>

"የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ያኮላሸ ጥቁር ታሪክ!!!" (መኳንንት ፋንታሁን)

“የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ያኮላሸ ጥቁር ታሪክ!!!”

 

መኳንንት ፋንታሁን
ከጎጃም ክፍለ ሃገር መተከል አውራጃ የበቀለው ሃምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ የከተበውን “አይ ምጽዋ” የተሰኘውን መጽሐፍ በእንባ ታጅቤ አነበብሁት፡፡ ሲቃ ተናነቀኝ ሆድ ባሰኝ የሰው ልጅ ጭካኔ ውስጤ ድረስ ዘልቆ ገባኝ፡፡የምጽዋ ጦርነት በወንድማማቾች መካከል የተካሄደ መራር ጦርነት ነበር፡፡ ቀይ ባህርን በደም ያጠላ ምጽዋን በአስከሬን የሸፈነ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት እንደ ግዑዝ ነገር በየመንገዱ የተበተነበት ዘግናኝ ታሪክ እውነትም አይ ምጽዋ ያሰኛል፡፡ ከ17ሺ በላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት አስር ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያለቀበት ቁጥሩ የማይታወቅ ኤርትራዊ ወንድም የወደቀበት አሳዛኝ ክስተት።የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ያኮላሸ ጥቁር ታሪክ፡፡
ከጥር 30 ቀን እስከ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ድረስ ለ10 ተከታታይ ቀናት የቀይ ባህር አዉራጃ ወደባዊት ከተማ ምጽዋን ለመቆጣጠር በኢትዮጵያው አብዮታዊ ሰራዊትና በሻብዕያ ተዋጊዎች መካከል የተካሄደዉ ታሪካዊ ፍልሚያ በ10 ቀኑ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ዋና ተሳታፊ በነበረዉ ግን ታሪኩ ለሁላችን ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር በኪነጥበቡ ባተረፈው በሃምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ በሚገርም አቀራረብ ተጽፋል።
ጥር 30ቀን 1982 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ምጽዋ ሰላማዊ እንቅልፏን መለጠጥ ጀምራለች፡፡ በከተማው የሚገኙ የአብዮታዊ ሰራዊት አባላትም ሀገር አማን ብለው ሌሊቱን በጸጥታ እያሳለፉ ነው፡፡ የስድስተኛው ክፍለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል ተሾመ ተሰማ ግን ሁኔታው ከብዶአቸዋል፡፡ ከምጽዋ በስተሰሜን ባለው የሸኢብ ግንባር ሻዕቢያ አዘናግቶ ጥቃት ይከፍት ይሆናል እያሉ ዘወትር ይሰጉ ነበር፡፡ ታዲያ በዚያች ደረቅ ሌሊት የፈሩት ነገር ደረሰ፡፡ ሻዕቢያ እጅግ ጠንካራ የሆኑ ተዋጊዎችን አሰልፎ በሸዒብ ከተማ የነበረውን የ6ኛ ክፍለ ጦር ቀዳሚ መምሪያ እንደወረረ በሬድዮ መልዕክት መጣላቸው፡፡ ወዲያውኑ ወደ ማዘዣ ጣቢያቸው ሄደው ከግንባሩ አዛዥ ጋር ግንኙነት ፈጠሩ፡፡ ያለውን ሁኔታ ከተረዱ በኋላ ረዳት ሀይል እስከሚላክላቸው ድረስ ጠንክረው እንዲዋጉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከዚያ በመቀጠልም አስመራ ለሚገኙት የ606ኛው ኮር አዛዥ ለብ/ጄ/ጥላሁን ክፍሌ ስልክ ደወሉ፡፡ ሆኖም ጄኔራሉን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ በርሳቸው ፈንታም ለሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ ለነበሩት ለሜ/ጄ/ ሑሴን አሕመድ በመደወል ሁኔታውን አስታወቁ፡፡ ጄኔራል ሑሴንም ረዳት ጦር እስከሚላክላቸው ድረስ ባለው ሀይል ሁኔታውን ለመቆጣጠር እንዲሞክሩ ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡
ጀኔራል ተሾመ በዚያች ቅጽበት በምጽዋ ዙሪያ የነበሩት የብርጌድ አዛዦች ጦራቸውን ለጠዋት እንዲያዘጋጁ ነገራቸው፡፡ ንጋት ላይም ከረዳቶቻቸው ጋር ወደ ውጊያው ቦታ ተንቀሳቀሱ፡፡ ሆኖም ያዩት ነገር ከጠበቁት ውጪ ሆነባቸው፡፡ ሻዕቢያ የሰለሞናን ግንባር ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በአካባቢው በነበሩት ተዋጊ ብርጌዶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ተረዱ፡፡ የሰራዊቱ ብርጌዶችም ከሰለሞና በማፈግፈግ በምጽዋ-አስመራ መንገድ ላይ ወደምትገኘው ጋህተላይ እያፈገፈገ እንደሆነ ለማወቅ ቻሉ፡፡ጄኔራል ተሾመ ባደረጉት ወታደራዊ ቅኝት የሻዕቢያ ግብ የምጽዋ-አስመራን መንገድ መቁረጥ ሊሆን እንደሚችል ገመቱ፡፡ ስለዚህ ሻዕቢያን በዚህ መስመር ገትረው ለመያዝ ወሰኑ፡፡ በአካባቢውም ከአራት ብርጌድ ያላነሰ እግረኛ ሰራዊት አስቀመጡ፡፡ ሆኖም የሻዕቢያን የግስጋሴ ፍጥነት ለመቆጣጠር ሳይቻል ቀረ፡፡ ከእኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ቀኑ 10፡00 ድረስ ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ሻዕቢያ “ጋህተላይ”ን ተቆጣጠረ፡፡ የአስመራ-ምጽዋ መንገድም በእጁ ወደቀ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊትም ለሁለት ተቆረጠ፡፡…….. እንዲህና እንዲህ እያለ መጽሐፉ ይቀጥላል፡፡
መጽሐፉ በጦርነቱ ዉስጥ ታላቅ ጀብዱ ስለፈጸሙ በርካታ ጀግኖች ያወሳል። በተለይም በሻዕቢያ በተከበቡ ሰዓት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው ጀግና ቢሞት ጀግና ይተካል ታሪክ ይናገር እንጅ ስለ እኔ ብዙ አልናገርም በማለት ወደ ምጽዋ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን ዙረው ካማተቡ በኋላ የክላሽንኮብ ጠመንጃ አፈሙዛቸውን ጎርሰው ስላሸለቡት ሣልሳዊ ቴዎድሮስ የ3ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዝ ጀግናው ኮሌኔል በላይ አስጨናቂ በስፋት ያትታል፡፡ እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስን እድል በማግኘቴ በጣም እኮራለሁ ሻዕቢያ ግን ሬሳዬን እንኳን ሊያገኘው አይገባም በማለት አስከሬናቸውን ለቀይ ባህር አሳ ስለገበሩት የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ስለሆኑት  ጀግና ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማም ብዙ ይነግረናል፡፡
ለሻዕቢያ እጅ በመስጠት በርካታ ወታደራዊ ምስጢሮችን ስላባከኑትና የወታደሩን ስነ ልቦና ስለገደሉት የ606ኛው ኮር ዋና አዛዥ ስለነበሩት ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ እና የ3ኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ስለነበሩት ብ/ጄኔራል ዓሊ ሐጂ አብዱላሂም የሚለን ነገር አለ፡፡
ሰው በላው የደርግ ስርዓት ስሜታዊና ግልፍተኛ በሆነው የፖለቲካ አስተሳሰቡ ተመርቶ የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ምቱን መፈንቅለ መንግስት አሳቦ እንደ ጀኔራል ደምሴ ቡልቶና ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ አይነት ጀግኖችን ለሞት ዳረጋቸው አገሪቱንም ቀበራት፡፡ወደ ማንወጣው አዘቅት ከተተን ለዉሻ አስረክቦን የሻዕቢያ መጫዎቻ አድርጎን ጠፋ፡፡
አንድ ወቅት ላይ የመጽሐፉ ደራሲ ሃምሳ አለቃ ታደሰ ስለ ምርኮ ሕይወቱ ቃለ መጠይቅ በተደረገለት ወቅት እንዲህ ነበር ያለው፡፡ ምርኮኛ ከሆነው ሰራዊት ውስጥ አማራ ከተገኘ ፋይል የሚደረገውም ለብቻው ነው በጣም ከባድ ስራዎችንም ያሰሩት ነበር፡፡ የኦነጉ መሪ ሌንጮ ለታ እና የሕወሐት ሰዎች በየወቅቱ እየመጡ ምርኮኛውን ያነጋግሩ እንደነበርና ኦሮሞውን ወደ ኦነግ ትግሬውን ወደ ሕወሐት ከደቡብ የመጣውን አማረኛ ተናጋሪም ወደ ፈቀደው እየመለመሉ ይወስዱት እንደነበር በአማራው ላይ ግን ግፍ የጸና እንደነበር ሲናገር ሰምቸዋለሁ፡፡ ለዚህ ጦርነት የዳረጉን የእናንተ አባቶች ናቸው እያሉ የአማራ ምርኮኞችን የሚዘገንን ግፍ ያደርሱባቸው እንደነበር የዓይን ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ምን ታደርገዋለህ ፖለቲካችን ሁሉ የግመል ፖለቲካ ከሆነ ቆዬ፡፡
ለማንኛውም ይህንን ኤርትራን ከኢትዮጵያ የነጠለውን የጦርነት ታሪክ አይ ምጽዋ የተሰኘውን መጽሐፍ ታነቡት ዘንድ ግብዣየ ነው፡፡
*
ጌታ ሆይ ከመጠፋፋት ተላቀን ከመለያየት ተፋተን በፍቅርና በአንድነት ንሴብሖ ብለን የምንዘምርበትን የድል ቀን ሳታሳይ አትግደለን፡፡አሜን፡፡
Filed in: Amharic