>

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ 

 

አሜን

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እና መስፋፋትን ለመግታት በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሰጠ ማብራሪያ።
በመላው ዓለም ለምትገኙ ወገኖቻችን በሙሉ!
የወቅቱ የዓለማችን ሥጋት በመሆን በፍጥነት እየተስፋፋ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ ሀገሮች ብሔራዊ ሥጋት ስላደረባቸው እርምጃዎችን በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡
በሽታውን እንዳይዛመት ከመከላከል ውጭ የሚፈውስ መድኀኒት ስለሌለው፣ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ስለሚዛመት፣ ጾታና የዕድሜ ክልል ሳይለይ ይልቁን አረጋውያንን ስለሚያጠቃ፣ ሁሉም ሀገሮች የመተላለፊያ መንገዶች በመለየት ሥርጭቱን ለመግታት ዝርዝር መግለጫ በማውጣት ሕዝባቸው ከሞት፣ ሀገራቸውን ከጥፋት ለመከላከል እየጣሩ ይገኛሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጸሎትና ምሕላ አጠናክሮ ከማድረግ በተጨማሪ ጤነኞችን የመጠበቅ፣ ሕሙማን የመንከባከብና የማጽናናት ኃላፊነት ስላለባት ቋሚ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡-
1. ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጀምሮ በየደረጃው የሚዋቀር ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከጤና ባለሙያዎች የተውጣጣ ግብር ኃይል ተቋቁሟል፤
2. ግብረ ኃይሉ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር አስፈላጊ መረጃዎችን በማሰናዳት በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣
3. ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጋር የማይጋጩ የመከላከያ መንገዶች ማለትም የእጅ ለእጅ መጨባበጥን ማቆም፣ እጅን በሚገባ መታጠብ፣ ሳይጠጋጉ ዘርዘር ብሎ መቆም፣ በመሳልና በማስነጠስ ጊዜ መጠንቀቅ፣ በመሳሳም ምትክ እማሄ ወይም ሰላምታ መስጠት በየአጥቢያው፣ በየገዳማቱና በያለንበት ሁሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ፤
4. መንፈሣዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት፣ የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብሮች ለጥቂት ቀናት እንዲቆሙ፣ በቅዳሴና በምሕላ ጸሎት ጊዜ በውስጥም ሆነ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዘርዘር ብሎ በመቆም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እንዲፈጸሙ፣
5. ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ከተሳሳቱ መረጃዎች ተቆጥባችሁ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድታስፈጽሙ፣
6. ለራሳችንና ለወገኖቻችን በመቆርቆርና በመተዛዘን፣ አረጋውያንን በመጠበቅ፣ ነዳያን በማሰብ የበሽታውን ሥርጭት ተባብረን እንድናስቆም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ይኽንን አስከፊ በሽታ ከዓለማችን እንዲያጠፋልን በማያልቅ ቸርነቱና በቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም አማላጅነት በምኅረቱና በይቅርታው ብዛት ይማረን፡፡
አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
Filed in: Amharic