኖት፣ የጾታ፣ የዕድሜ ልዩነት አይገድበውም፡፡ በሽታው “ኦርቶዶክሳውያንን አይነካም” የሚባል አይደለም፡፡ በግብር ኦርቶዶክሳዊ ከሆንን የማይነካን ወደ ሲዖል መውረድ እንጂ አለመታመም አይደለም፡፡ በሥጋ በሽታ የሞቱ ገዳማውያን አሉ፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የፈለገ ገድለ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስን ማንበብ ይችላል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምንም ማንሣት እንችላለን፡፡ አረጋዊነቱ ድካም ሳይፈጥርበት በ70 ዓመቱ ከገዳም ወጥቶ በኤዴሳ ተከሥቶ በነበረው በሽታና በርሃብ የተጠቁትን ሲረዳ ጤናው ተቃውሶ ማረፉን እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በሽታው ማንንም መርጦ የማይተው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በርግጥ በሃይማኖት የምንመላለሰው በዋናነት ከሥጋ በሽታ ለመጠበቅ ሳይሆን ከዘለዓለም ሞት ለመዳን ነው፡፡
ይቆየን
Filed in: Amharic