>

ለእጅ፣ለአፍና ለእግር የተጻፈ ደብዳቤ (እንዳለጌታ ከበደ)

ለእጅ፣ለአፍና ለእግር የተጻፈ ደብዳቤ

እንዳለጌታ ከበደ
ተዉኝ
ተለመኑኝ!
ከሕይወት ሰፌድ ላይ፣ ሞት አታዘግኑኝ
ተዉ አታነካኩኝ
ከዘመን ደዌ ጋር፣ ጥላ አታለካኩኝ፡፡
እጄ!
ዐይን እጄን ተኳረፍ፣ ለጊዜው ተጣላ
አፍንጫዬን ራቀው፣ ነገር አለው ሁዋላ፡:
ተው አትጨባበጥ
ሰላምታህን ለውጥ
በንክኪ ሆኗል፣ አለም የሚናወጥ
እንጀ እንቧይ የሚፈርጥ!
—–
አፌ!
ትንፋሽህን ጋርደው
ተሰትረኸው ዋል፣፡ ግሎ ከሚበርደው።
እማኝ እንዳትሆን፣ ስወድቀው አጓጓል
ሞት ከቫይረሱ ጋር፣ ሲተሳስር በውል!
—–
እግሬ!
እስኪ መንገዱን ጹመው
ታቀበው
ይህችን ክፉ ቀን፣ ተወጣው በመላ
ምሰሶዬ እንዳይዘም፣ የህይወቴ ባላ።፡
—–
እጄ፣ አፌ፣ እግሬ!!!
ግዴላችሁም ንቁ
‘ያላወቁ አለቁ’ ነውና ተረቱ
‘እያወቁ ማለቅ መጣ በሰአቱ’
ያላወቁ አለቁ
የናቁ ተናቁ፤ ከሞት ተናነቁ።
ያላወቁ አለቁ
እየተቧደኑ
ቅርጫ ስጋ ይመስል፣ ተከፋፍለው ዋሉ
ሕይወትን እያሙ
ዝንጋዔ ለብሰው፣ ቫይረሱን ተሻሙ
ክልል አካለሉ
አየሩን በከሉ
ሞትን ለማቆንጀት፣ ዐይን ዐይኑን ኳኮሉ
እንደተቧደኑ
በዝግታ መንገድ፣ እንደተቃቀፉ
እንቅፋት ጣላቸው፣ ተደነቃቀፉ!
—–
እጄ፣ አፌ፣ እግሬ
ግዴላችሁም ንቁ
ወይዛዝርት ሁሉ
ጎበዛዝት ሁሉ፣
እውቀትን ሰንቀው እስኪረማመዱ
አዋጁን ንገሩ
ለይተው ሊኖሩ
እሳቱን ከአመዱ
እባብ ከገመዱ
ሰናዩን ከእኩዩ
ወንጌላዊ ሁኑ ሙአዚኑን ሁኑ
ሞትን እንዳትዘግኑ!
—-
አጎንብሸው ልዋል፣
ቅዝምዝሙ እስኪያልፍ
ትንፋሽ ላሳጥረው፣
የቫይረሱን ወናፍ
መውጪያ መግቢያ እንዲያጣ፣
ሞት ከደጄ ሲያልፍ
መቸም እንዳልተኛ፣
የዝንጋታን እንቅልፍ!
—-
እጄ፣ አፌ፣ እግሬ!!!1
ማግኔት ሆናችሁ፣ ቫይረሱን አትሳቡት
ኮሮናን አትሳሙት
ኑሮዬን አልሙተው፣ በኮሮና ዝሙት
ከቶም አታትሙት!
ለምነው ማትሰሙ፣ የነፍሴን አበጋር
የምን መጣደፍ ነው፣ ሞትን ለመጋገር
መዝጋት ነው የምሻ፣
የሞት መምጫውን በር!
(መጋቢት 2012)
Filed in: Amharic