>
5:13 pm - Tuesday April 19, 3768

የህዳሴው ግድብ ሱዳን፣ግብጽና አረብ ኢምሬት!! (አወድ ሞሀመድ)

የህዳሴው ግድብ ሱዳን፣ግብጽና አረብ ኢምሬት!!

 

አወድ ሞሀመድ
በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ጀርመን ሞሆን እና እድርሴ የሚባሉ ሁለት ወሳኝ ግድቦች ነበሯት። እነዚህ ሁለት ግድቦቿ ሰፊዉን የጀርመንን ኢንዱስትሪ ሀይድሮፓወር በማቅረብ ከማነቃነቅም በዘለለ ለአብዛኛዉ ህዝቧ የንፁህ መጠጥ ዉሀንና እጅግ አስፈላጊ ለሆኑት የጀርመን ብረት ፋብሪካዎች የተጣራ ዉሀን የሚያቀርቡላት ነበሩ። በዚህም የተነሳ እንግሊዝና አጋሮቿ  የጀርመንን ኢንዱስትሪያል አጥንት ለመስበርና በመሳሪያ ጥራትና ምርት ላይ ያላትን የበላይነት ክፉኛ ለመጉዳት እነዚህ ግድቦች መመታት እንዳለባቸዉ በመወሰናቸዉ፣ በተለያየ ጊዜ የጀርመንን ድርብርብ መከላከያ ወጥመዶችን በማለፍ በግድቦቹ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ነበር። ነገር ግን ሳይሳካላቸዉ ቀረ።
ጀርመን በግድቦቿ ዙሪያ ካሰፈረችዉ መከላከያዎቿ አንዱ በዉሀዉ ዉስጥ ለዉስጥ በተለያየ ርቀትና ደረጃ በመወጠር የዘረጋችዉ ዉስብስብ የብረት ሰንሰለት ይገኝበታል። የአንድ ግድብ ኋይል ማመንጫዎቹ ያሉት ከዉሀዉ ስር በመሆኑ ከባድ ዉድመት እንዲደርስበት ከተፈለገ በዋናነት መመታት ያለበት ከታች ነዉ። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለዉ በዉሀዉ ዉስጥ ተለቀዉ እየተምዘገዘጉ ሊሄዱ በሚችሉ ቶርፒዶ ቦንቦች ነበር። ለዚህ ደግሞ ጀርመን የዘረጋቻቸዉ የሰንሰለት መከላከያዎች የሚያሳልፉ አልነበሩም። ተምዘግዛጊዉን ቶርፒዶ ከርቀት ጠላልፈዉ ማገትና ማምከን በመቻላቸዉ ግድቦቿን በዚህ መልኩ ከጥቃት ተከላክላ ለማቆየት ቻለች።
ግድብ በመደበኛ የአይሮፕላን ቦንብና ድብደባ ሊፈርስ የሚችል መሰረተ ልማት ባለመሆኑ እንግሊዝ ወታደራዊ ሳይንቲስቶቿን ለዚሁ ጥቅም ሲባል ብቻ ሊዉል የሚችል አዲስና ረቂቅ ቦንብ በመፈብረክ ላይ እንዲጠመዱ አዘዘች። በአጭር ጊዜም ባርነስ ዋለስ የተባለዉ ሳይንቲስት ነጣሪ ቦንብን ፈበረከ።
ባርንስ ዋለስ የፈጠረዉ ቦንብ ሁለት ጊዜ መፈንዳት የሚችል ቦንብ ነበር። ይህ ቦንብ በዉሀዉ የላይኛዉ አካል እየነጠረ ወደ ግድቡ ግድግዳ ጥግ መድረስ የሚችል ሲሆን፣ ከደረሰም በኋላ በግድግዳዉ ላይ በሚያደርሰዉ የመጀመሪያ የፍንዳታ ፍርስራሽ ተገፍቶ ወደታች በጥጉ በኩል እያስታከከ እንዲወርድ ይሆንና ዋነኛዉን ፍንዳታ በታችኛዉ የግድቡ ክፍል ላይ ማድረስ የሚችል ነበር።
እንግሊዞች ይሄን በማድረግ ግድቦቹን ከስር በዋነኝነት ለመብሳትና ለመሸንቆር ስምንት አይሮፕላኖቻቸዉን ከ 60 በላይ አብራሪዎችና ቴክኒሻኖቻቸዉ ጋር በጀርመን አየር መቃወሚያዎች ያጡ ቢሆንም ዘመቻዉን እንደ ፈረንጆች May 17 1943 በተሳካ ሁኔታ በማድረግ የፈለጉትን የግድቡን ክፍል ደርምሰዉ ጀርመንን ሊያዳክሟት ቻሉ። ነጣሪዉ ቦንብ ክብደቱ 4196 ኪ ግራም ነበር።
ከሰሞኑ ስሙን ለመጥራት ባልፈለኩት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በእንግድነት የቀረበዉ ሻለቃ ግብፆች ግድባችንን ካፈረሱ እኛም አስዋንን ለማፍረስ ቴክኖሎጂዉና አቅሙ አለን ብሎ በድፍረት ሲናገር ገርሞኝ ነዉ ይሄን ያመጣሁት። በመሰረቱ ግድብ የተወሰነ ግንባታዉ ከተጠናቀቀ በኋላ ፍረስ ብትለዉም አይፈርስም። ተራራ መምታት ማለት ነዉ የሚሆነዉ። በጣም የረቀቀ መሳሪያ ከወታደራዊ ምሁራን ጋር  ከሌለህ ለማፍረስ አይደለም ለመሽረፍም ይከብዳል። ለዛም ነዉ አሜሪካኖች ኦባማ እንደመጣ አካባቢ ለግብፆች ግድቡን ለመምታት የሚቻለዉ ግንባታዉ 30 እና ከ 30 በመቶ በታች ከሆነ ብቻ እንደሆነና ከዛ ካለፈ የሚያዋጣቸዉ መነጋገርና ስምምነት ማድረግ መሆኑን የነገሯቸዉ። አሁን ግንባታዉ 70 በመቶ በደረሰበት መምታት የሚለዉ ነገር በሁለቱ አገሮች ካለዉ ርቀት አንፃርም የሚታሰብ አይደለም።
አሁን ግብፅ ግድቡን በቀጥታ ለመምታት መሞከር ሳይጠበቅባት ኢትዮጲያን ለማሽመድመድ የምትችልበትን መንገድ ከተሳካላት እየሞከረች ነዉ።  እየሞከሩት ያለዉ አካሄድ እንደምንም ከተሳካላቸዉ፣ ግድቡንና የግድቡን ስራ ሊያዉኩና እስከወዲያኛዉ ሊያስተጓጉሉት ይችላሉ። መረሳት የሌለበት ግድቡ ያለዉ ከሱዳን ድንበር 17 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ነዉ።
ሱዳን ከለዉጡ በኋላ ዉስብስብ ችግሮች እየገጠሟት ነዉ። ህዝቧም በከፍተኛ ሁኔታ በአዲሱ መሪዎቻቸዉ ላይ እያጉረመረሙ፣ ዉስጥ ዉስጡንም እየቆሰሉ ነዉ። ገና ትናንት አልበሽርን ገልብጠን በአዲስ የተካነዉን መንግስት አሁን ደግሞ ሰልፍ ወጥተን ዉረድ ብንለዉ አለምስ ምን ይለናል የሚል እፍረት ይዟቸዉ እንጂ ምሬታቸዉ ጥግ ደርሷል። የሱዳን ፓዉንድ እያሽቆለቆለ ነዉ። የመሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ በተለይ የዳቦና ዘይት ከመናሩ በላይ በአገሪቱ ጠፍቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። መብራት በዋናዉ ከተማዉ ካርቱም ሳምንቱን ሙሉ ጠፍቶ የሚጨልምበት፣ ዉሀ ጠፍቶ የሚከርምበት፣ የሰላምና ፀጥታዉ ሁኔታ ምስቅልቅሉ የወጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ሁሉ በሚሆንበት ነዉ ሱዳን ከአረቦች አፈንጋጣ ከኢትዮጲያ ጎን ለመቆም የደፈረችዉ። በዚህም አቋሟ የአረብ መንግስታትን በማስቆጣቷ ሰሞኑን ባለባት ችግር ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሳዑዲና ኤመሬትስ ለኢኮኖሚዋ ድጋፍ ሊሰጧት የነበረዉን $3.1 ቢሊዮን ዶላር ሰርዘዉባታል። በቅርቡም በመንጋ ከሚመራዉ አረብ ሊግ ከተባለዉ ስብስብ ሊያገሏትና በግዷ ከእናንተ ጎን ለመቆም ወስኛለሁ ከኢትዮጲያ ጎን የቆምኩት ተሳስቼ ነዉና ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እለምናለሁ እስክትል ድረስ የዲፕሎማሲና የበረራ ከዛም አልፎ ከእነሱ ጋር የምታደርገዉን የንግድና ኢኮኖሚ ዕቀባ ሊያደርጉባት ይችላሉ። በቀላሉ አይፋቷትም።
ሱማሊያ ሌላዋ የአረብ ሊግ አባል ናት። ሱማሊያ የኢትዮጲያ ታሪካዊ ጠላት እንደመሆኗ ከግብፅ ጎን መቆሟ የሚጠበቅ ነዉ። ደሀና ከሞላ ጎደል መንግስት አልባ ልትባል የምትችል ስለሆነችም ከፍ ያለ ብር ይዞ ለመጣላት ቀሚሷን ታወልቃለች። ከኢትዮጲያ ጋር ካላት ቅርበት የተነሳ ለግብፅ ጦር ሰፈር የሚሆን ቁራሽ መሬት ብትሰጣት ግብፅ ኢትዮጲያን ለማወክና ለማስፈራራት በቂ መደንፊያ ሜዳ አፍንጫችን ስር አገኘች ማለት ይሆናል። ቁርጡ ቀን ሲመጣ ሱማሌዎች ከግብፅና ከአረብ ሊግ ካልሸሹ በስተቀር ግብፆች በሉ አባል እንደመሆናችሁና አጋራችሁ ነን እንዳላችሁን የሚጠበቅባችሁን አሁን በተግባር አምጡ ማለታቸዉ አይቀርም።
ደቡብ ሱዳን ሌላዋ በሁለት እግሯ ለመቆም የምትዉተረተር ቤሳቤስቲን የሌላት ደሀ አገር ናት። ግብፆች ሰሞኑን ወታደራዊ ሹማምንቶቻቸዉን ወደ ጁባ በመላክ ሳልቫኪር ከጎናቸዉ እንዲሆን ወጥረዉ ይዘዉታል። ይህን የሚያደርጉት እንደ ሱዳንና ሱማሊያ ከኢትዮጲያ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ለጦር ቀጠና የሚሆን መሬት በሚያስፈልገን ጊዜ ይሰጠናል በሚል ተስፋ ነዉ። አሁንም መረሳት የሌለበት ግድቡ የተገነባዉ ሱዳን ድንበር ላይ መሆኑን ነዉ። ግድቡ ለኢትዮጲያ መሀል አገር ከሚቀርብ ይልቅ ግብፅ ሊኖራት ለሚችለዉ የጦር ቀጠና በጣም የቀረበ ይሆናል ማለት ነዉ። ስለዚህ ግብፅ እየተሟሟተች ያለችዉ እነዚህን በኢትዮጲያ ዙሪያ ያሉትን ሶስት አገሮች በቻለችዉ ሁሉ አስገድዳና አማላ የርሷ ማድረግ ነዉ። ለአሁኑ ኢትዮጲያ የሱዳንን አጋርነት አግኝታ ይሆናል። ግብፅ ከተቀሩት ሁለቱ አገሮች አንዷን እንኳ ማሳመን ብትችል ሱዳንን ከናካቴዉ ላትፈልጋት ትችላለች።
ከዛስ በኋላ? ግብፅ ግድብ መምቻ መሳሪያ ሳይኖራት ምን ልታደርግ ትችላለች? 
ግብፅ ኢትዮጲያ ዙሪያ ካሉ አገሮች በተለይ ከደቡብ ሱዳን የጦር ቀጠና ካገኘች በኋላ ልታደርግ የምትችለዉ በመጀመሪያ የተወሰኑ ወታደሮቿንና አየር ሀይሏን በዛ በማምጣት ማስፈር ሊሆን ይችላል። ከዛ ከጦር ቀጠናዉ እየተነሳች በድንበሩ ጥጋ ጥግ እንደፈለገች መብረር፣ አስፈላጊ ሲሆን አልፎ አልፎ የኢትዮጲያን የአየር ክልል ጥሳ በመግባት ቀጠናዉን ማወክ ነዉ። በግድቡ የሚሰሩ ሰራተኞችንና ኮንትራክተር ካምፓኒዎችን ለደህንነታቸዉ የሚሰጉ እንዲሆኑ በማድረግ ስራቸዉን ማስተዉና ማስተጓጎል ነዉ። መረበሽ  Harass ማድረግ ነዉ። ኢትዮጲያን በተጠንቀቅና በቋፍ በማቆም ሌላ ምንም ስራ እንዳትሰራና ሀሳቦቿን ሁሉ በፀጥታና ደህንነቷ ላይ እንድታተኩር ማድረግ ነዉ።
ጥያቄዉ ግብፅ ከጎረቤት ሀገር ይሄን የጦር ቀጠና ይዛ እንዲህ ስታደርግ ኢትዮጲያ ዝም ብላ ታያለች ወይ? ደህንነቷን ለመጠበቅና ለማስጠበቅስ እስከምን ድረስ ትጓዛለች? ግብፅ ሊኖራት የሚችለዉን ይህን ቀጠና በቅድሚያ መዉረርና መምታት ትችላለች ወይ? መቼ? እንዴት? ምን? በየት በኩል? የሚሉትን ጥያቄዎች ኢትዮጲያ ካሰበችበት በጣም ትችላለች።
*********
ነቢዩ ሙሀመድ ሰዐወ በትንቢታዊ ሀዲሳቸዉ/ንግግራቸዉ ኢትዮጲያና ኢትዮጲያዉያን ወደ መጨረሻዉ አካባቢ በአረቦች እምብርት ላይ በመረማመድ ያደርሳሉ ያሉትን ዉድመት ምናልባት ሊመጣ ከሚችለዉ ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያገናኘዉ ነገር ይኖር ወይም አይኖር ይሆን የሚለዉን ወደፊት እናየዋለን ኢንሻአላህ።
Filed in: Amharic