>
5:13 pm - Monday April 18, 1927

በሽታውም እንደ ታሪክ እራሱን እየደገመ ይሆን?? (እንዳለ ጌታ ከበደ)

በሽታውም እንደ ታሪክ እራሱን እየደገመ ይሆን??

እንዳለ ጌታ ከበደ
* በጥንቃቄና በዲሲፕሊን ጉድለት ራስንም ሌላውንም እንደማጣት ለጸጸት የሚዳርግ ነገር የለም!
በኮሮና ቫይረስ በሚያጋልጥ ሁኔታ ራስን ማግኘትም፣ ቫይረሱ በሚመራው የአጥፍቶ መጥፋት ጦር ውስጥ፣ የሰራዊቱ አዝማች እንደመሆን ነው!!!
በደርግ ዘመን፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ፣ በጸረ-አብዮተኛነት ተፈርዶባቸው የነበሩ ወጣቶች ከርቸሌ በነበሩበሩበት  አንድ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ። ከርቸሌ ወረርሽኝ ገባ። ኮሌራ በእስረኞች ላይ ዘመተ።
ከስንትና ሰንት ጥይት አምልጠው በቁጥጥር ስር የዋሉ እነዚህ ፖለቲከኞች ኮሌራ አለርህራሄ አንክቶ ይበላቸው ጀመረ። “የሞቱትና የታመሙት ልጆች ልብሶች ደግሞ ተቃጠሉ” ትለናለች፣ ደራሲት ሕይወት ተፈራ፣ Tower in the sky(ማማ በሰማይ) በተሰኘው መጽሐፏ፣ በዘመኑ ስለነበረው ሁኔታ ስትተርክልን። “ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሲባል ከወህኒ ቤቱ ምንም ሳህን ወደ ውጭ እንዳይወጣ ተደረገ።”
ኮሌራው የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ወንዶች ላይ ነበር የዘመተው። ወደ ሴቶች ክፍል ክንፍ አብቅሎ በላያቸው ላይ እንዳያንዣብብ ሴት ታሳሪዎች ውሏቸው አልጋ ላይ ሆነ፤ ከንኪኪ ተራራቁ። የእጅ ሰላምታ መለዋወጥ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊትነት የተመዘገበ መሠለ። ሰሞኑን ሲደረግ እንዳየነው፣ መድኃኒት ነው ተብሎ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚ፣ ዝንጅብል፣ ቃርያና ሌሎች የሚያቃጥሉ ቅመማ ቅመሞች ተደማምረው መወሰድ ተጀመሩ። በዚህ ወረርሽኝ ከሃምሳ እስከ መቶ ሃምሳ ወንዶች የመጨረሻውን እንቅልፍ አንቀላፉ፤ ተቀጠፉ። እና በዚህ የሽብር ዘመን ሕይወት እጅግ ወሳኙን ጥያቄ ራሷን ትጠይቀዋለች።
“ከደርግ ጥይት አምልጬ፣ ከስምንት ዓመት በላይ በወህኒ ቤት ቆይቼ በተቅማጥ ብሞት፣ እጅግ አሳዛኝ ይሆናል”
አኗኗራችንም አሟሟታችንም ያሳምረው ማለት ተገቢ ምኞት ነው። እውነትም ሰው ዋጋ ለከፈለበት ጉዳይ ሲኖርና ሲሞት ነው ደስ የሚለው።
በጥንቃቄና በዲሲፕሊን ጉድለት ራስንም ሌላውንም እንደማጣት ለጸጸት የሚዳርግ ነገር የለም!
በኮሮና ቫይረስ በሚያጋልጥ ሁኔታ ራስን ማግኘትም፣ ቫይረሱ በሚመራው የአጥፍቶ መጥፋት ጦር ውስጥ፣ የሰራዊቱ አዝማች እንደመሆን ነው!
ይህ ደግሞ ይበልጥ አሳፋሪ ነው!!!!!
Filed in: Amharic