>
5:13 pm - Saturday April 19, 9045

እንደ “የሕዳር በሽታ”፥ “ኮቪድ-19” ያሉ ድንበር ዘለል ወረርሽኞች ገዳይ በሽታዎች እንደሆኑ እመን እንጂ አትጠራጠር!!! (መሰለ ተሬቻ)

እንደ “የሕዳር በሽታ”፥ “ኮቪድ-19” ያሉ ድንበር ዘለል ወረርሽኞች ገዳይ በሽታዎች እንደሆኑ እመን እንጂ አትጠራጠር!!!

 

መሰለ ተሬቻ፥
የሕዳር በሽታ የካቲት 1910 ዓ.ም በUSA ካንሳስ ሐገረ ግዛት ተከስቶ፣ በመጋቢት አጋማሽ ላይ አዲሰ አባባ ብቅ አለ። አገባቡም በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ነው። ይኸውም ደዌ የኢትዮጵያን ኀገረ-ሰብ ሲተዋወቅ እንደው እንደ ዘበት ተራ ጉንፍን መስሎ እያዘናጋ ነበር። የኢትዮጵያም ሰው ክፉ ድንበር ተሸጋሪ ደዌ እየገባው እንደ ሆነ ሳይታወቀው ብቻ እያነጣጠሰ ትኩሳትም ሽው እያለው ለአምስት ወራት ሰነበተ። ይኸውም አኳኳን ዛሬ ኮቪድ-19 ከተባለው ደዌ አገባብ ጋር ፍጹም ተመሳሳይነት እንዳለውና ላለፉት ወራት ስታነጣጥስ እንደከረምክ ልብ ካለህ ልብ እልያልክ። በዚህ ግዜ በሌላው ዓለም ደዌው እያስከተለ የነበረው ጥፋትም ፍነጩ ከኀገረ-ስብ ኢትዮጵያ ጆሮ ዝር ሳይል ሰነበተ። ነሐሴ ላይ ደርሶ ግን በሽታው መልሶ አገርሽቶ ከመክፋትም የመጀመሪያውን ሰው አዲስ አበባ ላይ ገደለ። ይኸውም ሟች የ24 ዓመቱ ግሪካዊ ስታማቲዎስ ግሐኖታኪስ ነው። ዛሬ በዚህ የኮሮና የጥፋት አፋፍ ላይ ሆነን የስታመተዎስን ነፍስ ይማር በማለት እናስባለን። በነሐሴ ደዌው ናኝቶ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩትን አርመኖች፣ አረቦች፣ ሕንዶች፣ ግሪኮች … ወዘተ በሞት ያራግፍ ገባ። ይህም ሲሆን ዛሬ ጎሮቤቱ የሆነውን የውጭ ዜጋ ገድሎ ሲጨርስ ወደ እርሱ እንደ ሚዛመት ያልገባው የኢትዮጵያ ሰው ከመጠንቀቅ ይልቅ ይዛበት ነበር። ደዌውንም “የፈረንጅ ጉንፋን” ሲል እያቃለለ ተሳለቀበት።
በነሐሴ ማብቂያ ላይ የደዌው ይዞታ ወደ ኢትዮጵያ ሰው ዘልቆ ገባና ይጥለው ያዘ። ነሐሴ 21 ቤተ መንግስት ዘው ብሎ አልጋ ወራሽ ተፈሪን ከመልከፍም በ2 ሳምንታት ግዜ ውስጥ የአልጋ ወራሹን ሊባኖሳዊ የግል ሐኪም፥ ዶ/ር አሳድ ቻይባንን፥ ገድሎ አልጋ ወራሹንም ከሞት አፋፍ አድርሶ፥ የኢትዮጵያን ሰው በፍርሃት አስቃተተው። ጥቅምት አጋማሽ ላይ ሌላ የገዳይነት አቅሙን ያደረጀ “የሕዳር በሽታ” ዓዲስ ዓይነት መስሎ ሲገሰግስ በኤደን የጅቡቲን ሐዲድ ተከትሎ አዲስ አበባ ገባና ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሐገሩን የሞት ዶፍ አወረደበት። ይህ ደዌ በሐገሩ ከነበሩት ስምንት ሐኪሞች ሰባቱን ገድሎ የኢትዮጵያን ሰው መጠጊያ አሳጣው። የሚያደርገው ቢያጣ ጉልበት ያለው ከከተማው እየሸሸ በዙሪያው ተራሮች እየወጣ ይሰፍር ያዘ። መጀመሪያ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቶዎስ ወደ መነገሻ ወጨጫ ሸሽተው ሄዱ። ከዛ ራስ ከሳ ሐይሉ ዳርጌ ብሞትም በሀገሬ ይሻላል ብለው ወደ ሰላሌ ሸሹ። ከዚያ ሁሉም በያአቅጣጫው ከከተማው እግሬ አውጪኝ አለ። ንገስተ ነገስታት ዘውዲቱም ከከተማው ሽሽት ቢያስቡ ያልጠናው መንግስት ሊፈርስ ሆነና የግድ እንዲቀመጡ ተደረገ። ንግስቲቱም ጣረ ሞት ሰልጥኖባቸው አይከርሙ አከራረም ከረሙ። ግን ቤተ መንገስቱ ተዘግቶ ሰው ከውስጥም እንዳይ ወጣ ወደ ውስጥም እንዳገባ ጥብቅ እግድ ተደረገበት። ከከተማ የመሸሽና ወደ ተራራ ፈልሶ የመውጣት ብልሃት ለነባሮቹ የተስቦና የፈንጣጣ ወረርሽኞች ሲሰራለት ቢኖር አሁን ግን “ከሕዳር በሽታ” የኢትዮጵያን ሰው ያማያስጥለው ሆነ። ነጭ ሽንኩርቱ፣ ዝንጅብሉ፣ አረቄው፣ ጠበሉ፣ ፌጦው፣ የባህር ዛፍ ቅጠሉ፣ የወይራ ዕጣኑ… ሁሉም አልሰራለት እያለ ደዌው በየደረሰበት እንደ ዝንብ እያራገፈ ገደለው። ከሕናቱም በስውር አፄ ዘርዓ ያቆብን ይረግሙ ያዙ። ለወትሮው እንዲህ ያለ የወረርሽኝ ደዌ መቅሰፍት ሲወርድ በቤተ ክርስቲያን “መፅሐፈ አስማት” ይደገም ነበር። ታዲያ ይህ ንጉስ መረገሙ መፅሐፉ የጥንቆላ ነው በሚል ስለ ማቃጠሉ ነበር።
በነገራችን ላይ የሕዳር ሚካኤል በጢስ የመታጠን ነገር በዚህ ግዜ ተጀመረ የሚባለው አባባልም የተሳሳተ ነው። ሕዳር ሚካኤል ከዚያ ግዜ ሃምሳና ስልሳ ዓመታት በፊትም በሸዋ ይታጠን ነበር። የሚታጠነውም የጥቁር ጤፍ ምርት መድረስን ተንተሶ ስለ አዲስ ምርት የመድረሱ  ብስራት ማብሰሪያ ነው። አንባቢ ሆይ እንደ “የሕዳር በሽታ”፥ “ኮቪድ-19” ያሉ ድንበር ዘለል ወረርሽኞች ተራ መዘበቻ እንዳልሆኑ እመን እንጂ አትጠራጠር። አሁን ከዚህ በላይ የፃፍኩልህ እና አዲስ አበባ ላይ ብቻ ከአምስት አንድ እጁን ሕዝብ ገድሎ እንዳለፈ የሚታመነው የሕዳር በሽታ እንደው የፈጠራ ድርሰት እንዳልሆነ ለማየት እንድትችል በግዜው በስፈራው የነበሩት አለቃ ክንፌ አዲሱ “መፅሐፈ ነገስታት” በሚል ርዕስ አዘጋጅተው ሳይታተም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ላይብረሪ በሚገኘው ድርሳናቸው ስለ “የሕዳር በሽታ” እና የኢትዮጵያ ሰው አኳኳን የፃፉትን በቀጥታ ጠቀሼ ላስነብብህ፤
“… ይህንንም ሕመም መጀመሪያ ቀን እንደ ዘመድ እንግዳ እየሳቁ ተቀበሉት … በየቤታቸው ሆነው ሕመሙ መጀመሪያ ቀን ብዙ የሰከሩ ሰዎች ለመደጋገፍ ይያያዙና ሲሄዱ መንገዱ በዚህ ነው አይደለም በማለት ሲጓተቱ አንዱ ሲወድቅ ሁሉም ባንድነት ይወድቁና እንደሚስቁ በጎረቤት ያሉ ሰዎች ቢጠያየቁ ሁሉም አንድ ቀን ወደቁ … ። በዚህ ግዜ ከሚቀረው ወደ መቃብር የሚሄደው ይበልጣል። የቆመውም ሰው እንደ ተተኮሰበት አውሬ በፍርሃት ይንቀጠቀጥ ነበር። ዛሬ የታየው ነገ አይገኝም፤ የዕለት ሞት ይሞታል። በጦርነት ላይ የወንድሙን ሬሳ እየረገጠ እንደሚሄድ ከመንገድም ወድቆ ሲያዩት እንቅበር የሚል የለም እየረገጡት ያልፋሉ። … ዛሬ ግን በገዛ ሐገራቸው ሁሉም መሻዳሪ ሆኑና እርስ በርሳቸው መቀባበር አልሆንላቸው ብሎ በዳሪ እየወደቁ ሬሳቸውን ቀን ውሻና አሞራ ሌት ጅብ በላው። በዚህም ግዜ ዳኝነት አልነበረም። ስራው ሞትና መታመም ብቻ ነበር። ወደ ቤተ መንግስትም ከግቢው አይወጣ ከውጪም አይገባ ክልክል ነው። …” (አለቃ ክንፌ አዲሱ፤ “መፅሐፈ ነገስታት” ገጾች፥ 69-73)።
አንባቢ ሆይ “የይመናሹን ጠባሳ ያየ በጋለ ብረት አይቀልድም” በዘገይም ትምህርት ቢሆንህ ብዬ ይህን “የሕዳር በሽታ” ታሪክ  አጋራሁህ። እንኔ አያገኘኝም የሚባል ዳተኝነት አያቂልህ። “የሕደር በሽታ” የማህበረ-ባህል አስተምህሮ በልዩልዩ ምክንያቶች ተወራርዶ ባይደርስህ ነጭ ሽንኩርት፣ ፌጦ፣ ዝንጅብል፣ ካቲካላ … ወዘተ አለልኝ እያልክ እራስህን መሸንገል ይቅርብህ። በተቻለህ መጠን ከጋርዮሽ ቦታ እራስህን አርቅ ስለዚህም ይሉኝታ አይግዛህ። አካልህን በቂ ዕረፍት፣ የረጋ መንፈስ አታሳጣው። በየ መገናኛ ብዙሃኑ የሚነገርህን መመሪያ እንደ ዘበት አትየው።
መጋቢት 8፥ 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ።
Filed in: Amharic