>
5:14 pm - Tuesday April 20, 9300

እምነት እንደ ወርቅ የሚፈተነው በመከራ እሳት ነው!!! (መ/ታሪኩ አበራ)

እምነት እንደ ወርቅ የሚፈተነው በመከራ እሳት ነው!!!

መ/ታሪኩ አበራ
ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከዕንቁ የከበረች ነች።†
 
† የራሻ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በከተማና በገጠር በየጎዳናው ጸሎተ ዕጣን በማድረስ አጋንንትን እያስጨነቀች የሕዝቧንም ሥነ ልቡና ከጭንቀትና ከሥጋት እያላቀቀች በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይለ መስቀል በእምነት እያበረታች ነው ።†
እምነት እንደዚህ ነው፤ እንደ ሠለስቱ ደቂቅ የምናመልከው አምላክ ከነደደው ደዌ ያድነናል ባይድነንም እንኳ እምነታችን በእርሱ ላይ የጻነ ነው ብሎ በመከራ ላይ መዝመት ነው፤ እንደ ዳንኤል አምላኬ መልአኩን ልኮ የአጋንንትን ድንፋታ ይዘጋል ብሎ በስሙ ሥልጣን መነሳት ነው፤ እንደ ሙሴ የአባቶቼ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ባህሩን የብስ አድርጎ ሕዝቡን ወደ ተሻለ ለምለም ዘመን ያሻግራል ብሎ የእምነትን በትር መያዝ ነው።የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሁሌም አጋንንትን ድል የምታደርገው በኃይልና በሥልጣን በዲያብሎስ ወረዳ ላይ የክርስቶስን ስም በማስመሰል ሳይሆን በእምነት ስለ ምታውጅ ነው።
እምነት ቀልድና ተራ ነገር አይደለም እንደ ወርቅ በእሳት የሚፈተን የክብር ዘውድ ነው። ሌሎች ቤተእምነቶች  በሰላሙ ጊዜ ተአምራትና ፈውስ እናደርጋለን እያሉ በየአዳራሹ ጤነኛ ሕዝብ ላይ ሲቀልዱና ሲያጭበረብሩ ውለው ያድራሉ እውነተኛው ደዌና እውነተኛ ሕሙማን ሲመጡ ግን እግሬ አውጭኝ ብለው ፈርጥጠው ይጠፋሉ ምክንያቱ አማኞች ሳይሆኑ አስመሳዮች ናቸው።   እምነት በእውነተኛ የመከራ ቀን በችግር ላይ የእምነትን አዋጅ አውጆ በኃይልና በሥልጣን መውጣት ነው። ኃይል የእግዚአብሔር ነው።ድሉም የኦርቶዶክሳውያን ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም  በታላቅ እምነት እግዚአብሔርን እየተማጸነች  በምህላ፣በጸሎተ ዕጣን የአጋንንትን ውጊያ ድል እያደረገች ነው።ክብር ሁሉ በሰማይና በምድር ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን።
ያዕቆብ 5፥14፤ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።
15፤ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።
16፤ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።
17፤ ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥
18፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።
እግዚአብሔር ምድራችንን በልጁ ደም ይፈውሳት።
Filed in: Amharic