>

ከላይ ከታዘዘ ቁርጥ ቀን ከመጣ ... (ሸህ ጀማል ሙሃባ ሁሴን - ከወሎ ወረኢሉ)

ከላይ ከታዘዘ ቁርጥ ቀን ከመጣ …

 

ሸህ ጀማል ሙሃባ ሁሴን

ከወሎ ወረኢሉ

 

 

ከላይ ከታዘዘ ቁርጥ ቀን ከመጣ፤

ማምለጫ የለውም እፎቅ ላይ ቢወጣ፡፡

እስቲ ሁላችሁም አላህ አላህ በሉ፤

የመጣብን ዘመን ቀውጢ ነው ይላሉ፤

አሻቅቤ ባየው ሰማዩ ዳመነ፤

ቀወጢ ቀን ይመጣል አላህ ስላዘነ፡፡

ዱኣ ማድረግ ብቻ ነውና ምሕረቱ፤

ሀበሽ ዱኣ ያድርግ በየሃይማኖቱ፡፡

ለይምሰል አይደለም ይህን መናገሬ፤

ለማቃንት ብዬ ነው ሰነፉን ገበሬ፤

መታጠኑ እንዲቀር በሰሜን በርበሬ፡፡

ሁሉ ከይሲ አይደለም ከሰውም ሰው አለው፤

አላህ ግን ያዘነው በሆዳሞቹ ነው፡፡

በደረቅ አበሳ ሲቃጠል እርጥቡ፤

የሰው ልጅ ክፉ ነው ለዚያ አለማሰቡ፡፡

ሚሌኒየም ደርሶ ድግስ ይደገሳል፤

በረሀብ በችግር ሰፊው ሕዝብ ያለቅሳል፡፡

ዘንድሮ አይቀሬ ነው ይመጣል ክፉ ቀን፤

ብዙው ይታጨዳል እንደጓሮ ጎመን፡፡

♦♦♦♦♦♦

ህልምን እየፈራን ሳንተኛ አናድር፤

ክፉ ቀን መምጣቱ ጭራሹን ለማይቀር፡፡

ተሰሜን የመጣ የበርበሬ ንፋስ፤

ሕዝቡን ለበለበው አሳጣው እስትንፋስ፡፡

ክፉ መዥገር ናቸው አገር ይታመሳል፤

በነሱ ምክንያት ስንት ደም ይፈሳል፡፡

እስላም ክርስቲያኑ የጦቢያ ልጆች፤

ጠልዩ እባካችሁ ላገር እንዲመች፡፡

ባንዲራን ሰንደቅን ጨርቅ ነው ያሉት፤

 ስንት ህልቅ እኮ ነው የወደቀላት፡፡

ደንቆሮ ብቻ ነው ይህን የማያውቀው፤

እባክህ አንበሤ ኹዳዱን አሳየው፤

ጀግንነት እንደሆን የ’ናት ያ’ባትህ ነው፡፡

እስቲ ተመልከቱት አያሳዝንም ወይ የጊዜ ነገር፤

በጎጠኞች ምክንያት ስትናጋ አገር፤

ብሔር ክልል ብሎ በማደናገር፡፡

አውሮፓ አሜሪካ የረዱት በርበሬ፤

ለብልቦ ጨረሰኝ ከራሴ እስተ እግሬ፡፡

ብዙ እምለው ነበር በጎም ይሁን ከፉ፤

ሃሳብና ጭንቀት መተከዝ ነው ትርፉ፡፡

እነኚህ መዥገሮች ምነው ምን ነካቸው፤

ተሰሜን ገስግሰው ሸዋ መግባታቸው፤

ወይንስ ትንግርት አለ ቀድሞ ሹክ ያላቸው፡፡

ተናገር አድባሩ ምን ይሆን ጣጣው፤

መስከረም አንድ ቀን የሚደገሰው፤

ወይስ የመጥፊያቸው ሰደቃቸው ነው፡፡

ያሩሲዋ እመቤት እነሼህ ጅብሪል እስቲ መላ በሉ፤

ሃበሽ በያለበት ጠሎት ያድርግ በሉ፤

መርገጫ የታለ እሾህና ቀጋ አጋም ተረብርቧል፤

የማልቀሻው ቀኑ ጨለማው ተቃርቧል፤

ይህን ተናግሬ ሰሚ ሰው ተጠፋ፤

ሀበሽ አለቀለት መጣ ቀን የከፋ፡፡

ተሰሜን የመጣች የጫካ ጠበንጃ፤

ሃበሽን ዘንድሮ ልታጭደው ነው እንጃ፡፡

ያም አለ ያም አለ ያላህ ቃል አንድ ነው፤

ልብን ንጡህ አርጎ መጠለይ ብቻ ነው፡፡

እውጭም ያለኸው አገርም ያለኸው ያበሻው ፍጡር፤

አገርህን ጠብቅ ከዳር እስከዳር፤

ጦቢያን ለማፍረስ ብሎም ለመውረር፤

ስንት መሠሪ አለ ሁሌም የሚጥር፡፡

♦♦♦♦♦♦

ቃሊቲ ታጠረች በሰሜን ጠበንጃ፤

የዛሬው እንዲህ ነው የነገውን እንጃ፤

ይብሰልም አይብሰል ቂጣው ተጋገረ፤

የቃሊቲው በቻ እንዳረረ ቀረ፡፡

በሰፈረው ቁና ሰፋሪው ሲሰፈር፤

እኔን ያሳሰበኝ የቃሊቲው ነገር፡፡

ወረኢሉ ሆኜ የታየኝ መብረቅ፤

በቀላል አይለቅም ሳያደባልቅ፡፡

በመጨረሻ ግን የማታ የማታ፤

ህልቁ ያሸንፋል ክንዱ ተበረታ፤

ህልቁ እንዳይታመስ እንዳይበዛ ጣጣ፤

በገባህበት በር ሹልክ ብለህ ውጣ፤

የኋላ የኋላ ቂምም አያመጣ፡፡ 

ምርጥ ዘር ነን ይላል እንክርዳድ መዥገሩ፤

አያስገርምም ወይ የዐይጥ ምሥክሩ፤

የሚሻለው ደጉ ተቃቅፎ መኖሩ፤

ምን ያደርጋል ከቶ በዘር መፎከሩ፤

የጦቢያ ዝርያ አንድ ነው ባሕሩ፤

የሚበልጠው ደጉ ተሳስቦ መኖሩ፡፡

ጦርነት መጥፎ ነው ህልቅን ይጨርሳል፤

በፍቅር መኖር ግን ለሁሉም ይበጃል፡፡

ይህን መጥፎ ተግባር ስለጠላሁት፤

እቤት ነው ውሎየ እየቃምሁኝ ጫት፡፡

ባደባባይ መጮህ ስለማልፈልግ፤

ጠሓፊው ይጣፈው አስመስሎ ወግ፡፡

♦♦♦♦♦♦

ትግሬ፣አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ከምባታ ማለቱን ትታችሁ፤

አንድ ጦቦያ በሉ ጠልዩ እባካችሁ፡፡

አህያ መጣች ተጭና ኮባ፤

ልትናወጥ ነው አዲስ አበባ፤

ህልቁም ሊወቀጥ ልክ እንደተልባ፡፡

እጅግ አዝናለሁ ይህን ማለቴ፤

ታይቶኝ ነውና ስሙኝ በሞቴ፤

በሬን ዘግቼ ብቻየን ሆኜ ጫቴን ጎርሼ የሚታየኝ፤

እኔን እራሴን አስገረመኝ፤

በይበልጥ ደሞ አስጨነቀኝ፤

ግልጥልጥ ብሎ ስለታየኝ፡፡

ሦስት ዓመት ሙሉ ይፈሳል ደም፤

ተዛ በኋላ ሁሉም ያልፍና አለ ሰላም፤

አገር በልጽጋ ሆና ለምለም፤

ፍቅር ደርጅቶ ለዘላለም፡፡

♦♦♦♦♦♦

ተሰነጣጥቋል የመለስ አልጋ፤

ምንም አልቀረው ወድቆ ሊናጋ፤

የጨለመው ቀን ደርሷል ሊነጋ፤

ህልቅ ሁሉ በርታ ምንም አትስጋ፡፡

ጎጠኛው መዥገር አገር ሲያጠፋ፤

ዘራፊውና ሌባው ሲስፋፋ፤

በርህን ዝጋ ዕቃህን ሸክፍ ሞልቷል ዘረፋ፤

በተለይ ሌባው ሽንጡን ገትሮ ቅሚያ ሊያስፋፋ፡፡

ሁሉም ላገሩ ይሁን ዘበኛ፤

ከሌባውና ካለው ቀማኛ፤

እህልም ሸክፍ የምትበላው፤

ይኼው ብቻ ነው ያለው መላው፤

ተናገር ብሎኝ ተናግሬያሁ፤

ተዚህ የበለጥ ምንስ እላለሁ?

አላህ ያለኝን ተናገርኩ እንጅ፤

ሁሉን ብናገር ለሰሚ አይበጅ፤

እምለው ነበር በጎ ከክፉ፤

እስቲ ልተወው እንዳትከፉ፤

ኋላ እንዳታዝኑ ነው ይህንም ማለቴ፤

ፍርድ ተራሴ ነው አለቀ መልክቴ፡፡

♦♦♦♦♦♦

ይህ ጽሑፍ እጄ የገባው ከዛሬ 15 ወይም 16 ዓመት በፊት ገደማ በአንድ የግል ፕሬስ ውስጥ እሠራ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በያኔው የፖለቲካ ትኩሳትና የከረረ ወያኔያዊ አገዛዝ ይህን ጽሑፍ ማውጣት ራስን ጭዳ ማድረግ ነበር፡፡ አንድ ቦታ ሸጉጬው ኖሮ በቅርቡ አንድ  ሌላ ነገር እየፈለግሁ ሳለ አገኘሁት፤ እፈልገው ስለነበር ሳገኘው ደስ አለኝ፡፡ ካገኘሁትም በኋላ ከነገ ዛሬ ለንባብ አበቃዋለሁ ስል አንድ ወር ያህል ዘገየሁ፡፡ አሁን እንደምንም ብዬ ስንፍናየን ሰብሬ እንዳለ ገለበጥኩትና ላክሁት፡፡ የተመቸው ያውጣው፤ ያልተመቸው በልቶ ወደማይጠረቃ ቅርጫቱ ይጣለው፡፡ 

እኔ ግን “ይነጋል በላቸው” መሆኔን ልናገርና ልሰናበት፡፡ ቻው፡፡ ለማንኛውም አስተያየት – yinegal3@gmail.com

በነገራችን ላይ  የሦስቲትን ዓመት መከራና ስቃይ ግን እያንዳንድሽ እንዳትረሽ! አሁን በቅጡ ጀምራለችና፡፡ ኮሮና ምናምንን ተያት፡፡ እርሷ ለሁሉም ዓለም የመጣች ዱብ ዱብ መባያ – የመጨረሻውን ለመጀመር ማሟሟቂያ ነገር ናት፤ ዱሮውንስ ህግ ጸድቆለት ሰውና እንስሳ በካህናት ቡራኬ እየተጋባ ምንጠራ ሊቀር ኖሯል!  ገና ምን ታየና! ከእንግዲህ ዘመኑ አዝመራን የመሰብሰቢያ ወቅት ነው፡፡ ታላቁ ገበሬ ሽልሸላውን ተያይዞታል፡፡ መሸልሸል ማለት አንድን ማሣ ለጥሩ ዘር ዝግጁ ማድረጊያ አንዱ ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ መሆኑን ታዲያ ልብ ይሏል፡፡ እርሻ ላይ የበቀለው አዝመራ አበቃቀሉ ሳያምር ሲቀርና የሚፈለገውን ምርት ሳይሰጥ ቀጭጮ እንደሚቀር ገበሬው ሲገምት ቡቃያው ላይ ወይም ከፍ ብሎ የሚታየው ሰብል ላይ በሬ ጠምዶ ይሸለሽለዋል – በዘራው ዘር መባከን ጭክን ብሎ! ከዚያም እንደፍጥርጥሩ የወጣው ይወጣል፤ የወደቀውም ለወጣው እንደማዳበሪያ ይሆናል፡፡ ይሄው ነው፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ እናም እየተሸለሸልን ነው ማለት ነው እኛም፡፡ ይህ እንዳይገባን ግን ሌላኛው ኃይል አንዳች ነገር ያዞረብን ይመስላል፡፡ ሰው ሆነን እንደሰው እንዳንኖርም ጭምር፡፡

Filed in: Amharic