>

እግዚአብሔርና ኮሮና ቫይረስ (ፕሮፈሰር መስፍን ወልደማርያም)


እግዚአብሔርና ኮሮና ቫይረስ

 

ፕሮፈሰር መስፍን ወልደማርያም

 

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ በእግዚአብሔር የሚያምን ነው፤ መናፍቃን የሉበትም ማለቴ አይደለም፤ የዘንድሮው ወረርሽኝ ግን መናፍቃኑን የበዙ አድርጓቸዋል፤ በዚህም የተነሣ በእግዚአብሔር ማመንና መተማመን ከወርሽኙ ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጡ ይመስላል፤ ወረርሺኙን መፍራት እግዚአብሔርን ችላ ማለት፣ እግዚአብሔርን መፍራት ወረርሺውን ችላ ማለት እየመሰለ ነው።

‹‹እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር›› የሚለውን ያመነ ለቫይረሱ ተገዝቶ ከቤተ እግዚአብሔር አይቀርም፤ ቫይረሱ በበኩሉ ‹‹ብታምንም ባተምንም እኔ አልምርህም፤›› ካለ እምነትና ቫይረስ ተፋጠጡ! ሀኪሞች እምነቱን ሳያድኑ ወረርሺኙን ማዳን ይችላሉ ወይ? ሊቃነ ጳጳሳቱስ ወረርሺኙን ሳያድኑ እምነታቸውን ማዳን ይችላሉ ወይ? ሀኪሞቹና ሊቃነ ጳጳሳቱም የተፋጠጡ ይመስላል!

ችግርና መፍትሔ

ብዙ ሰዎች እኔ ስለማኅበረሰባዊ ችግሮች ስጽፍ መፍትሔ አታቀርብም እያሉ ይወቅሱኛል፤ ችግራቸው ይገበኛል፤ እነርሱ ግን የኔ ችግር የገባቸው አይመስለኝም፤ አንደኛ እኔ ሥራ አስፈጻሚ አይደለሁም፤ እኔ በግለሰብ ደረጃ የአገሬንና የማኅበረሰቡን ችግር መገንዘብና ማስገንዘብ የምፈልግ የሀሳብ ሰው ነኝ፤ ከዚህ ውጭ ብወጣ አድማጭ ካለመኖሩ ሌላ ጠብ ይሆናል፤ በጃንሆይ ጊዜ አንድ ሀሳብ አቅርቤ በጀማ የተለየውን መርሀቤቴን አውራጃ እንዲሆን አስደርጌአለሁ፤ ሌሎችም ጥቃቅን ነገሮች አሉ፤ ግን ጮኬ ጮኬ ያልሆነልኝም ብዙ አሉ፤ ለምሳሌ ከእጅ ወደአፍ የሚያመርተው ገበሬ ግብር መክፈል የለበትም፤ አንዱ የችጋር ምክንያት ይህ ነው፤ እሰካሁን ጆሮ አላገኘም!
መፍትሔ ካላመጣህ ስለችገር አትናገር ወይም አትጻፍ የሚሉ ካሉ አስቸጋሪ ነው፤ እኔ ችግሩን ሳየው እንዳየሁት አቅርቤው የሚነካው እንደነካው ይመልሳል፤ ያልገባው እንዳልገባው ቢጠይቅ መልካም ነው፤ ሌሎች ሀሳቡን ይዘው ይበልጥ እያፍታቱ ወደላቀ ደረጃ ያደርሱታል ብዬ አምናለሁ፤ ወድቆ ከቀረም ዋጋ የለውም ማለት ነው፤ የአንድ ሰው ሀሳብ ነው!

Filed in: Amharic