>

ኃይልን የመልበሻው ሚስጢር ይህ ነው፡፡ (ዲያቆን ኃይለመለኮት ግርማ  ወንድሙ)

ኃይልን የመልበሻው ሚስጢር ይህ ነው፡፡

 

ዲያቆን ኃይለመለኮት ግርማ  ወንድሙ
አሁን የሞባይል ቻርጅን አስቡ፡፡ የሥልካችን የባትሪ ኃይል በቀነሰ ጊዜ በኤልክትሪክ ሞገድ የደከመውን ባትሪ እንሞላዋለን፡፡ ሲሞላም ከተነሳበት አቅም እየጨመረ ይመጣል፡፡ 1%..2%..9%..17%..28%..42%..66%..80%..93%..ይልና 100% ይላል፡፡ የትኛውም ባትሪ እንደሰካችሁት አይሞላም፡፡ #እንደተሰካ_መተውን ይፈልጋል፡፡ ጊዜ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ መቆየትን ይፈልጋል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እየሰገዱ መቆየት፡፡ እየጸለዩ መቆየት፡፡ ንስሐ እየገቡ መቆየት፡፡ እየቆረቡ መቆየት፡፡ ክፋትን እየተቃወሙ መቆየት፡፡ ቃልኪዳኑን እየጠበቁ መቆየት፡፡ የወደቁትን እያነሱ መቆየት፡፡ የተራቡትን እያበሉ፣ የተጠሙትን እያጠጡ፣ የታረዙትን እያለበሱ መቆየት፡፡ እውነተኛ እየሆኑ መቆየት፡፡  መቆየት እንዴት ያለ ነው?፡፡
በመንፈሳዊውም ዓለም ኃይልን እስክትለብሱ ያለን፤ የኃይል ስጦታ የጸጋውንና የመለኮቱን ሞገድ ስጦታ ነው፡፡ ሞባይል የሚሞላው በኤልክትሪክ አቅም ነው፡፡
ኃይል የሚሞላው ደግሞ በዘወትር አምልኮ ውስጥ በመገኘት ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ የምትሸወዱት እዚህ ላይ ነው፡፡ ‘ቆዩ’ ያለውን ቃል ትዘሉታላችሁ፡፡ የእግዚአብሔርን ጊዜ ዘንግተነዋል፡፡ ነገርን ሁሉ #በጊዜው_ውብ_አድርጎ ሰራው ነው፡፡ የምንሰራው ሁሉ በኛ ጊዜ ይለፍ ካልን ውብ አይሆንም፡፡ በረከት አይኖረውም፡፡ ጸጋ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ አለብን፡፡ መቆየት አለብን፡፡ ስግደትና ቁርባን ኃይልን የሚሞሉ ሞገዶች ናቸው፡፡ ዛሬ ሰግዳችሁ ነገ ስትደግሙበት የሚያድግ ኃይልን ታገኛላችሁ፡፡ 1% ወደ 2% ታድጋላችሁ፡፡
የሞባይሉ ባትሪ ቻርጅ ከተነቀለበት ቅጽበት አንስቶ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ በአንጻሩም መስገድና መቁረብ ስታቆሙ ጸጋችሁና የነፍሳችሁ ኃይል እየቀነሰ ይመጣል፡፡
አባቶቻችን ይህንን የመቆየት ኃይል ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ቃሉን እየጠበቁ ይቆያሉ፡፡ ጸጋቸውን እያከበሩ ይጠብቃሉ፡፡ የእያንዳንዷ ቀን አካሄዳቸውን ከኢየሩሳሌም ውስጥ ያረጉታል፡፡ አምልኮን አያቆሙም፡፡ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃይላቸው እያደገ እያደገ ይመጣል፡፡ ጽድቃቸው መነበብ ይጀምራል፡፡ ክብሩን ይገልጡታል፡፡ ሞገሱ በገጻቸው ይታያል፡፡
ስለዚህ በርቱ፡፡ በጸሎት ቤታችሁ እየበረታችሁ ቆዩ፡፡ ቻርጅ እንድትነቅሉ የሚታገላችሁ ዓለምና ሰይጣን መጨረሻችሁን ስለሚያውቅ ይታገላችኋል፡፡
Filed in: Amharic