>

ብ.አ.ዴ.ን. ይፍረስ ያልነው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲኾን ነው!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ብ.አ.ዴ.ን. ይፍረስ ያልነው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲኾን ነው!!!

አቻምየለህ ታምሩ
‹አማራ ክልል› የሚባለውን የዐቢይ አሕመድ የማደሪያ መሬት በእንደራሴነት የሚገዘግዙት ነውረኞቹ ብ.አ.ዴ.ኖች የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶችን ለማጥፋት ቆርጠው መነሣታቸውን ነግረውናል። እነዚህ በድኖች ይህን ያስታወቁት በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የአፓርታይድ አገዛዝ ለ30ኛ ዙር ያሰለጠነውን የኦሮሞ ተወርዋሪ ጦር ባስመረቀበት ሳምንት ነው። ለመኾኑ እነዚህ በሆዳቸው የሚገዙ አጋስሶች ስለ ጎበዝ አለቃ ምንነትና ፋይዳ ያውቃሉን?
ሀገራችንም ኾነ መንደራችን አደጋ ላይ በወደቁበት ጊዜ ሁሉ የጎበዝ አለቃ የሕዝቡን ደኅንነት፣ ሰላምና ነጻነት ለመጠበቅ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በራስ አነሳሽነት ሲያገለግል የቆየ ሀገር በቀል አደረጃጀት ነው። ይህ ሀገር በቀል አደረጃጀት እንኳን እንዲጠፋ ሊዘመትበት ቀርቶ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ የሚፈለግበት ጊዜና ወቅት ነው። አደረጃጀቱ አማራውንም ኾነ ሀገራችንን ከገጠማት ችግር ለማላቀቅ ብቻ ሳይኾን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣና ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲኾን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችል ኃይል ነው።
አጋሰሶቹ ብ.አ.ዴ.ኖች የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶችን ማጥፋት አለብን ብለው ካቀረቡት የድንቁርና ምክንያት አንዱ አደረጃጀቱ መሪ የሌለው የሽፍታ ስብስብ ነው ብለው ማመናቸው ነው። እነሱ የሚያውቁት የመሪ ሞዴል ከኮምኒስት ማኒፌስቶ የሚነሳ፣ በ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» የተጠመቀ፣ እንደ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ዓይነት ፈላጭ ቆራጭ ግለሰብ ስለኾነ ከዚያ የተለየ ሀገርኛ የትግል አመራር ዘዴ ቢኖርና ውጤት ቢያመጣ እንኳ መሪ ያለው መስሎ ባይታያቸው አይፈረድባቸውም። በርግጥ የብ.አ.ዴ.ኖች አለቃ የነበሩት ወያኔዎች ወላጆቻቸው፣ የኢትዮጵያ አርበኞች በየጎበዝ አለቃው እየተደራጁ ወራሪውን ፋሽስት ሲፋለሙ እነርሱ ባንዳ ኾነው ለወራሪው እንቁላል ይቀቅሉና ጀግኖችን ይፋለሙ ስለነበር ለሀገር በቀል የአርበኛነት ተጋድሎ አደረጃጀቶች ባዕድ ናቸው።
የጎበዝ አለቃ የመሪ ሞዴል፣ እንደ ብ.አ.ዴ.ን ፈጣሪዎቹ ወያኔዎች ከአምባገነን የአውሮፓ አገዛዞች ተኮርጆ የመጣ የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት የሚሰፍንበትና ሙታን እድምተኞች ጀሌ ኾነው የሚሰለፉበት ድንግዝግዝ ሳይኾን ከአባቶቻችን የተወረሰ፣ ከውጭ የመጡ ጥጋበኛ ወራሪዎችን በተደጋጋሚ ያሳፈርንበት ሀገር በቀል የኅብረተሰብ አደረጃጀት ዘዴ ነው።
የጎበዝ አለቃ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ፣ ጎበዞች ከመሀከላቸው አንዱን ጎበዝ አለቃ አድርገው ለተጋድሎ የሚሰማሩበት የአርበኞች አደረጃጀት ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት እንደ ብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ አንድ ጮሌ ሺህ ነፈዞችን በዙሪያው አሰልፎ የሚነግራቸውን ብቻ የሚደግሙ ደናቁርት የተሰበሰቡበት ስምሪት አይደለም። በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ሁሉም ጎበዞች ስለኾኑ በመካከላቸው የበላይና የበታች የለም። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት እንደ ወያኔ አንዱ ሲሞት ያለመሪ የሚቀር ስብስብ ሳይኾን ሁሉም በማንኛውም አስፈላጊ በኾነ ጊዜ አለቃ የመኾን ችሎታውም ኾነ ፈቃደኝነቱ ያላቸው ጎበዞች አደረጃጀትና ሥርዓት ነው። ባጭሩ የጎበዝ አለቆች የምንላቸው በራሳቸው ጉብዝና ተከታይ አፈርተው ባለብዙ ተከታይ የኾኑና ከጠላት በፊት ምንም ያልነበሩ (ለምሳሌ ደጃች በላይ ዘለቀ እና ልጅ ካሣ ኃይሉ) ጀግኖችን ነው።
የብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ የፈጠረው የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» አደረጃጀት፣ በበሉበት የሚጮሁ፣ በሆዳቸው የሚገዙ ካድሬዎች ጥርቅም ነው። ስለኾነም ውላቸው ሆዳቸው እስከሞላ ድረስ ስለኾነ አለመተማመን፣ አለመከባበር፣ ጥላቻ፣ አንዱ ባንዱ ላይ መረማመድ የስብስቡ መገለጫ ነው። ለዚህም ነው ብ.አ.ዴ.ን የሚባል የአጋሰስ ስብስብ በመንደር አስተሳሰብ እየታመሰ ያለው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ግን የመዋቅሩ መሠረት የቆመው በእኩልነት ላይ በመኾኑ መተማመን፣ መከባበር፣ መፋቀር፣ አንዱ ላንዱ አንተ ትብስ መባባል ጎልቶ የሚታይ የስብስቡ መገለጫ የኾነው።
በባህላችን አንድ ሰው የጎበዝ አለቃ የሚኾነው እንደ ብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ ጮሌ ስለኾነ ብቻ ሳይኾን ከስብስቡ ውስጥ በሥነ ልቦና፣ በሥነ ምግባር፣ በሞራል ሥልጣኔ፣ በጥበብ፣ በመንፈስ ጥንካሬና በአመዛዛኝነት የተሻለ ኾኖ ሲገኝ ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት በቤተሰብ ደረጃ በሚታይ መተሳሰብ የቆመ የተጋድሎ መዋቅር ነው። በጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የጎበዝ አለቃው አብረውት የተሰለፉ አርበኞችን በቅድሚያ ሸልሞና ማዕረግ ሰጥቶ በትህትና መንፈስ ተልዕኮ በመስጠት ለተጋድሎ ያሰማራቸዋል። ለአርበኞች የሚሰጠው ማዕረግና ሹመትም በብቃት ልክ የተመጠነ ነው። የአቸፈሩ ጀግና ፊታውራሪ አያሌው መኮንን በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ተጋድሎ ዘመን የጎበዝ አለቃ ኾነው ሕዝብ ሲያታግሉ በየጊዜው ሲሾሙና ሲሸልሙ የነበሩት ለራሳቸው ሳይኾን አብረዋቸው ለተሰለፉ ጭፍሮቻቸው ነበር።
የብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ የገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» ግን የበላይና የበታች ያለበት፣ መጠራጠር፣ ፍራቻ፣ ጥላቻ፣ ቅናትና ጊዜን ጠብቆ መጠቃቃትን መርሁ ያደረገ የእፉኝት ልጆች ስብስብ ነው። መለስ ዜናዊ በገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» የማዕረግና የሥልጣን ምንጭ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ተቃራኒ ነው። መለስ ዜናዊ በገነባው «አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» ሞዴል መለስ ዜናዊ ለራሱ በቅድሚያ ሥልጣን ሸልሞ በኢትዮጵያ ላይ ቁብ ይልና የማዕረግ እድገቱንና ሹመቱን የሚቀበሉት ደግሞ ክህሎት በዞረበት ዝር ብለው የማያውቁ ዝቃጮት ናቸው።
መለስ ዜናዊ የፈጠረው የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» ማዕከላዊነት አደረጃጀት የአንድ ግለሰብ አስተሳሰብ ያለ ገደብ የሚፈጸምበት ልቅ ሥርዓት ነው። ስለኾነም የሚያኮርፈው፣ የሚከፋው፣ የሚያዝነውና ቂም የሚቋጥረው ሎሌ፣ አሽከርና ጀሌ ቁጥር የትየለሌ ነው። የአማራ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ግን የሁሉም ሐሳብ በእኩልነት የሚስተናገድበት፣ የተሻለው በውይይት ተቀባይነት የሚያገኝበት፣ ከሐሳቦች ሁሉ ምርጥ የኾነው በሁሉም የጎበዝ አለቆች ይሁንታ አግኝቶ በሙሉ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግበት፣ ውጤቱም ሁሉንም የሚያረካ ሥርዓት ያነበረ/ያኖረ የአባቶቻችን አስተዳደራዊ መዋቅር በመኾኑ የሚያኮርፍ፣ የሚከፋ፣ የሚያዝንና ቂም የሚቋጥር አንድም ሰው አይኖርም።
እኩልነት ብሎ ነገር ደብዛው የሌለበት የሊቀመንበር መለስ ዜናዊ የ«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» አደረጃጀት ግን፣ ስብስቡ የሚዘወረው በአንድ ሰው ሐሳብ በአንድ ሰው ፍላጎት ስለኾነ የተሻሉ ሐሳቦች ወደፊት የመምጣት እድል የላቸውም። ሊቀ መንበሩም ከራሱ የሥልጣን ጥቅም አንጻር ብቻ ስለሚያስብ ውጤቱ አብዛኛውን የስብስቡን አካላት የማያረካ ይኾናል። ይህ የበለጠ ጥርጣሬ፣ የበለጠ በቀለኝነት ያሰፍናል። ሊቀመንበሩም ይህንን ስለሚያውቅ ጥርጣሬና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ሲል ነጻነትን እያፈነ ይሄዳል። «ውስጣዊ ዲሞክራሲ» እና «ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት» የሚሉት የመለስ ዜናዊ «አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ» አስተሳሰቦች በግለሰብ አምባገነንበት የተደመደሙት ጥርጣሬንና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ሲል ነጻነትን በማፈኑ ነው።
«ልማታዊነቱን» እንዳስመሰከረ በብ.አ.ዴ.ኖች ሲመሰከርለት የኖረው መለስ ዜናዊ አስመዘገበ የተባለው ልማትና እድገት በቃላትና በፊደል የሚሟሟ ይመስል የሕትመት፣ ብሮድካስቲንግና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ማለትም የግል ጋዜጦችንና መፅሔቶችን፣ የግል ሬዲዮኖችንና የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን፣ የሚነበቡና የሚደመጡ ዌብ ሳይቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ተቺ ምሑራንንና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ትንሽ ትልቅ ሳይል በጠላትነት ፈርጆ በማፈን፣ በማዋከብ፣ በማሰርና በማወክ ሥራ ባገዛዝ ዘመኑ ሙሉ ተጠምዶ የኖረው የሚቃወሙትን ብቻ ሳይኾን በዙሪያው ያሰለፋቸውን ግብረ አበሮቹን የሰበሰባቸው ከራሱ የሥልጣን ጥቅም አንጻር ብቻ ስለኾነ ጥርጣሬና በቀለኝነትን ለመቆጣጠር ነው።
በእውነቱ የዲሞክራሲ መሠረቱ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ነው፤ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት በጫካ ወይንም በከተማ ሊፈጠር ይችላል። በታሪክ እንደምናውቀው የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የሚንቀሳቀሰው ጎበዞች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች በራሳቸው ጥረት ፈልገው በማግኘት ነው። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሳሪያ ወይንም ገንዘብ የሚያገኘው በሌላ ድርጅት ሳይኾን በራሱ ጥረት የሚያስፈጉትን ማቴሪያሎች በማሟላት ነው። ሌላው መሳሪያ ወይም ገንዘብ ስለሰጠው ሊያዘው፣ ተከተለኝ ሊል አይችልም። የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት የማንም ውለታ የሌለበት፣ እያንዳንዱ አባል ለራሱና በእኩል ለሚያያቸው ጓዶቹ ብቻ ታማኝ የኾነበት አደረጃጃት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ከጎበዝ አለቃ አደረጃጀት ይለያል። በመሠረቱ አንድ ግለሰብ ወይንም ማኅበረሰብ መደራጀት ያለበት በመርሕ በሚመራ ዓላማ ሥር እንጂ በፖለቲካ ፓርቲ ወይንም በድርጅት ሥር መኾን የለበትም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይንም ድርጅቶች ተቀዳሚ ተግባር ግን ሕዝብ የሚደራጅበትን ዓላማ መቅረጽ ነው።
ስለዚህ የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሪ አለው፤ መሪዎቹ ደግሞ በአባቶቻችን ትውፊት የተደራጁትና በዘመናዊ መልክ የተቀናጁ መሬት ላይ ያሉ ጎበዞች ናቸው። የጎበዝ አለቆች ተከታቶቻቸውን እየመሩ ያሉት እንደ ብ.አ.ዴ.ን በሆዳቸው እየተገዙ ጀሌ ኾነው ሳይኾን ሕዝባቸው መሀል እየዋሉ፣ እያደሩና የሕዝቡ አካል ኾነው ነው። የጎበዝ አለቆች ሕዝባቸውን እየመሩ ያሉት እንደ ጎቤ መልኬ ያሉ አለቆቹ ሲሰውበት የተሰዋውን አርበኛ በክብር መዝገብ አስፍረው እንደየቤተ እምነቱ በክብር እንዲያርፍ በማድረግ እንጂ እንደ ብ.አ.ዴ.ን የነፍስ አባት መለስ ዜናዊ «የሟች ወታደሮችን አሃዝ ይፋ የማድረግ ግዴታ የለብኝም» በማለት ያሰማራውን ኃይል ሞራል በመግደልና የጠላትን ሞራል ደግሞ ከፍ በማድረግ አይደለም።
ጀግኖች አባቶቻችን በጎበዝ አለቃ ተደራጅተው ሲፋለሙ የኖሩት በአምስት ዓመቱ የፀረ ፋሽስት ተጋድሎ ብቻ ሳይኾን ከዚያ በፊት በተካሄደው የአድዋ ተጋድሎም ጭምር ነው። ጥሊያን አንዱን የጎበዝ አለቃ አደረጃጀት መሪ ቢገድልም ሁሉም የጎበዝ አለቆች መሪ ሊኾኑ የሚችሉ ጎበዞች ስለኾኑ አንድ መሪ የጎበዝ አለቃ ቢሰዋ ትግሉ ነጻነታችንን መልሰን እስክናገኝ ድረስ ሊቆም ያልቻለው ለዚያ ነበር። በአድዋ ጦርነት ወቅት…
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤ 
 
የተባለው ለዚያ ነበር።  ይህም በመኾኑ በሁለቱ ዙር በተካሄዱ የጎበዝ አለቃ ተጋድሎዎች ነጻነታችንን ልናስመልስ ችለናል። ዛሬም በየአካባቢው በጎበዝ አለቃ በመሰባሰብ የሚካሄደው አደረጃጀት ይህን የቀደምት አያቶቻችንን አሠራር የተከተለ ነው።
ብ.አ.ዴ.ን የወቅቱ ጌታውን የዐቢይ አሕመድ ተልዕኮን ለማስፈጸም ሲል የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶችን አጠፋለሁ የሚለው አደረጃጀቱ አንድ ልብ የኾኑ ጀግኖች የሕልውና አደጋ የተጋረጠበትን ሕዝብ ሊያጠፋ በሚሰማራው ጠላት ላይ የሚያደርጉትን ትግል ኢንተርኔት ቢያቋርጡ፣ ነፍሰ በላ ጦር ሠራዊት ወይንም ተወርዋሪ ጦር ቢያሰማሩ፣ አፋኝ ቡድንም ኾነ ያላቸውን ምድራዊ ኃይል ሁሉ ቢያሰልፉ የጎበዝ አለቃ ተጋድሎን ሊያስቆሙት እንደማይችሉ ስለሚያውቁ ነው።
Filed in: Amharic