አድዋና የህዳር በሽታ….!!!
(በእውቀቱ ስዩም)
* ጀግንነት ማለት የእሳት ራት መሆን አይደለም፤ ጀግንነት ከጠላትህ ጋር መጋፈጥ በሚገባህ ሰአት መጋፈጥ፤ መሸሽ በሚያዋጣህ ሰአት መሸሽ ነው!
—-
በአድዋ ጦርነት ዘመቻ ታውጆ ፤ ሰራዊቱ ወደ ሰሜን ሲዘምት፤ በትውልድ ግብጣዊ፤ በሙያ የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት አቡነ ማቴዎስ ቀሳውስትን መርተው፤ የማርያምን ታቦት አስይዘው ወደ ጦርሜዳ ዘምተዋል፤ ለወታደሮች ወኔና መንፈሳዊ ብርታት ለግሰዋል! እየሸለሉም ባይሆን እየቀደሱ ተመልሰዋል ::
ቆይቶ ቆይቶ…
ዘመን አልፎ ዘመን መጥቶ…
በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት የኮሮና ታላቅ ወንድም የሆነው የህዳር በሽታ፤ ወደ አገራችን ገብቶ ብዙ ህዝብ ፈጀ፤ የእልቂቱ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፤ “ በዘውዲቱ ሬሳ ጎትቱ “ የሚለው ያማርኛ ፈሊጥ ነገሩን ጠቅለል አድርጎ ይገልፀዋል፤
በጊዜው አቡነ ማቴዎስ ሁኔታውን በቅርብ ርቀት ሰለሉት፤ ወረርሽኙ በትንፋሽ እንደሚተላለፍ ባነኑ ፤ አጅሬው ቫይረስ እንጂ ብኤልዘቡብ ወይም ጄኔራል አልበርቶኒ አይደለም:: እና ሊሳፈጡት አልሞከሩም ፤ በቅሎቸውን ኮልኩለው ፤ ወደ መናገሻ ተራራ ስልታዊ ማፈግፈግ አደረጉ ::
በርግጥ በጊዜው መንፈሳዊ ልጆቻቸውን በትነው መሸሻቸው ትክክል ነበር አይደለም የሚለው ሊያከራክር ይችላል ፤ ግን ራስን አድኖ ሌላውን ከማዳን ጥበብ አንፃር ከመዘንነው አቡኑ ያደረጉት ትክክል ይመስለኛል ፤ ቢያንስ ለተጨማሪ አመታት በህይወት እንዲኖሩ አድርጉዋቸዋል፤ ለሌላውም ጠንቅ ከመሆንም ታቅበዋል፤
ጀግንነት ማለት የእሳት ራት መሆን አይደለም፤ ጀግንነት ከጠላትህ ጋር መጋፈጥ በሚገባህ ሰአት መጋፈጥ፤ መሸሽ በሚያዋጣህ ሰአት መሸሽ ነው፤