>

በኮሮና ምክንያት ቦርዱ ምርጫውን አራዘመ! (አሰፋ ሀይሉ)

በኮሮና ምክንያት ቦርዱ ምርጫውን አራዘመ!

አሰፋ ሀይሉ
* ፕሬዚደንት የባራክ ኦባማ፡- “በኢትዮጵያ ያለው በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው!” በማለት ለዓለም በአደባባይ ያወጁትን ያንኑ የኢህአዴጓን ኢትዮጵያ ዘመን ከኦባማዊው ‹‹ወርቃማ ዲሞክራሲ›› ድምዳሜ ‹‹ወደለየለት ግንባር ቀደም አረመኔያዊ አምባገነን›› ሥርዓትነት አውርዶ በዜሮ የሚያባዛው – የአሜሪካኖቹን የቀድሞ አስተያየት የከለሰ ‹‹አንኦፊሺያል›› አቋም መሆኑ ነው መሰል! 
 
*  ጠ/ሚ አብይና ብሔራዊባንክ እነ ቮዳኮምና ኤምቲኤንን በሀገርውስጥ ባንክ ንግድ ላይ አሰማሩ… — ያንድ ቀን ዜናዎች!”
* ቀልቀሎ ስልቻ… ስልቻ ቀልቀሎ!
ትናንት በጠዋቱ – ገና ለማኝ ሳይፀዳዳ – በዓለማቀፍ የዜና አውታሮች ስለ ኢትዮጵያ የተሰራጨ የተጠበቀም ያልተጠበቀም ዜና ነበር፡፡ “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኮሮናው ምክንያት ለነሐሴ የያዘውን የምርጫ ሰሌዳ – ወረርሽኙ እስኪያበቃ ድረስ – ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን አስታወቀ!” የሚል ዜና በዓለም ተሠራጨ፡፡ ይቀጥልና አልጀዚራ ደግሞ በዜናው በ‹‹አሻጋሪው›› በአብይ አህመድ አሊ ላይ የተሰማውን ኩምታ – የቀድሞውን የወያኔ-ኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ከሰጠው የሰላ ትችት ጋር እንዲህ በማለት ያቀርበዋል፡-
‹‹የዚህ ምርጫ መካሄድና አለመካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ ማንነት የሚፈተንበት ቁርጥ ተግባር ነው በሚል በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም መጨረሻው በወረርሽኙ ሰበብ ምርጫውን በማራዘም ተደምድሟል!››
በማለት ኩምታውን አስፍሮ – ቀጥሎ ግን እንዲህ በማለት ያለፈውን የኢህአዴግ ዘመን እንዲህ በማለት ይሄላ፡-
‹‹ኢትዮጵያ እስከዛሬ ድረስ በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ
ግንባር ቀደም አረመኔያዊ አምባገነን አገዛዝ ከነገሰባቸው ሀገሮች በዋነኝነት ተጠቃሽ ሆና መቆየቷ ይታወቃል!››
በማለት እነ አብይ አህመድን በሚኒስትርነት ሲያንጎማልል የነበረውን የኢህአዴግ ዘመን አምባገነናዊ ባህርይ አስቀምጦ ዜናውን ይደመድማል፡፡
ይሄ አስተያየት እንግዲህ አሁን በአሜሪካ ባለቤትነት ሥር የወደቀው አልጄዚራ – በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ አያያዝ ጉዳይ ላይ የቀድሞው ዲሞክራት የአሜሪካ ፕሬዚደንት የባራክ ኦባማ፡- “በኢትዮጵያ ያለው በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው!” በማለት ለዓለም በአደባባይ ያወጁትን ያንኑ የኢህአዴጓን ኢትዮጵያ ዘመን ከኦባማዊው ‹‹ወርቃማ ዲሞክራሲ›› ድምዳሜ ‹‹ወደለየለት ግንባር ቀደም አረመኔያዊ አምባገነን›› ሥርዓትነት አውርዶ በዜሮ የሚያባዛው – የአሜሪካኖቹን የቀድሞ አስተያየት የከለሰ ‹‹አንኦፊሺያል›› አቋም መሆኑ ነው መሰል!
እና እኛስ የቱን ኢህአዴግ አምነን እንቀበል? ዲሞክራቱን ኢህአዴግ? ወይስ የአምባገነኖች ቁንጮውን ኢህአዴግ? አሁንስ ስሙን ቀይሮ ያለው የኢህአዴግ ወራሽ ማነው? ሰዎቹስ ማን ናቸው? አሁን ‹‹የለየለት አረመኔያዊ አምባገነን›› በተባለው በቀድሞው ኢህአዴግ ዘመን በሁለት እጃቸው ሲፈተፍቱ የነበሩት ራሳቸው እነዚያው የኢህአዴግ ሰዎች፣ ፓርቲውስ ስሙን የቀየረ ያው ራሱ ፓርቲ፣ ፓርላማውስ ስሙንም አባላቱንም ያልቀየረ ያው ራሱ ፓርላማ፣ እነዚያው ራሳቸው ፍርድ ቤቶች፣ ያው ራሱ ሚሊቴሪ፣ ያው ራሱ የኢ-ፍትህ ሥርዓትና ሰዎች አይደሉም ወይ? እና የቱን የኢህአዴግ ማንነት ኮንነን፣ የቱን የኢህአዴግ ማንነት ደግሞ በአዲስ ባህርይ እንቀበለው??
እንዲህ እንዲህ እያልኩ የኢህአዴግ ወ ብልፅግናን ዘመን አደናጋሪ አንድነትና ሁለትነት ሳሰላስል የ60ዎቹ የኃይሉ ገብረዮሐንስ (የገሞራው) ‹‹ስልቻ ቀልቀሎ›› ግጥም ፊት ለፊቴ መጣብኝ፡-
‹‹ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ፣
ማንን ይመርጡታል፣ ማን ከማን ተሽሎ!
ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ
ምን ደኅና አለበት፣ ሁሉም አራሙቻ!
ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ
ዝም ብለሽ ተቀበይ፣ የሰጡሽን ብቻ!››
          – ገሞራው (ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ 1966)
ምርጫው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሟል! ጥሩ ነው! ማለቴ ምርጫው ቢካሄድም – ኢህአዴግ በአካሉ፣ በአምሳሉ የፈለፈላቸው ዘረኞችና ጎጠኞች ‹‹የፖለቲካው አጋፋሪዎች›› – በሕዝባዊ ምርጫ – ‹‹ለመመረጥ›› እና ‹‹ወደ ሥልጣን ለመውጣት›› እንዲችሉ አድርገው – ሕዝቡን ባገነገነ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ጫፍ ላይ አድርሰው – ቄጠማ ጎዝጉዘው – በክልላዊ የመቦረቂያ ሜዳቸው ላይ ምንሽርን ከአመፃ ጉግማንጉግ ሠራዊት ጋር አነባብረው – የምርጫውን ፊሽካ በንቃት እየተጠባበቁ ያሉበት ሰዓት ነው አሁን፡፡
ምርጫው ቢካሄድም ዘረኛው ፖለቲካችንና የኢህአዴጓ የጎጠኞች ኢትዮጵያ – ከነተዋናዮቿና ከነአበጋዞቿ እንደምትቀጥል የታመነ ነው! ምርጫው ባይካሄድም – ለቀጣዮቹ የኮሮና ወረርሽኝም ጊዜያት ሆነ – ለቀጣዮቹ ጃዋራዊያንና ብጤዎቻቸው ወረርሽኝ ዘመን – ሀገሪቱ በእነዚያው በለመድናቸው ጠባቦችና የኢህአዴግ የተስፋ ወራሾች እየተዘወረች እንደምትቀጥል ግልፅ ነው! ምርጫው ተካሄደም፣ አልተካሄደም – አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ ኢንጅሩ ነው!!
(ለመሆኑ ተፎካካሪዎችም ሆኑ ተባዪዎች – በአሁኑ ወቅት እንደልባቸው ተዘዋውረው ሃሳባቸውን ማስተላለፍና ሕዝብን መቀስቀስ ይችላሉ ወይ? ግለሰቦችና ሕዝብስ የፈለገውን ዓይነት የፖለቲካ አቋም መርጦ ሳይደበደብና ሳይቀነደብ ባገነገኑና በታጠቁ ዘረኞች ቁጥጥር ስር በገቡ የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ እንደልብ በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላሉ ወይ አሁን? የግለሰብን አይደለም… የሕዝብን መብት የሚያስከብር ህጋዊ አካልና ኃይል አለ ወይ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት? … እና ጥሩ ነው፡፡ ምርጫው ቢራዘም! ደግሞም ጥሩ ነው፡፡ ባይራዘምም! ቀልቀሎ ስልቻ! ስልቻ ቀልቀሎ….!)
ትናንት በጠዋት የምርጫ መራዘም ወሬ ተሰማ፡፡ ጥሩ ነው – ወይም – እንዳሻው – ብለን አንለፈው፡፡ ዛሬ ደግሞ በጠዋቱ – የለማኝ እዳሪ ሳይታይ – አሁንም ደግሞ – ሌላ ከኢትዮጵያ የወጣ እንግዳ ዜና ዳግም በዓለማቀፍ ማሰራጫዎች ተናኘ፡፡ “ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ላልሆኑ ዓለማቀፍ የቴሌ ቸርቻሪዎች በሀገሯ ገብተው የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ አዋጅ አፀደቀች!” ይላል የብሉምበርግ የዜና ማሰራጫ፡፡
‹‹ታላቁ የፕራይቬታይዜሽን ተስፋ የተጣለባቸው አሻጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ – የኢትዮ ቴሌኮምን ሼሮች ለውጭ የቴሌኮም አቅራቢዎች ለጨረታ አቀረቡ – ኤም ቲ ኤን፣ ቮዳኮም፣ ኦሬንጄ ኤስ ኤ… ፍላጎታቸውን አሳይተዋል…›› እያለ ያትታል ሌላው ደግሞ…፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አሁን 105 ሚሊየን ነው – በከ30 ዓመት በኋላ የህዝብ ቁጥሯ በእጥፍ ተባዝቶ በ2050 ላይ 210 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖራት – እና ከፍተኛ የስልክ ተጠቃሚ ገበያ እንደጉድ የሚገኝባት – ለቴሌኮም ንግድ እና ለከፍተኛ ትርፍ የጎመራች – ገና ፖቴንሻሏ ያልተነካች ድንግል ገበያ ነች… ›› እያለ በአሁኑ ብቻ ሳይሆን – ለወደፊቱ የሚወለደውን ስልክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊ እየቀመረ ዜናውን ያስውባለው ሌላው ዜና ማሰራጫ ደግሞ፡፡
ሌላው ደግሞ ‹‹ይህ የኢ-ባንኪንግ ንግዱን ዘርፍ ለቴሌኮም ቸርቻሪዎች ክፍት ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ መንግሥት ተስፋ የተጣለበትን የሀገሪቱን በመንግሥት የተያዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ወደ ግል ይዞታ የማዞር ታላቅ ዲሞክራሲያዊ እመርታን የፈነጠቀ ቁርጠኛ ተግባር ነው…›› እያለ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዘመናይነትና ዲሞክራትነት፣ አርቆ አስተዋይነትና የለውጥ ብርሃን አመንጪ መሆናቸውን… እያተተ የውዳሴ መዓት ያዥጎደጉዳል፡፡
ያው በመነሻችን የጠቀስነው ብሉምበርግ ደግሞ መልሶ፡- ‹‹አዲሱ የአብይ አህመድ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ የውጭ የቴሌኮም ኢንቬስተሮቹ በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ንግድ ሲሰማሩ 10 ኢትዮጵያውያንን ያካተቱ ሼሮች የግድ እንዲኖራቸውና፣ ባለቤትነታቸውንም ከኢትዮጵያውያን ጋር በሼር የማጋራት ግዴታን ይጥልባቸዋል… ያም ለኢትዮያውያን ዕድል የሚከፍት ነው… ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ አዋጃቸው – በዚህ የቴሌኮም ኢ-ባንኪንግ ሥራ መሳተፍ የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ባንኮችም – ፍላጎታቸውን ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት እንደሚችሉ አስታውቀዋል…፣ የውጭ ኢንቬስተሮቹ የተጠየቁት መነሻ ካፒታል 1.5 ሚሊየን ዩኤስ ዶላር ወይም 30 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር ነው…!›› እያለ ይዘግባል ዜናውን፡፡
ለአሁን በዜና ዘገባዎች የሰፈሩትን የመንግሥትን የሽቀላ ዜናዎች ብቻ ሰምተን እዚሁ ላይ ብንለያይ ጥሩ ነው፡፡ ቆይ ቆይ… ግን! እንዴ…?! የምርጫ ዘመኑ ያበቃ እና ኮሮና በመሐል ባይመጣለት የነሃሴን ዝናብ አልፎ ለመስቀል ሀገሬ እገባለሁ እያለ የሚብሰከሰክ ምክር ቤት… በምን አግባብ ነው ግን… የኢትዮጵያን የሕዝብ ሃብት የሆኑ ተቋማት ባለቀ ሰዓት እንደማጣሪያ ሽያጭ ለዓለም በጨረታ አውጥቶ ለመቸርቸር የሚችለው? አሁን ስልጣኑ የሚያበቃ ፓርላማ እንዴት ብሎና ምን አስቦ ነው በወደፊቱ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ የሃብት አስተዳደር መመሪያ አውጥቶ የወደፊቱን ጊዜ በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል የሚዳዳው??
ገና በሕዝብ ያልተመረጠውና አሻጋሪ ነኝ ብሎ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁት የቀድሞው የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ሥልጣኑን የተረከበው የኢህአዴጉ (የአሁኑ የብልፅግናው) የአብይ አህመድ መንግሥትስ – በምን ሥልጣኑ እና በየትኛው የሕዝብ ውክልናው ነው – ምርጫውን ባራዘመ ማግሥት – የሀገርን ሃብትና ንብረት – ከፐብሊክ ይዞታነት ወደ ፕራይቬት ይዞታነት እያዛወረ በሃላል የማጣሪያ ሽያጭ መቸብቸብ የሚችለው?? በየትኛውስ አግባብና የፋይናንስ አካሄድ ነው… የፋይናንስ ተቋማት ላልሆኑ የተለያዩ የውጭ ሀገራት የቴሌኮም አገልግሎት ቸርቻሪዎች በኢትዮጵያ ገብተው የባንኪንግ ፋይናንስ የንግድ ሥራን እንዲቀሽቡ የሚደረጉት?
ቆይማ..! ዓለማቀፍ እንቅስቃሴ ያላቸውን ትላልቅ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገብተው የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ መፍቀድ ቁርጡ የታወቀ አንድ ነገር ነው! ዓለማቀፍ ዝና ያላቸውን የቴሌኮም ቸርቻሪዎች ግን በኢትዮጵያ ገብተው የባንክ አገልግሎት ስጡልን ማለት… – እንዴት ነው ነገሩ…?? ባንኮች ከቴሌ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ዲል (ስምምነት) ያደርጋሉ፣ በዚያ መሠረት የባንኪንግ አገልግሎታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የቴሌ ኮርፖሬሽኖችን ግን ወዳገር ቤት እየጠራህ – እስከከፈላችሁኝ ድረስ ምናገባኝ – ኑ እና በኦንላይን ባንኪንግ ንግድ ተሰማሩ – የሚለው የጠሐዩ፣ የለውጡ፣ የብልፅግናው፣ የብሩሁ መንግሥት ጥሪ… ግራ የሚያጋባ ነው! ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን… ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ሀገሪቱን እንዲያስተዳድር ሥልጣን ይዞ የተቀመጠ አካል – በሽግግር ዘመኑ – ይህንን ለማድረግ ማን ስልጣን ሰጠው?? የሚለው ጥያቄ ገና ብዙ ጭቅጭቅ የሚያስነሳና የሚያከራክር ነው!!!
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የአናርኪዝም ሁናቴ – እና በገባንበት ተጠያቂነት የሌለበት ከፍ ያለ የውዥንብርና የግርግር ወቅት ላይ – በዚያ ላይ የወረርሽኙም ሆነ ሌሎች ቀውሶች፣ ግርግሮችና የግጭት ጦሶች ተጨምረውበት – በግብርና ምርቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ የሆነው ኢኮኖሚያችንና – በቋፍ ላይ የሚገኘው የአብዛኛው ሕዝባችን ኑሮ መጻዒ ሁኔታ – እና በሀገር ደረጃ ሊያጋጥም የሚችለው የኢኮኖሚ አቅም ውሱንነትና ቀውስ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም! አንዳንድ ግሎባል የኢኮኖሚ ዳሰሳዎችም ይሄንኑ የተጋረጠብንን አደጋ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
እና በዚህ ወቅት የዓለማቀፉን አበዳሪዎች ይሁንታ ለማግኘት፣ ከዚያም ከፍ ሲል የግል ዝናና ስም ለማትረፍ ተብሎ – የህዝብን ሀብት ለውጭ ኮርፖሬሽኖች በመቸርቸር ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ የተነሳው የጠ/ሚ አብይ አህመድ መንግሥት – የተሰማራበት ሀገሪቱን በአስቸኳይ የማጣሪያ ሽያጭ የማዋል አጉል አካሄድ – በተለይ በዚህ ወቅት – ጊዜያዊ ችብቸባው ካበቃ በኋላ – በእውን የታቀደለትን ኢኮኖሚያዊ ግብ ሊያሳካ የመቻሉ ጉዳይ አጠያያቂ ነው! አጠያያቂ ብቻም ሳይሆን አስከፊ አሉታዊ ውጤቶችን የሚያመጣና ግራ የገባው ነገር ነው! ግራ የገባው ነገር ብቻ ሳይሆን – በሌለና ባልተሰጠ የሕዝብ ሥልጣን ላይ ተሁኖ – መንግሥት እየፈለጠ-እየቆረጠ ሲንቀዠቀዥ የምናይበት የለየለት አምባገነናዊ ሩጫ ነው!
ከመዓቱ ይሰውረን! ቸር ቸሩን ያሰማን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic