>

የኮሮና ወረርሽኝ መምጣት ያስደሰታቸው ነጋዴዎች እና የሐይማኖት ተቋማት መንበርከክ  (ፍቅር ሰይድ)

የኮሮና ወረርሽኝ መምጣት ያስደሰታቸው ነጋዴዎች እና የሐይማኖት ተቋማት መንበርከክ

ፍቅር ሰይድ
ስለ ኮሮና ቫይረስ ብዙ ነገር ተብሎዋል:: አንድ አይነትና አሰልች የሆነ ዓለም አቀፍ ትንታኔ ሲሰጥ ቆይቶዋል:: ስለ ቅድመ መከላከልና ስለ ጥንቃቄ ስለ ስርጭቱ፣ ስለገደለው ህዝብ ብዛት፣ ወዘተረፈ…..ያልተባለ ነገር የለም::ይህን በሚመለከት ደጋግሞ የመተንተኑን ስራ ለጤና ባለሙያዎች እንተወውና ኮሮና ቫይረስ ስላስደሰታቸው ስለ ንግድ ድርጅት ባለቤቶች እንዲሁም ስለ እምነት ተቁዋማቱ ግራ አጋቢ ማሳሰቢያና ስለክፉው መንፈስ ስልቂያ ጥቂት ነገር እናንሳ::
*
  በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውናና የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የግድ ወደ ኦንላይን ግብይት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው የገለጸው፣ለዚህም በርትቶ እንደሚሰራ ቃል የገባውና፤ በዘርፉ ለመሰማራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተስማማው፣ ወደፊት ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ቅኝ ተገዥ አገር እንደሚያደርጋት የሚገመተው፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና አቀንቃኝ የሆነውና የወሲብ ሮቦቶችን ሳይቀር በገፍ እያመረተ ለሽያጭ የሚያቀርበው፣ጃክ ማ እና ድርጅቱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እጅግ ተጠቃሚ ሆነዋል:: የመላው ዓለም ህዝብ ቤቱን ዘግቶ መቀመጡ ለእነ ጃክ ማ እና ለ ጄፍ ቢዞስ ሰርግ እና ምላሽ ሆኖላቸዋል!
*
ኮሮና የኦንላይን ቢዝነሳቸውን በእጅጉ አጧጡፎላቸዋል:: በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ አገሮች በሚገኙ ሁለገብ የግብይት ተቁዋማቶቻቸው በኩል ኦርደር የሚደረጉትን ነገሮችም ከዚህ ቀደም በነበረው ዘገምተኛ አካሄድ ማስተናገድ አቅቶዋቸዋል:: ትእዛዝ በዝቶላቸዋል::  እባካችሁ ቶሎ አምጡልን እየተባሉ እየተለመኑም ይገኛሉ:: የኦንላይን ቢዝነሱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስለተጧጧፈላቸውም የጃክ ማ ው አሊባባ ግሩፕ እና የጄፍ ቢዞስ አማዞን ለድርጅታቸው በአንድ ሳምንት መቶ ሺ ሰራተኞችን ለመቅጠር አስገድዶዋቸዋል::
*
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተጠቃሚ ከሆኑት ግለሰብና ድርጅቶች ውስጥ ዋናዎቹ የአሊባባ ግሩፕ እና የአማዞን ባለቤቶች ናቸው:: በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቻቸው ተሸፋፍነው እየመጡ ማናቸውንም አይነት ምርቶቻቸውን የእለት ምግቦችን ጨምሮ ቤት ለቤት ያደርሳሉ:: በዚህም ካሰቡት በላይ (ምናልባትም ከጠበቁት በላይ) በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሳምንታዊ ትርፍ እያጋበሱ ይገኛሉ:: ይህ ስለሆነ ብቻ “ኮሮና ቫይረስን እነሱ ፈጠሩት” ማለት ባይቻልም፤ ከዚህ በሁዋላ በሚኖረው ጊዜ ግን እንዲህ አይነቱ ወጣ ያለ ክስተት ለቢዝነሳቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡና ወደፊትም እንዲህ አይነቱ ነገር ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያበረታታቸው ሆኖ ሊገኝ ይችላል:: ምክንያቱም ቢዝነስ ነው:: ቢዝነስ ደግሞ ምንጊዜም ቢዝነስ ነው…።
*
ሌላው የዚህ ቫይረስ መከሰት ተጠቃሚ ያደረገው ደግሞ ታጥቀው የሚያገለግሉትን አለቃቸውን ነው:: የክፉው መንፈስ አለቃ አማኙንና አማኝ ነኝ ባዩን ህዝብ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ዘፍቆ “ከአምላክህና ከቫይረስ?” ሲል አስመርጦታል! አማኙ ህዝብ በየቤቱ ዘግቶ እንዲቀመጥ በማድረግ ምዕመኑ ላይ እየተሳለቀ ይገኛል:: ምዕመኑ ከአምላኩና ከቫይረስ ቫይረስን እንደሚፈራ አረጋግጦበታል ማለትም ይቻላል:: ወደፊት ምን ያህሉ የምድር ሰው የእርሱ ወታደር እንደሚሆንም ሊገምትበት ይችላል::
*
በዚህ ቫይረስ ምክንያት ፈጣሪን አማኝ የሆነው ህዝብ (ምዕመን) ከስር የምትመለከቱትን አይነት ከየሐይማኖት ተቁዋማቱ የተሰጠ ማሳሰቢያ (የማስፈራሪያ መልዕክት) ተቀብሎ  እንዲህ ከሆነ፤ ወደፊት በሚኖሩ እጅግ አስከፊ በሚሆኑና አማኞች የሚፈተኑባቸው ከባባድ ጊዜያቶች ሲመጡ ምን  ሊከሰት እንደሚችል ለመገመት ሞክሩ። የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ በሐይማኖተኛው ላይ የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ የሚያሳቅቅ ነው:: ቫይረስ ፈርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ከመሄድ የሚቆጠብ ምዕመን ከመሆን ይሰውረን የሚያስብልም ነው! እርግጥ ነው መንግስት እንደ መንግስት ህዝቡን ማስጠንቀቅና መከልከል ሊኖርበት ይችላል:: ምዕመኑም ከአምላኩ በታች የየራሱን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል::
*
ነገር ግን ይህ አይነቱ ማስጠንቀቂያ ከሐይማኖት ተቋማት አመራሮች በኩል መሰንዘሩ እጅግ አስገራሚና ምዕመኑን “ሞራል ዳይለማ” የሚባል ነገር ውስጥ የሚከት ነው። “በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቤተ እምነቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ስለዘጋን በየቤታችሁ ሆናችሁ ጸልዩ” ማለት ለአንድ ሃይማኖተኛ ወይም አማኝ ምን እንድምታ ይኖረዋል? “በማህበር ሆናችሁ ብትጸልዩ እኔ በመካከላችሁ  እገኛለሁ” የሚለውን ቃል፤ ደጋግመው ሲሰብኩ የነበሩ ሁሉ ዛሬ ላይ ቫይረስ ፈርተው ከተደበቁ አምላካቸው ከምን ከምን አይነት ነገር እንደሚያድናቸው በዝርዝር ለይተው ማስቀመጥ አለባቸው! ይህ በራሱ እምነት ምንድነው?ሐይማኖትስ ምንድነው?ለሚለው ለአህዛብ ጥያቄ “ምንም”ብሎ እንደመመለስ የሚቆጠር ነው:: “በአምላክህ መተማመን አቁም፤ ትበላለህ!” ብሎ እንደማስተማርና እንደመምከር  ያለ የኢኣማኒያን አቁዋም ሆኖ እናገኘዋለን::
*
በመሰረቱ አምላክ ሰዎችን ከማዳንና ለሚያምኑት ከመታመን፣ የሚያምኑትንም ከመጠበቅና ከመንከባከብ፣ የአማኞችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ፣ ፍላጎታቸውን ከማሙዋላት፣ ጸሎታቸውን ከመስማት፣ አጥፍተው ይቅር በለን ለሚሉት ምህረት ከመስጠት ውጭ ሌላ ስራ የለውም:: የስጋት፣የበሽታ፣ የሽብርና የክፋት አምላክም አይደለም! በተመሳሳይ ሁኔታ የክፉው መንፈስ አለቃ ሰዎችን ከማሸበር፣ ከመጉዳት፣ ከማጎሳቆል፣ ከማቁሰልና ከማሳመም፣ ከመረበሽና ከማጥፋት በቀር ሌላ ስራ የለውም። ልዩነታቸው በርህራሄና በጭካኔ፤ በምህረትና በምህረት የለሽነት፤ በመግደልና በማዳን ዙሪያ የሚሽከርከር ነው!አንድ አማኝ እነዚህን ነገሮች በውል ሳይረዳ ከሆነ ሐይማኖተኛ የሆነው የማያውቀውን አምላክ እንዲሁ በደመ-ነብስ ሲያመልከው እንደኖረ ይቆጠራል።
*
ቫይረሱ ከምድር ሳይንስ አቅም በላይ ከሆነ፣ ከምድር ሃያላን መንግስታት አቅም በላይ ከሆነ፣ ሰዎች በተለይም አማኞች ወደ መፍትሄው አካል ወደ አምላካቸው የበለጠ መጠጋት ነው የነበረባቸው:: የሐይማኖት መሪዎችም ምዕመኑን የበለጠ ወደ አምላካቸው እንዲጠጉ መቀስቀስ፣ ቃሉን መሰረት አድርገው መገፋፋት፣ በግፊትም ማስጠጋት ሲኖርባቸው፤ በተቃራኒው እነሱም ፈርተው ምዕመኑንም አስፈራርተው ማህተም ባለው መግለጫና ማሳሳቢያ “ቤተመቅደስ ዘግተናልና እንዳትመጡ” ማለት፤ “ከእኛም ከአምላካችንም አቅም በላይ የሆነ ቫይረስ ተከስቶዋልና አትምጡ” እንደማለት ይቆጠራል። ይህም በሌላ አገላለጽ መፍትሄው ከሃያል አገራትና ከበለጸጉ አገራት፤ እንዲሁም ከምድራዊው ሳይንሳዊ   ጥበብ እስኪመነጭና እስኪገኝ ድረስ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት አቁመናል” ብሎ እንደመግለጽ የሚቆጠር ነው።
*
ይህም በራሱ መፍትሄውን ከቫይረሱ  ፈጣሪ ከራሱ ከክፉው መንፈስ አለቃ እንደመሻትና ከእርሱ ብቻ እንደመጠበቅ የሚቆጠር ነው! በጥቅሉ ይህን ቫይረስ አስመልክቶ ከየሐይማኖት ተቁዋማቱ የተሰጡ ማሳሰቢያዎች የምዕመኑን የእምነት ጽናት የሚሸረሽሩ ናቸው። የየሐይማኖቱ መሪዎች እራሳቸው ስተውና የአምላክን ህልውና ተጠራጥረው ምናልባትም ክደው ምዕመኑንም ለጥርጥር እየዳረጉትና እያስካዱት እንዳለ የሚያስረዳ ነው።
Filed in: Amharic