>

ፈተናን ድል እንነሳለን እንጅ አይሰለጥንብንም (አባይ ነህ ካሴ)

ፈተናን ድል እንነሳለን እንጅ አይሰለጥንብንም

አባይ ነህ. ካሴ
በዚህ ክፉ ቀን በየቤታችሁ ተሰብሰቡ የተባሉ ሁሉ መውጫ ላለው ፈተና እንዳይዝሉ ልባቸውን ሊያበረቱ ይገባል። የምናመልከው እግዚአብሔር እንደ ጢስ አብንኖ እንደ ጉም አትንኖ ያጠፋዋል!!!
በእምነት ስንጓዝ ባሕረ ኤርትራን የሚያኽል ፈተና አላራምድ ይለን ይኾናል። ግን እግዚአብሔር በሠዓቷ ሳይዘገይ ከተፍ ይላል። በአንዲት በትር ፈተናችንን ግራና ቀኝ ይከፍለዋል። ከዚህ ቀደም የሰው እግር ባልረገጣት አዲስ መንገድም ያሻግረናል። ለእኛ ብቻ የተፈቀደች መንገድ ናትና ፈርዖን እና ሠራዊቱ በዚያች መንገድ ደፍረው ሲገቡ ዶግ አመድ ይኾናሉ። ፈተናውም መውጫውም ለእኛ የተዘጋጀ ነውና።
ጎልያድ ፈተናችን ከፊታችን ሲቆም በሰልፍ ኃያል እግዚአብሔር ልበ አምላክ ዳዊትን ማምለጫችንን ያመጣል። ባቢሎናውያን ነቢዩ ዳንኤልን በተራቡ አናብስት ጉድጓድ ሲጥሉት መልአኩን ልኮ የአናብስቱን አፍ ይዘጋል። አውሬው ስለእኛ ራቡን ይታገሳል። እየጎመጀ አይበላንም። እያዛጋ አይውጠንም።
እነ ቅዱስ ጴጥሮስን በኢርቱዕ ፍርድ የጊዜው ዳኞች በወኅኒ ቢቆልፉባቸውም እግዚአብሔር መልአኩን ልኳል። የታሰረበት ሰንሰለት ተበተነ። በሰው የተዘጋጀው ደጅ እንደተዘጋ ቁልፍም ሳይሰበር የራሱን በር ከፍቶ አውጥቷቸዋል። በሩ ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው የሚለውን ስናነብብ እግዚአብሔር የፈታውን ሰው አስሮ ሊያቆየው እንዳይችል እንታመናለን። የሰው ፍርድ ሲያስራቸው የእግዚአብሔር ፍትሕ በነጻ ለቅቋቸዋል። በእርሱ ታምኖ ታስሮ መቅረት የለም። ሥራ ፲፪ ፡ ፮-፲፩።
በዚህ ክፉ ቀን በየቤታችሁ ተሰብሰቡ የተባሉ ሁሉ መውጫ ላለው ፈተና እንዳይዝሉ ልባቸውን ሊያበረቱ ይገባል። የምናመልከው እግዚአብሔር እንደ ጢስ አብንኖ እንደ ጉም አትንኖ ያጠፋዋል። ሐዋርያው እንዲህ ብሎናልና ወደ ምክሩ እንመልከት።
“ለሰው ፡  ሁሉ ፡ ከሚኾነው ፡  በቀር ፡ ምንም ፡  ፈተና ፡ አልደረሰባችሁም፤ ነገር ፡  ግን ፡ ከሚቻላችሁ ፡ መጠን ፡ ይልቅ ፡ ትፈተኑ ፡ ዘንድ ፡ የማይፈቅድ ፡ እግዚአብሔር ፡ የታመነ ነው። ትታገሱም ፡ ዘንድ ፡ እንድትችሉ ፡ ከፈተናው ፡ ጋር ፡ መውጫውን ፡ ደግሞ ፡ ያደርግላችኋል።”
፩ቆሮ ፲ ፡ ፲፫።
አዎ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ እግዚአብሔር የፀጥታ እና የሰላም የነጻነትም መንገድ አለው። ናሆ ፩ ፡ ፫። በእሳት እና በውኃ መካከልም ልዩ መንገድ አለው። መዝ ፷፭ ፡ ፲፪። እኛ የምናምነው ይህን እግዚአብሔርን እንደኾነ ለአፍታ እንኳ አንርሳ።
ለፈተናው ፈተና እንሁንበት እንጅ ልባችን አይደንግጥ። ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ልባችሁ አይታወክ አይፍራም ብሎናልና። ዮሐ ፲፬ ፡ ፳፯። ለፈተናው ሁሉ መውጫ አለው። ፈተናን ድል እንነሳለን እንጅ አይሰለጥንብንም። ምክንያት “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ኹሉን እችላለሁ” እና። ፊል ፬ ፡ ፲፫። ልባችንን በእግዚአብሔር እናበርታ። አንጠራጠር እርሱ መሐሪው አምላክ ከፈተናው ፡ ጋር ፡ መውጫውን ፡ ደግሞ ፡ ያደርጋል።
Filed in: Amharic