>

መንግስት ድንበር ያስጠብቅ፣ ከእገታ ያትርፈን፤ያኔ ፈተናዎች ይቀላሉ!!! (ረ/ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ደነቀ)

መንግስት ድንበር ያስጠብቅ፣ ከእገታ ያትርፈን፤ያኔ ፈተናዎች ይቀላሉ!!!

 

ረ/ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ደነቀ
በአማራ ህዝብ ላይ በተለይም በጎንደር አማራ ላይ ሶሶት አይነት ፈተናዎች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ እነዚህም የኮሮና ቫይረስ፣ የሱዳን ሰራዊት ወረራ እና የህዝብን ቀጣይ ሰላም የሚያናጋ/ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ/ በፋኖን ላይ በኢህዴን ቁጥር-4 የታወጀ ዘመቻዎች ናቸው፡፡ ለተገዳይ አማራ በሱዳን አልበሽር በተሰኘ ታንክ እና በአሜሪካ ሰራሽ ስናይፐርም ሆነ በኮሮና ቫይረስ መሞት ያው ሞት ነው፡፡
 በግልጽ እንደሚታየው የኢትዮጵያ መንግስት ድንበር ጥሶ የገባን የሌላ ሀገር ሰራዊትን ባለማስወጣት ከመንግስትነት ዝቅ የሚያደርግ ምግባር ማሳየቱ ሳያንስ የአማራ ባህላዊና ለአደጋ ጊዜ ደራሽ የማህበረሰብ ተቋም የሆነውን ፋኖን ለመደበደብ ታንክ እየጎተተ እንደሆነ ከቦታው የሚሰራጩ መረጃዎች አስረጂ ናቸው፡፡
ድርጊቱ ጊዜውን ያልጠበቀ ስለመሆኑ እና የአማራ ህዝብ ከኮሮና ለመትረፍ ከቤት ቁጭ እንዳለ ህግ በማስከበር ሰበብ ፋኖን ለመምታት እንደታሰብ ያለመረዳት የፖለቲካ ጨዋነት ነው፡፡
ሞት በታንክም ሆነ በኮሮና ያው ሞት ነውና ተፋልሞ መሞትን የሚመርጥ አማራ እንደሚበረክት ታሪክ ምስክር ነው፡፡ከእናት አባታቸው ጉያ ከተነጠሉ መንፈቅ ያልሞላቸውን ተማሪዎች ከእገታ ነጻ ማድረግ እና ድንበር ጥሶ ሉአላዊነትን የተጋፋን የጎረቤት ሃገር ሰራዊት የማስወጣት ወታደራዊ ስምሪት ቅድሚያ የሚሰጠው የእውነተኛ መንግስት ተግባር ነው፡፡
 የዶ/ር አብይ እና የኢኅዴን ቁ-4ቱ የደመቀ መኮንን መንግስት ይህን ኃላፊነት በመወጣት ከተባበረን ለጊዜው የአማራ ህዝብ ፈተና ኮሮና ብቻ ይሆናል፡፡ በጎንደር አካባቢ ለሚታዩ የሰላም መናጋቶች የደረጀውን የበላ-ልበልሃ የሙግትና የእርቅ ባህል ተጠቅመው የሀገር ሽማግሌዎች፣ ፋኖ፣ የኃይማኖት አባቶች ችግር ፈቺ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ይህ ካልተደረገና ማዋከቡ ከቀጠለ ህዝቡ በጥንቃቂ እና በመረጋጋት ጤናውን ለመጠበቅ ይቸገራል፡፡ ቀጣይነት ያለው ሰላም የማስፈን ፈተናው እየከበደ ይመጣና ችግሩ ለሁላችንም ይተርፋል፡፡
Filed in: Amharic