>
5:13 pm - Monday April 20, 6685

ህዝቡ መንግስቴ በሚለው ወራሪ የተላከበትን ጦር ይከላከል ወይስ የሳምባ ቆልፍ ወረርሽኝን??? (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

ህዝቡ መንግስቴ በሚለው ወራሪ የተላከበትን ጦር ይከላከል ወይስ የሳምባ ቆልፍ ወረርሽኝን???

ቴዎድሮስ ሀይለማርያም
* ….በላሊበላ ህዝብ ላይ የበድኑ ብአዴን ጋሻ ጃግሬዎች ከመከላከያው ጋር በመጣመር “ፋኖ ናችሁ ፣ ትደግፏቸዋላችሁ” በሚል ሰንካላ ምክንያት ባካሄዱት ወረራ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉና ከአስራ ሁለት በላይ ሰዎች በጽኑ እንደቆሰሉ ታውቋል!!!
 
      በሀገራችን ላይ የተጋረጠውን  ተግዳሮት በጋራ ተሰልፈን ካልተፋለምነው በጋራ እንደምንጠፋ አይጠረጠርም።  ነገር ግን አንዱ ቅን ሌላው ሴረኛ ፣ አንዱ ትጉህ ሌላው ዳተኛ ፣ አንዱ ሀገራዊ ሌላው ቡድንተኛ ከሆነ ልፋታችን ፋይዳ አይኖረውም።
      እውነት እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ወቅት የኮቪድ—19 ወረርሽኝ ለሚያስከትለው ብሄራዊ የህልውና  አደጋ ዋነኛው እንቅፋትና  ተጠያቂ  ራሱ የኢትዮጵያ መንግስት ነው።
    ይህ አገዛዝ የወያኔ ውላጅ እንደመሆኑ ትልቁ በሽታው የሀገር አስተዳደር ከባድ ምርጫዎችን  በአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ መወሰኑ ነው። በዚህ ላይ በተፈጥሮ የተጣቡት አቅመ ቢስነትና ውስጣዊ ሰላም  እጦት ይደመራሉ።
     ገና ከጅምሩ የሳምባ ቆልፍ በሽታ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ዛሬም ድረስ ከባህር ማዶ በየእለቱ  የሚጋዘው  በአብይ መንግስት ዳተኝነት ነው። ለዚህ አየር መንገድ አንድ መላ ዘይዱ ሲባል አብይ ከነሚኒስትሮቻቸው ሰላሳ ቧልት ሲቦልቱ መክረማቸውን ዋጋ ልንከፍልበት ነው።
   አሜሪካ ባለፈው ፌብርዋሪ መጨረሻ ላይ 54 ህመምተኞች ብቻ ነበሯት። ዛሬ ይህንን  ሁሉ ርብርብ እያደረገች በቀን 2 ሺህ ገደማ ዜጎች እየተቀጠፉባት ነው። የእኛስ እጣ ፋንታ ምንድነው? አሁን በሳምንታት እድሜ  52 ላይ ደርሰናል። የዛሬ ወር   የት እንደምንደርስ ገምቱ።
    አሁን የእኛ ችግር አፍጥጦና አግጥጦ  በምንም ተአምር የማናመልጠው ሆኗል። የአብይ አገዛዝ ወረርሽኙን ቀድሞ ለመከላከል ያፌዘባትና  የዘገየባት እያንዳንዷ  ቀን የሺህዎች ዜጎችን ህይወት ማስከፈሏ  አጉል ሟርት አይደለም። የራሱ የጤና ጥበቃ ግምት  ነው።
    በሌላ አነጋገር እንደዛ የሀገር ዋልታችንን አትንኩብን የተባለው የአየር መንገዱ ገቢ በሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን  መከራና ህይወት ዋጋ ሊመነዘር ነው። የምንጊዜም አጋሮቻችን እየተባሉ የተቆላመጡት ቻይናውያኑ  ዢም ሆኑ ጃክ ማ የኢትዮጵያን ህዝብ ከተደቀነበት መቅሰፍት  ሊያድኑት አይችሉም።
   እጅግ የሚያስፈራው ነገር ደግሞ ዛሬም  መንግስታችን  ያንዣበበውን አደጋ ልክ አልተረዳውም ወይም ከልብ አላመነበትም።  ዛሬም ለሚጠፋው የዜጎች ህይወትና  ላንዣበበው  መከራ ሳይሆን አየር መንገድ ላጣው ዶላር የሚጨነቅ መሆኑ  ያሳቅቃል።
    የአብይ አገዛዝ አሁንም በህዝብ ሰቆቃ የፖለቲካ ትርፍ ላይ መቋመጡ እዚህም እዚያም እየታየ ነው። ሀገሪቱን በአንድ ልብና መንፈስ አስተባብሮ ለመምራት አልተዘጋጀም። ወቅቱ የሚጠይቀውን ትክለ ስብእና መፍጠር  አልቻለም።
እንርዳህ ፣ እንተባበርና ሀገር እናድን የሚለውን በቅንነት ለመቀበል ክፉኛ  እየተናነቀው ነው።
   መንግስት እያንዳንዷን ሰአት በባለሞያ የታገዘና ትርጉም ያለው ስራ ከመስራት ይልቅ  ባልተጠና የስሜት ወፈፍታና አጉል  ድራማ ተጠምዷል። በማህበረሰቡ ምሰሶ እሴቶችና ስርአታት ላይ አስፈሪ ጥራዝ ነጠቅ ሙከራዎችን ማድረግ መርጧል። በየአቅጣጫው ሀገር አንቅሮ  የተፋቸው ሚኒስትሮችን እያሰማራ ህዝብ አስተምሩልኝ የሚል ቧልት ይዟል። ኩንታል የመሸከም ውድድር ያደርጋል።
    መንግስት ግራ ገብቶት ሀገር ግራ እያጋባ ነው። ተሸብሮ እያሸበረን ነው።  ትምህርትን ፣  ስራን ከዘጋና በአንዳንድ ከተሞች የህዝብ እንቅስቃሴ ጭምር ከገደበ በኋላ በጎን ካድሬ ልኮ  ህዝብ በግዳጅ ይሰበስባል። ሰራዊቱን በካምፕና በመደብ አጉሮ የኮሮና ኢላማ እንዲሆን መተው ሳይበቃው  “ወንጀለኛ” ለማደን እያለ በየክልሉ ለደም መፋሰስ ያሰማራል።  በትናንትናው እለት እንኳ በላሊበላ ህዝብ ላይ የበድኑ ብአዴን ጋሻ ጃግሬዎች ከመከላከያው ጋር በመጣመር “ፋኖ ናችሁ ፣ ትደግፏቸዋላችሁ” በሚል ሰንካላ ምክንያት ባካሄዱት ወረራ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉና ከአስራ ሁለት በላይ ሰዎች በጽኑ እንደቆሰሉ ታውቋል።
    ልብ ያለው መራሩን እውነታ ልብ ይበል! ብልፅግና የተያያዘው  የህዝብን ትኩረት የሚከፋፍልና የህልውና ፍልሚያውን የሚያመክን ፣ የተምታታና ሴረኛ  ድርጊት ነው።  መንግስት በአስቸኳይ ከችግር ፈጣሪነት ወደ መፍትሄ አካልነት ካልመጣ የሀገራችንና የህዝባችን ህልውና ፅኑ አደጋ ላይ ነው። ፈጣሪ በኃይለ መለኮቱ ይታደገን!
Filed in: Amharic