>

11 ጋዜጠኞች ከሀገር ተሰደዱ

Exile Journalists in Kenya 1

 (ኢ.ኤም.ኤፍ) በቅርቡ በአምስት ነጻ ፕሬሶች ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር በተያያዘ እስካሁን አስራ አንድ ጋዜጠኞች ለስደት መብቃታቸው ታወቀ። አቃቤ ህጉ በአዲስ ጉዳይ፣ ሎሚ፣ ጃኖ፣ አፍሮ ታይምስ እና እንቁ አዘጋጆች ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው። ጋዜጠኞችን በመክሰስ እና በማሰር በአሸባሪነት ሽፋን እስከ አስራ ስድስት አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት መፍረድን በነእስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርእዮት አለሙ ላይ የታየ እውነት ነው። አሁንም ሌሎች ጋዜጦች ላይ የሚደረገው ጫና እየበረታ እንጂ እየቀነሰ ባለመሄዱ ነው እነዚህ ጋዜጠኞች አገር ለቀው ለመሰደድ የበቁት።

እስካሁን ስማቸው የደረሰን ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው። 1-እንዳልካቸው ተስፋዬ (የአዲስ ጉዳይ መጽሄት አሳታሚ) 2-ኢብራሂም ሻፊ (የአዲስ ጉዳይ ምክትል ዋና አዘጋጅ) 3-እንዳለ ተሼ (የአዲስ ጉዳይ ከፍተኛ አዘጋጅ) 4-ሃብታሙ ስዩም (የአዲስ ጉዳይ አዘጋጅና አምደኛ) 5-ቶማስ አያሌው (የአፍሮ ታይምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 6-አስናቀ ልባዊ (የጃኖ መጽሄት አሳታሚ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 7-ግዛው ታዬ (የሎሚ መጽሄት አሳታሚ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር) 8-ዳንኤል ድርሻ (የሎሚ መጽሄት ሚዲያ ዳይሬክተር) 9 ሰናይ አባተ ቸርነት (የሎሚ መጽሄት ዋና አዘጋጅ) 10-አቦነሽ አበራ (የሎሚ መጽሄት ከፍተኛ ሪፖርተር) 11-ሰብለወንጌል መከተ (የሎሚ መጽሄት ከፍተኛ ሪፖርተር ናቸው) ከአምስቱ ተከሳሽ ጋዜጠኞች መካከል እስከአሁን ያልተሰደዱት የእንቁ መጽሄት አዘጋጆች ሲሆኑ፤ የመጽሄቱ አሳታሚ አለማየሁ ማህተመወርቅ አሁንም አገር ቤት ነው።

Abonesh-abera2<<Abonesh-aberaፎቶ ይመልከቱ) ከተሰደዱት ጋዜጠኞች መካከል በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ቃል የሰጠችው አቦነሽ አበራ እንዲህ ብላን ነበር። (በነገራችሁ ላይ አቦነሽ አበራ የኢትኦጵ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረች፤ ከዚያም በ1997 ከመንገድ ተይዛ ተደብድባ እና ጽጉሯን ላጭተው  ያሰሯት ሲሆን፤ በተለይም የኢሳት ጋዜጠኛ የሆነው ሲሳይ አጌና እህት በመሆኗ ምክንያት ጫና በዝቶባት እንደነበረ እንዲህ በማለት ነበር የገለጸችው። “ከዚህ በፊት የሆነውን ታውቃለህ። ያን ግዜ ጭንቅላቴ ላይ ባደረሱብኝ ድብደባ ምክንያት አሁንም ድረስ አልፎ አልፎ በራስ ምታት ሕመም እሰቃያለሁ።በሎሚ መጽሄት ላይ የተደረገው ክስ ምክንያት ብታሰር እንደገና የሚፈቱኝ አይነት አይደሉም። ታስሬ መጸጸት ስለማልፈልግ ነው ከአገር ለመውጣት የወሰንኩት። በተለይም እንደሚታወቀው ታላቅ ወንድሜ ሲሳይ አጌና ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ጋዜጠኛ ሆኖ ስለሚሰራ፤ ከዚህ በኋላ ካሰሩኝ ብዙ ሊያንገላቱኝ ይችላሉ።” በማለት ከገለጸችልን ከሁለት ቀናት በኋላ ነው አገር ለቅቃ የወጣችው። አሁን በነዚህ ጋዜጠኞች ላይ ክስ ተመስርቶ ከአገር ከመውጣታቸው በፊት፤ ባለፈው ወር ሐምሌ ሰባት ቀን የደህንነት ኃይሎች ወደ ቢሯቸው በመምጣት ቢሮውን እንዳሸጉት ይታወሳል። በወቅቱ ስለተፈጠረው ነገር የመጽሄቱ ዋና አዘጋጅ ሰናይ አባተ ያስተላለፈውን መልእክት በዚህ አጋጣሚ መግለጹ አስፈላጊ ስለሆነ እናካፍላችሁ።

ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ከመንግስት በተላኩ ኃይሎች የ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ቢሮ ‹‹ያለ ንግድ ፍቃድ›› በሚል ሠበብ ታሸገ፡፡ እነዚህ ከየትኛው ወገን እንደተላኩ ያልታወቁት ኃይሎች በቢሮ ውስጥ የነበሩትን የሂሳብ ሠነዶች ‹‹ይዘን እንሄዳለን፣ አትሄዱም›› በሚል በተፈጠረው እሰጥ አገባ ምክንያት ስልክ ደውለው ቁጥራቸው ከ20 ያላነሱ የታጠቁ የፌደራል ኃይሎችን በመጥራት እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶችና ወረቀቶችን ጨምሮ እንዳናወጣ በመከልከልና በማስፈራራት አስቀድመው ታዘው ይዘውት የመጡት ወረቀት “ያልታደሰ ንግድ ፍቃድ” የሚል ቢሆንም፣ ንግድ ፍቃዱ የታደሰበትን ማረጋገጫ ሲመለከቱ ደግሞ ፊት ለፊታችን ወረቀቱን በመሠረዝ “ያለ ንግድ ፍቃድ” በሚል ጽፈው አሽገውታል፡፡ በወቅቱ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ለንባብ የምትበቃው ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ወደ ማተሚያ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳለች ይህ ችግር መፈጠሩ በሎሚ አባላቶች ላይ ግርታ ቢፈጥርም፣ በተወሰደው ሕገ-ወጥ እርምጃ ሳንደናገጥ ማተሚያ ቤት ከምንገባበት አንድ ቀን ዘግይተንም ቢሆን በተከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ማተሚያ ቤት ልናስገባ ችለናል፡፡ በወቅቱም ቢሮአችን እንደሚታሸግ ለምን አስቀድማችሁ በደብዳቤም ሆነ በስልክ አላሳወቃችሁንም ቢባሉም ‹‹የእናንተ ስፔሻል ኬዝ ነው፤ እኛ ከላይ ታዘን ነው›› የሚል ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ …እነዚሁ ኃይሎች ከመጀመሪያው ቀን በተለየ ሁኔታ በበነጋታው ተደራጅተው በመምጣት “ሠነዶችን እንፈልጋለን” በሚል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፌደራል ኃይሎች የታገዘ የ5 ሠዓታት ፍተሻ (ከብርበራ አይተናነስም) ካካሄዱ በኋላ በቢሮ ውስጥ የሚገኙትን የሂሳብ ሠነዶች በሙሉ ሰብስበው ወስደዋል፡፡ ሆኖም ግን የምንፈልገው የሂሳብ ሠነዶችን ይበሉ እንጂ፣ በቢሮው ውስጥ የሚገኙትን በተለያዩ ጊዜ የታተሙ የሎሚ መጽሔቶች፣ የአፍሮ ታይምስ ጋዜጦችና በእጅ ጽሁፍ የተተየቡ ወረቀቶችን አንድ በአንድ ሲፈትሹ ተስተውሏል፡፡ ይህ ከላይ የገለጽነው ተግባር የተፈጸመው ክስ ከመመሰረቱ አንድ ወር በፊት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሎሚ፣ ጃኖ እና አፍሮ ታይምስ ጋዜጦችን ደጋግመው ሲኮንኑ እና ሲያጣጥሉ እንደነበር ይታወሳል። አሁን የተደረገውም ክስ እስካሁን ሲደረግ የነበረው ክትትል እና የአፈና ውጤት ነው።

Filed in: Amharic