>

የታጋቹ ማስታወሻ ( በእውቀቱ ስዩም)

የታጋቹ ማስታወሻ

በእውቀቱ ስዩም
ዛሬ በጠዋት ተነሳሁ፤ አጠር ያለ ስፖርት ሰራሁ፤   ሳሎኔን አስር ጊዜ ዞርኩት፤  ከዚያ  ሳሎኑ በተራው   ዞረብኝ፤ ብዙ አልቆየሁም፤ በቁሜ ወደቅሁ፤ ከመድርደርያ ላይ እንደወደቀ  የመርቲ ጣሳ እየተንከባለልሁ አራት ደረጃ ወደ ታች !  እምገርም ነው!  እስከዛሬ አይቸው የማላውቀው ቤዝመንት አገኘሁ!   ቤቱ ባለ ቤዝመንት እንደሆነ አከራዩ  ለምን  አልነገሩኝም?
 ተመስጌን ነው! የወደቅሁት ከቤቴ ውጭ ቢሆን  ኖሮ አልቆልኝ ነበር፤ ይሄማ  አናቱ ላይ  ፊጥ ብሎበታል  ይሉና በአንቡላንስ አፋፍሰው  ይወስዱኝ ነበር! ከዚያ መርምረው ሲያጡብኝ “ ለዛሬ ኔጌቲቭ ነህ !  ይሁን እንጂ ቅድም አቅፎ የጫነህ   የአምቡላንሱ ሾፌር ፖዘቲቭ መሆኑን አሁን ስለደረስንበት ከሳምንት በሁዋላ ተመልስህ ና”   ሊሉኝ ይችላሉ ፡፡
 በማስቀጠል፤ መስኮቴ ላይ ሆኘ ፤በጦር ሜዳ መነፅር አካባቢውን ቃኘሁት ፤ ፖሊስ የለም! ምፅ!  ፖሊስ ራሱ ከቤት መስራት ጀመረ ማለት ነው! ያማሪካ ፖሊስ  ከቤት ሲሰራ አስቡት!
 ዜጋ- “ሄሎ ኦፊሰር ?
ፖሊስ- አቤት”
ዜጋ   – ሌባ  የቤቴን  ሰብሮ ገብቱዋል
ፖሊስ – you kidding me?” እየቀለድህ መሆን አለበት
 ዜጋ-  ከምሬ ነው
 ፖሊስ “-  እስቲ አገናኘኝ
ከቤቴ ወጣሁ እና ፓርኩ ላይ  በሚገኘው አግዳሚ ወንበር ቁጭ አልኩ!  የተራቡ ርግቦች እግሬ ስር ተሰበሰቡ!  ትናንት  ከቁርስ እስከ እራት ድረስ  ቅርፁን እየቀያየርሁ   የበላሁትን  በሶ  በተነንኩላቸው፤ በሶው  ኤክስፓየርዴቱ እንዳለፈ ያወቅሁት ሁለቱ ወፎች እዛው አረፋ ደፍቀው ሲሞቱ ሳይ  ነው!   ወገን!  እና ጊዜው ያለፈበት በሶ በልቼ ያልሞትኩት ሰውየ   የተበየደ ፍሬሽ  ጉንፋን   ይገለኛል ተብሎ ይታሰባል? እሱስ ድብን አድርጎ ሊገለኝ ይችላል! ብቻ   የምችለውን ያክል ተጠንቅቄና አስጠንቅቄ ከሞትኩም አይደብረኝም!  በሳልና በሳቅ መሀል  ለመሞት ዝግጁ ነኝ፤
 ድንገት በየነ ናፈቀኝ!   ልደውልለት ስልኬን ካነሳሁ  በሁዋላ መልሼ ተውኩት ፤ በዩማ (በየነ ሲቆላመጥ ነው)   ከሶስት ቀን በፊት ስልኩ ከእጁ አምልጦ  ተፈጥፍጦበታል ፤ በዚህ ዘመን ስልክህ ከወደቀ እጢህ ወደቀ ማለት ነው፤ አንደ ወትሮው ፤ ሞባይል ቤት ሄደህ ማሳከም  አትችልም፤ በዚህ ብቸኝነት ላይ ስልክ ጎድሎበት አስበው! አስቢው! ስልኩ እንዴት እንደ ተፈጠፈጠበት  በሚቀጥለው ክፍል እፅፋለሁ  በዚህ ሳቢያ የበየነ አመል ከፋ !
ባለፈው  በሜሴንጀር ደወልኩለት
“ ምን ፈለግህ? “ ብሎ አንባረቀብኝ!
“ ትርፍ ማስክ ካለህ  እንድትልክልኝ ፈልጌ ነበር” አልኩት፤
“ ያንተን ፊት ማስክ አይመክተውም! መለስተኛ ድንኩዋን ሰፍተህ ጣል ብታረግበት ይሻልሃል”
በጣም ነቀልኩ! ለእልኩ ብየ፤  ከንፁህ አንሶላና ከሽራ ጫማ ማሰርያ የተደቀለ  ቆንጆ ማስክ ሰርቼ ለብሼ  ሰልፊ ተነስቼ ላክሁለት፤
ፎቶየን አይቶት ሲያበቃ እንዲህ እሚል ምላሹን ሰደደልኝ፤
“  በስመአብ!  አላሙዲ አጥሮ የዘነጋውን መሬት መስለሀል  ! ደሞ ያምርብሃል!   ወረርሽኙ ከተወገደ በሁዋላ እንኩዋ እንዳታወልቀው
ፓርኩ ውስጥ ያለው አየር  በጣም ንፁህ ነው! የመኪና ፈስ የኢንዱስትሪ ግሳት አልበከለውም!  ይሄ ንፁህ አየር ተመልሼ ላላገኘው እችላለሁ ! ለምንም ለምንም ብየ  አንድ ጀሪካን ቀድቼ  ወደ ቤቴ ገባሁ!
በቀጣዩ ቀን “hi ”
  የሚል መልክት ስልኩ ውስጥ ገባ! ገረመው! ካራት ወር በፊት ለላከላት ሰላምታ ዛሬ ምላሽ መስጠቱዋ ነው  ፤  መልስ ትሰጠኛለች ብሎ ጠብቆ አያውቅም ፤ ዝነኛ ተዋናይት እና  በተምሳሌትነት የታወቀች ሴት ናት ፤  እንደሱ ላለ  ሰው ጊዜ   አልነበራትም ! ዛሬ ግን ምላሽ ሲያገኝ ገረመው! ግን  ብዙ ሊገርመው አይገባም! ቀሳ ወጥታለች! ውሎዋ ከስልኩዋ ጋር ነው!  ለከረሙ መልክቶች ሁሉ በፅሞና ምላሽ የምትሰጥበት ጊዜ አላት: :
“  እንዴት እንደምወድሽኮ” የሚል ምላሽ ሰደደላት!
“ አመሰግናለሁ”
“ የህይወት ዘመን ፎንቃየ ነሽ ብልሽ አታምኚኝም”
“  አይ እንግዲህ ! ”
 “ የሚገርምሽ  ከመደወልሽ  ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ፤ ፕሮፋይ ላይ ያለውን ፎቶሽን   እያየሁ  ስመታ ነበር፤”
“ ምንድነው እምትመታው?
“  ከበሮ!”
“  ተው ባክህ!”
“ ቁመናየን  ይንሳኝ”
ትንሽ ሲያወጉ ከቁዩ በሁዋላ ፤
“ ያው እንደምታቂው ሞት ከቦናል !  እኔ  ከፋም ለማም አብይም እስካሁን ኖርያለሁ  !  ከዚህ በሁዋላ በህይወቴ የምጠይቀው አንድ ነገር ነው !  ጡትሽን! ጡትሽን ፎቶ አንስተሽ ላኪልኝ! “
 የላከውን አይታ ከድፍረት ቆጥራ  asshole (ብሽቅ!) ብላ ብሎክ ታረገኛለች ብሎ  ጠብቆ ነበር፤
“  ምን ይጠቅምካል ?”  የሚል መልስ ላከችለት!
“  ለመጨረሻ ጊዜ ደስ ብሎኝ ልሙት !    ከተረፍኩ ደግሞ  ባንች ሰበብ እንደተረፍኩ እቆጥረዋለሁ”
“አልገባኝም”
“  እውነቱን ንገረኝ ካልሽኝ  በጣም ደብሮኛል!  መሞት ፈርቼ እንዳይመስልሽ!  ህይወቴንና ዶላሬን ለሀገሬ ስቆጥብ የኖርኩ ሰው ነኝ!  አገሬ ገብቼ፤ ህዳሴው ግድብን ከግብፅ ወረራ እየተከላከልኩ  ከመሰዋት ያለፈ አላማ ኖሮኝ አያውቅም! በቻይና ቫይረስ ተነድፌ ፤ ባሜሪካ ሆስፒታል ውስጥ መሞቴን ግን ልቀበለው እማልችለው  አሰቃቂ ቅዤት ነው   !  ደሞኮ እንዳገራችን ወግ በፍትሃት በፀሎትና በሙሾ መሸኘት በስንት ጣሙ  !  ከሞትኩ፤ ብድግ አድርገው  የቄራ ፍሪጅ የተገጠመለት ሲኖትራክ  ውስጥ ይወረውሩኛል !
  “ ያ እንዳይሆን በተቻለኝ መጠን   አጥብቄ እጠነቀቃለሁ! ቤት ውስጥ ሳይቀር ማስክ አደርጋለሁ፤  ፈረንጅ ስለማላምን ራሴ የሰራሁት ማስክ ነው ነው እማደርግ !   ማስኬ ባለሶስት ገበር ነው!  የፊትና የሁዋላ ኪስ ሳይቀር አለው፤ በርግጥ፤ ወፍራምና ክብ ፊቴ  ለማስክ አልተፈጠረም!  ቅድም በመስታውት ራሴን  ስመለከት አዘንሁ!  … ዳንቴል የለበሰ ግማሽ ድፎ   መስያለሁ ፤ ደሞ  ስተኛ ራሱ አላወልቀውም! ታፍኜ እንዳልሞት  ፀልይልኝ”
“ የኔ ጡት መላክ ከዚህ ሁሉ ጋር ያለው ግኑኝነት አልገባኝም”  አለቺው፤
 “ ጡትሽን ብትኪልኝ  በድብርትና በትካዜ ሳቢያ  ስራ ያቆሙት ህዋሳቴ ይነቃቃሉ፤ ተነቃቅተው  የተፈጥሮ ሞርታርና ባዙቃ ያመርታሉ፤  ኮሮናን ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ይደመስሱታል፤ በመጣበት እግሩ ይመልሱታል”
ፀጥ ብላ ቆየች፤
ከዚያ
…typing typing
ዝም!
ከዚያ
…uploading  picture
ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ጠበቀ!
ወድያው የስልኩ ስክሪን ወገግ አለ!
ጡት!
 ማተብ የሚያነጥር ጡት!
 እንኩዋን በዳበሳ፤ በመብረቅ የማያቀል-ጡት
ጡት!
ስልኩ ከጣቶቹ ላይ አመለጠ! ከደረጃው እየነጠረ ወርዶ ከታች ባለው የድንጊያ ንጣፍ ላይ ተኛ ! ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ስልክ የነበረው አሁን ዝሆን የረገጠው የሰርዲን ጣሳ  መስሎ ተጋደመ ! በየነ  በድንጋጤ ውሃ ሆኖ፤  የስልኩን  ስክሪን   ገልብጦ ተመለከተው ! እውር ሸረሪት ያደራው  ድር መስሎ ነበር!
Filed in: Amharic