>

ለመጣብን መአት ተመጣጣኝ የሆነ ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል!!! (ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

ለመጣብን መአት ተመጣጣኝ የሆነ ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል!!!

(ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት እና አጠቃላይ አስተምህሮ «ካህን መር» (Clergy Led) ነው። በሌላው ዓለም በተለይም በፕሮቴስታንቱ ዓለም ትምህርተ ሃይማኖቱ «ምእመን መር» ነው። አማኙ በድምጽ ብልጫ የሚወስናቸው አስተምህሮዎች የትምህርተ ሃይማኖቱ አካል መሆን ይችላሉ (ግብረ ሰዶም እና የሴቶች ክህነትን ይመለከቷል)።
ይሁን እንጂ አሁን አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በምእመኑ አስተሳሰብ እና አመለካከት ተጽዕኖ ውስጥ ወደመውደቅ እየሄደች ይመስላል። ካህናቱ (እስከ ቅ/ሲኖዶሱ ድረስ) ወሳኞች ሆነው ምእመኑን ከመምራት ይልቅ ምእመኑ በብዙ ነገር እየቀደመ በመምራት ላይ ይገኛል። የዚህ መጨረሻው ደግሞ ጥሩ ሊሆን አይችልም። አረረም መረረም በአባቶች የምትመራ ቤተ ክርስቲያን እስካልሆነች ድረስ «ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን» ልትሆን አትችልም።
ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ ለምሳሌ አሁን ባለው የዘመነ ኮሮና ውዥንብር ውስጥ እንኳን አበው ከፊት ሆነው ምእመኑ ማድረግ ያለበትን እና የሌለበትን በማሳየትና በመወሰን በኩል ቅድሚያውን ሲወስዱ አንመለከትም። በዚህ ረገድ በውጪው ዓለም ያሉ አባቶች ከየሀገሮቹ ሕግጋት ጋር የሚጣጣም ውሳኔ በመወሰን ለመምራት መሞከራቸው በአያሌው ያስመሰግናቸዋል።
በሀገር ቤትስ? ይህ የመጣው በሽታ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ (ይሰውረን) ዋነኛ ተጠቂ ሊሆኑ ስለሚችሉት የቤተ ክርስቲያናችን ስሱ አባላት ምን አስቧል? የዛሬ 100 ዓመት ተስቶ የነበረው የሕዳር በሽታ ብዙ ሊቃውንትን፣ የአብነት ት/ቤት ተማሪዎችን እና ምእመናንን ጠርጎ እንዳልጨረሰብን አሁንም ያንን ረስተን ሌላ ጥፋት እንዳይደርስብን አለመዘጋጀታችን ምን ይባላል? ከዚህ በሽታ በርቀት ላይ ያሉ ገዳማት ስለ በሽታው መምጣት እንኳን ሳይሰሙ ከከተማ አካባቢዎች በብዛት በምንጓዝ ምእመናን አማካይነት በሽታውን ልናደርሳቸው እንደምንችል አስበን፣ ለእነርሱ አዝነን ሌላ ውሳኔ ያልወሰንነው ለምንድር ነው? ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ የነገረ መለኮት ሊቃውንት፣ ማኅበራት እና ስለ ቤተ ክርስቲያን ይገደናል የሚሉ አካላት ራሳቸውን እና ሌላውን ሕዝብ ከዚህ መቅሰፍት ለመጠበቅ እያደረጉ ያለው ተግባራዊ ርምጃ ምንድር ነው?
አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን በአባቶች መንፈሳዊ እና ዘመኑን የዋጀ አመራር ወደ መመራት ትመለስ። ማንም ደስ እንዳለው የሚመራቸው ምእመናን እንዲኖሩን አንፍቀድ። ስለኮሮና አስቸኳይ ጉባኤ እና አስቸኳይ ውሳኔ ይተላለፍ።
እግዚአብሔር ከዚህ ከመጣብን መአት ይሰውረን። አሜን።
Filed in: Amharic