>

ተመረመርኩ!!! ( በእውቀቱ ስዩም)

ተመረመርኩ!!!

 

( በእውቀቱ ስዩም)
  ወደ  አሜሪካ የተመለስኩት ትራምፕ ከግብፅ ጋ ተሞዳሙዶ ኢትዮጵያን አስገድዶ ለማስፈረም  በዛተበት   ቀን ማግስት ነው::  ብዙዎቻችሁ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ባለ የጭንቅ ቀን ጥለሃት መሄድህ ክደት ነው በማለት በኢንቦክስ ወቅሳችሁኛል: :  የወጣሁት ለታክቲክ ነው!   እንደኔ እንደኔ ያሜሪካን   ከውስጥ ሆኖ ለመታገል ከዚህ ጊዜ  የተሻለ  አጋጣሚ  የለም::
 እና ስም አይጠሬው እንዴት  እያረጋችሁ ነው?  ከአምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠው ትኩሳታም ዜጋ ፤   ሲረሸን ላይቭ የሚተላለፈው መቸ ነው? ለመሆኑ  ዛፓዎች  አስፈላጊው ፍተሻ  አድርገውበታል ?  እንደኔ እንደኔ ኤርፖርት ላይ በመሳርያ ሲዳብሱት  ትኩሳቱ  ያሸቀበው፤  በቫይረሱ ምክንያት  አይመስለኝም:: የሆነ በዱባ ቅጠል  ጠቅልሎ የዋጠው ኮኬን ሳይኖር አይቀርም!!  አለበለዝያ ሰው እንዴት የጤና ድጋፍ ሸሽቶ ያመልጣል?
እኔማ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳረግ ቆይቻለሁ::   ፊትህን አትንካ ተብሉዋል  ፊቴን አልነካም::  መንገጭላየ ግድም ሲበላኝ   ፤ እንደ ዳንግሌ በግ የግድግዳውን  ጠርዝ  በመታከክ ጥሜን አረካለሁ:: ማንኛውንም አይነት  የበር እጀታ አልጨብጥም::  ትናንት ያንዱን  ሚኒማርኬት በር እንደቻክኖሪስ በርግጫ ከፍቼ ስገባ ዘበኛው   ተናዶ በጥፊ ሊያጮለኝ ከቃጣ በሁዋላ፤ ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል በጠረባ ጣለኝ::
በቀደም ለት፤  ወደ ቤቴ እየሄድኩ አንዱ ከጀርባየ  አስነጠሰ:
 ዞር አልኩና ” ሶየ ..  በህግ አምላክ እንዳትንቀሳቀስ ! “
“ምነው?”
ያነጠስክበት ቦታ ከኔ ጋ ያለውን ርቀት ልለካው ነው !!!  ከሶስት ሜትር ካነሰ ወደ ጤና ጣቢያ እደውላለሁ”
 በተቻለኝ መጠን ቅድመ ጥንቃቄዎችን ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ ጉሮሮ መድረቅ የለበትም  በተባለው መሰረት ውሃ ካጠገቤ አይለይም ::  አሜሪካ  ውስጥ የውሃ ችግር የለም፤   ከፈለግሽ ትራስሽ አጠገብ  ቧንቧ ማስገጠም ሳይቀር ትችያለሽ ::  እዚህ አገር  በፈረቃ እሚመጣ ጥም እንጂ በፈረቃ እሚመጣ ውሃ የለም !  ድሮ አንድ ጣሳ ውሃ ከጠጣሁ  በመላው ሰውነቴ ሲንሸራሸር ሰንብቶ፤ ሁለመናየን አፅድቶ   በሁለተኛው ቀን ነበር ተረፈ ምርት ሆኖ የሚወጣው::  እንዲያውም አንዳንዴ  ሳምንት የማልሸናበት ጊዜ ነበር፤
አሁን  ገባ ብርጭቆው ካፌ ሳይወርድ፤ የምጠጣው ነገር  በቀጥታ ስርጭት ወደ ፊኛየ ይሄዳል::   “ከበውቄ ጋራ  መጠጣት እኮ  ውሃ በወንፊት  ውሃ እንደ መቅዳት  ነው “ ይላሉ አብሮ ቀምቃሚዎቼ!   ደሞ አንድ ብርጭቆ  ውሃ ጠጥቼ  አንድ ማድጋ  የምሸናበት ምሲጢር አይገባኝም  ፤ የሆነ  ለጡሮታ የተጠራቀመልኝ ሽንት  ሳይኖር አይቀርም ::
 ችግሩ ፤ ምኝታ ቤቴ ከሽንት ቤቴ በጣም ይርቃል:: በዛ ላይ ያሜሪካ ሽንት ቤት በጣም ፅድት ያለ ስለሆነ  በቀላሉ  እሺ ብሎ አይወርድልኝም ::   የመጣው  ሌሊት ከሆነ ደግሞ አባብየ ወይም ጨቁኘ አሳድረዋለሁ፤
 ከትናንት ወድያ  በተከታታይ በእሩምታ ማስነጠስ ጀመርኩ ፤   ብዙም ሳልደናገጥ  911 ደወልኩና “ መጥታችሁ ትወስዱኝ ወይስ መደዳውን ልበክል?”  አልኳቸው፤ በታንክ የታጀበ  አምቡላንስ ልከው ወሰዱኝ::(ከኢትዮጵያ መምጣቴን ስለሰሙ ሰብሮ ያመልጣል ብለው ሰግተው ነው)
ዶክተሩ መርምሮኝ ሲያበቃ
“ ጥሩ  እና መጥፎ ዜና አለኝ” አለ፤
“ከጥሩ ጀምር!”
“   ኮረና የለብህም:: ግንባርህ ላይ ነጥሮ ተመልሷል::”
“ተመስጌን .  .መጥፎው ዜናስ ምንድነው?”
“   ሁለተኛው የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው   ፊኛህ ላይ ችግር ተከስቷል”
“ፊኛየ ምን ሆነ?”
‘’ ፊኛህ  ሽንት በማቆር ብዛት የተነሳ ተለጥጦ  የላም ጡት መስሏል፤”
“ እና ምንድነው እሚሻለኝ?” አልኩ በጭንቀት::
“ አለም በወረርሽኝ በሚዋከብበት ዘመን ያንተን ፊኛ ስራ ፈቶ እሚያክም የለም! እዛው አገርህ ገብተህ  እንድትሞት ሪፈር ፅፈንልሃል ! “
Filed in: Amharic