>

እምነትና ጥንቃቄ..!!! (ዳንኤል ክብረት)

እምነትና ጥንቃቄ..!!!

ዳንኤል ክብረት
በክርስቲያኖች ላይ ሁለት ዓይነት መከራ ይደርሳል። በእምነት ምክንያት የሚመጣና በሰውነት ምክንያት የሚመጣ። ሃይማኖት እንድንቀይር ምግባር እንድንተው የሚመጣ መከራ አለ። ይህ በክርስቲያኖች ላይ ተለይቶ የሚመጣ ነው። ለዚህ መልሱ ሰማዕትነት ነው።
በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ የሚመጣ መከራ አለ። ይህ በሰው ልጅ ሁሉ ላይ የሚመጣ ነው። ለዚህ መልሱ መንፈሳዊ ዕሴትና ጥንቃቄ ነው።
አሁን ከኮሮና ጋር ተያይዞ የመጣው መከራ ሁለተኛው ነው። ስለዚህም መፍትሔው መንፈሳዊ ዕሴትና ጥንቃቄ ነው።
ከ70 ዓም ቀደም ብሎ ኢየሩሳሌም ከባድ መከራ እንደመጣባት ክርስቲያኖች ተረዱ። ስለዚህም ከተማዋን ለቅቀው ፔላ ወደምትባል (ዛሬ ሊባኖስ ውስጥ ናት) ከተማ ሸሹ። በ70 ዓ/ም ከመጣው የኢየሩሳሌም ጥፋትም ተረፉ። ይህ ጥንቃቄ ነው። ገዳመ ደብረ ሊባኖስ ከጥፋት የተረፈው በንጉሥ ሱስንዮስ ጊዜ መጀመሪያ ወደ እንፍራንዝ በኋላም ወደ አዞዞ ሄዶ ነው።
እምነትና ጥንቃቄ የሚግባቡ እንጂ የሚወዛገቡ አይደሉም። የምንወስደው የጥንቃቄ ርምጃ እምነትን የሚያጠፋ መሆን የለበትም።  የምንከተለው እምነትም ዕውቀት ሊጎድለው አይገባም ።  መጠንቀቅ ካለ ማመን መድፈርም ከማመን አይቆጠርም።   ምን ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ንጽሕና እንድንጠብቅ ታዘናል። እንድንታጠብና ንጹሕ ልብስ እንድንለብስ። አሁን የምንታጠብበት መጠንና አስተጣጠብ፣ ብቻ ነው የተለየው።
አንድ ሰው ስለበሽታ ጥንቃቄ የሚያደርገው ለራሱ ብቻ አይደለም። ለወንድሙ ጭምር ነው። ወንድሜ የኔ ዓይነት የእምነት ጽናት ሊኖረው ይገባል አይባልም። ለእኛ ማመን ለሌሎች ደግሞ መጠንቀቅ ይገባል።   ተራርቀን መቆም፣ ርቀታችንን መጠበቅ፣ የምንሳለማቸውንና የምንነካቸውን ገሮች በመመሪያው መሠረት በጥንቃቄ መያዝ፤ የማንጠነቀቅ ከሆነ ለጊዜው ማቆም፣ በብዛት ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከመግባት በዐዉደ ምሕረት ማስቀደስ። ደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጨምሮ ደብረ ነጎድጎድና የሰሜን ገዳማት በወረርሽኝ የተነሣ መነኮሳቱ አልቀው ተዘግተው ያውቃሉ። እምነታቸው ከኛ አንሶ ግን አልነበረም።
 ሐኪሞች የሚሰጡትን ምክር መጠቀም፣ ሥርዓታችንን ጥንቃቄ  በታከለበት መንገድ መፈጸም ለሕዝባችን መራራት ነው። የሚጠነቀቁትን በእምነት አልባነት መፈረጅ ፈራጅነት እንጂ አማኝነት አይደለም።  የማይበላ የሚበላውን አይናቅ፣ የሚበላም በማይበላው ላይ አይፍረድ እንደተባለ። በተለይ ሰባክያን የምንናገረው ነገር ሕዝብን ከእምነት አውርዶ ሞኝነት፤ ከእምነት አውጥቶ ድፍረት የሚከት እንዳይሆን እንጠንቀቅ።
Filed in: Amharic