>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1989

ኮሮና ወ ፖለቲካ ...!!! (ዘሪሁን ብርሀኑ)

ኮሮና ወ ፖለቲካ …!!!

 

 

ዘሪሁን ብርሀኑ
በየቀኑ አስራ ስምንት ሰው ብቻ የመመርመር አቅም ያለት ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እየተዘጋጅች ነው ፡፡ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ቀድመን ልነከላከለው ካልቻልን  በፊት ለፊት ውጊያ ኮሮናን እንደማናሸንፈው ገብቷቸዋል ፡፡ ድንበር ከመዝጋት አንስቶ የመንግስት ስራን እስከማቆም የደረሰው ውሳኔም ለዚህ ማረጋጋጫ ይመስላል ፡፡
ይህ በመገናኛ ብዙሃን የሰማነው መረጃ እንጅ የመንግስት አቅጣጫ አልፋና ኦሜጋ አይደልም ፡፡ ወረሽኙን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል  ሆስፒታልም  የቀብር ስፍራም እንዲዘጋጅ አዟል  ፡፡ነገሩ ከተባባሰ የሚሊኒየም አዳራሽን የጽኑ ህሙማን ማዕከል ለማድረግ ታሰቧል ፡፡ለጣሊያን ያራራው ፅልመት ወዲህ ቢመጣስ በሚልም አብያተ ክርስትያነትና ሌሎች የዕምነት ተቋማት 200 ሺህ የሚሆን የቀብር ስፍራ እንዲዘጋጁ ርብርቡ ተጀምሯል ፡፡ የመንግስት አፈ ቀላጤ ፌስቡከሮች በመጭዎቹ ወራት በሚሊዬን የሚጠጋ ሰው ሊሞት እንደሚችል እየተናገሩ ነው ፡፡
ትንቢቱ የሚያስፈራ ቢሆንም የሚያስወቅስ ግን አይደለም ፡፡ በትልቁ መዘጋጀት የሚያሳጠው ነገር ገንዘብ እንጅ ህይወት ስላልሆነ ፡፡ ጥያቄው በሌለ ገንዘብ ስለሚሞት ገንዘብ እንዴት ይወራል የሚለው ይመስለኛል ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ማምሻውን ተማጽኖ እና ዛቻ ያዘለ መልዕክት ለዓለም አስተላልፈዋል  ፡፡
 አፍሪካ በኮሮና እየታመሰች ሌላው ዓለም እድናለሁ ብሎ እንዳያስብ የሚል ፅሁፍም አስፍረዋል ፡፡
 ንግግሩ ከመሬት ተነስቶ የተባለ አይደለም ፡፡ ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል  ለምታደርገው ጥረት በቂ ድጋፍ እያገኘንች አይደልም ፡፡አሁን ባለው ነባራዊ ሆኔታ ወረሽኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከቁጥጥር ውጭ ቢወጣ  ለማዳን አይደልም የበሽታውን ተጠቂ ለመለየት እንኳን የሚያስችል በቂ የህክማ ቁሳቁስ የለም ፡፡
ከጤና ሚኒስትር ተወክለው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ደረጀ የተባሉ ግለሰብም እንዲህ ያለውን እውነት በአደባባይ አረጋግጠዋል ፡፡ ኢትዮጵያ ኮሮናን መከላከል እንጅ ለትዋጋው አቅም የላትም ፡፡ በዚህ ሁሉ መኻል የመጀሪያው የአሰራ አራት ቀናት የዳሰሳ ጥናት ዛሬ ይታወቃል ፡፡ የሁለቱ ሳምንቱ ትንታኔ ቫይረሱ በአስራ አራት ቀናት ውስጥ  በህመም ደረጃ የሚከስት ነው የሚለውን  ሳይንስዊ መረጃ መነሻ ያደረገ  በመሆኑ የሀገሪቱን እጣ ፋንታ  ይጠቁማል ፡፡
ሪፖርቱ ካለን የመመርመር  አቅም አንፃር ሙሉ  ሀገራዊ ስዕሉን ሊገልፅ ባይችልም ተጨማሪ ጥብቅ እርመጃዎችን ለመውሰድ ግን ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ያደረገ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አለማወጇ  ይረጋገጣል  ፡፡ እዚህ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የዳሰሳ ጥናቱን ሳይመለከት ከባድ ኢኮኖሚያዊ  ጫና የሚፈጥረውን አዋጅ ተጣድፎ  አለማፅደቁ   ሊያስመሰግነው ይገባል  ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለአዋጅ መቻኮሉ ግራ ያጋባል ፡፡የደብረፂዮን ገ/ሚ (ዶ/ር)አስተዳደር ለአዋጅ የሚያበቃ አሁናዊ ትንታኔን ከየት እንዳመጣ  ማንም እርግጠኛ አይመስለኝም ፡፡ የትግራይ ክልል ለአዋጅ መጣደፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን አስተዳደር ስትራቴጅ አልባ ለማስባል ካልሆነ ፋይዳው እምብዛም ነው  ፡፡
ኮሮና የተካረረውን የሀገራችንን ፖለቲካ እንደ ሳሙና አረፋ ድንገት ቢያጠፋውም ቀዝቃዛ ውጥረቶችንና አሰላለፎችን ግን ሊያከስም አልቻለም ፡፡ ለአብነት ያህል የምዕራብ ወለጋ የኢንተርኔት መቋረጥ የማታረቁ የመሰሉትን ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) እና ጃዋር መሐመድ ለሁለተኛ ጊዜ (ወያኔን ማሰወገድ ከሚለው አጀንዳ በመቀጠል )ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ አድርጓል ፡፡
 ይህ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድዳል ፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ ኮሮና ያቀራረባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ከወረሽኑ በኋላ ወደ ቀደመ የለየለት ተቃርኗቻ ይመለሱ ይሆን ? የሚለው  ነው ፡፡ ዝርዝር ነገሩን ትተነው  ምለሹ ግን አይመስለኝም ይሆናል ፡፡ ሌላው ጉዳይ ከመጀመሪያው ሙግት የሚቀጥልና ህዝባዊ አስተሳሰብ የወለደው ነው ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ኮሮና የጦዘውን ብሄርተኝነት እንዳረገበው ይናገራሉ ፡፡በርግጥም ወረሽኙ የዘውጌ ፖለቲካን ከፍ ባለ ደረጃ ተግዳድሯል ፡፡ ይህ ማለት ግን ኮሮና ብሄርተኝነቱን አክስሟል ማለት አይደለም ፡፡
 ወረሽኙ የፖለቲካ ልሂቃኑን የብሄርተኝነት መንገድ ቀየረ እንጅ አለጠፋውም ፡፡ ነገሩን ግልፅ ለማድረግ ልሞክር ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የብሄርተኝነት አረዳድ ቁንፅልና ፖለቲካዊ ብያኔን የተንተራሰ ነው ፡፡ በዚኽ የተነሳም ብሄርተኝነት ሁሉ አንድ ተደርጎ ይወሰዳል ፡፡  እውነታው ግን ከዚህ ፍፁም ይለያል ፡፡
 ብሄርተኝነት በየትኛወም ዓለም ሦስት መልክ ያለው ነው ፡፡ ዘርን ማዕከል ያደረገ፣አካታችንና ሀገራዊ ፡፡ በኢትዮጵያ ኮሮና ከመከሰቱ በፊት የተካረረ ዘር ተኮር ብሄርተኝነት ይስተዋል ነበር ፡፡ ወረሽኙ ሲከሰት ግን የዘር ብሄርተኝነት ለሀገራዊ ብሄርተኝነት ቦታውን ለቀቀ ፡፡በሰሜንም ሆነ በደቡብ ያለ ህዝብ ስንት ኢትዮጵያዊ እንጀ ስንት ሲዳማ፣ወላይታ እና ሀድያ ታመመ አላለም ፡፡
 ይህ የብሄርተኝነት ሽግሽግ በተለያዩ ሀገራት የተስተዋለና መሰረታዊ ልዩነቶችን እንደ ረመጠ አዳፍኖ የሚተው  ነው  ፡፡ የዌልስ ብሄርተኝነት ክፉ ቀን ሲመጣ በታላቋ ብርታኒያ ብሄርተኝነት ደጋግሞ የተረታ ቢመስልም አንቀላፋ እንጅ ለዘላለሙ አላሸለበም ፡፡   ኮሮና በኢትዮጵያ ያለውን  የዘር ብሄርተኝነት እንዲያፈገፍግ ቢያደርገውም አንድ ሌላ እውነትን ግን ለፖለቲካችን አረጋግጧል   ፡፡
እሱም በሀገራችን ያለው ብሄርተኝነት  እውነተኛ የዘር ጉዳይን የተንተራሰ  ሳይሆን   ስነ-ልቦናዊ መሆኑ ነው ፡፡ ነገሩ የቤንዲክት አንደርሰንን የብሄር ትርጓሜ ያስታውሰናል ፡፡ አንደርሰን ብሄር በምናብ ላይ የተመሰረተ ማኅበረሰብ ነው ይላል ፡፡ የዘውጌ አስተሳሰብ መነሻውም የዘር ሀርግ ሳይሆን አጉል  አዕምሯዊ ንቃት መሆኑን ይጠቅሳል ፡፡ ለታዋቂው የስነ-ማኅበረሰብ አጥኝ አጉል አዕምሯዊ ንቃት ቋሚ አይደልም ፡፡ ይልቁኑስ አሁን በኢትዮጵያ እንደሚታየው የህልውና ጥያቄ ሲመጣ እራሱን የሚሸሽግ ፖለካው ሲገዝፍ ከፊት የሚሰለፍ ነው ፡፡
Filed in: Amharic