>

የዐፄ ምኒልክ እናት (ከግዛቸው ጥሩነህ (ዶ/ር))

የዐ ምኒልክ እናት

 

 

ከግዛቸው ጥሩነህ  ዶ/ር

 

 

 በቅርቡ አቶ አቻምየለህ ታምሩ ““የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እናት ማን ናቸው?”  በሚል ርእስ ሁለት አጫጭር ጽሁፎችን በኢትዮሬፈረንስ መጽሄት ድህረ-ገጽ አቅርቧል፡፡

በጽሁፎችም መሰረት የዐፄ ምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ በምስራቅ ጎጃም ውስጥ የጎዛምን አካባቢ ተወላጅ እንደሆኑና የአባታቸውም ስም “ኃይሉ ማሮ” መሆኑን “የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ” በሚል ርእስ በአቶ ግርማ ጌታሁን በተዘጋጀው የአለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ መጽሀፍ ውስጥ ማግኘቱን ገልጾልናል፡፡ የአለቃ ተክለ እየሱስ ዘገባ (አቶ አቻምየለህ እንዳለው)፤ ታዋቂው ጋዜጠኛ አቶ ፓውሎስ ኞኞ፤ ወ/ሮ እጅጋየሁ የጉራጌ ሰው መሆናቸውንና፤ አባታቸውም “ለማ አድያሞ” ይባሉ እንደነበር ከጻፈው ጋር የሚቃረን ነው፡፡ በተጨማሪም አለቃ ለማ ኃይሉ የሚባሉት ሰው፤ የወ/ሮ እጅጋየሁ አባት “አድያሞ ለማ” ከላስታ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ከመንዝ ናቸው ብለው ከ70 አመታት በፊት መጻፋቸውን አቶ አቻምየለህ ጨምሮ ከመግልጹም በላይ በእኒህ ጸሀፊም ዘገባ እንደማይስማማ ነግሮናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አቶ ታየ ቦጋለ የሚባለው የታሪክ ምሁር፤ ወ/ሮ እጅጋየሁ ኦሮሞ ናቸው ብሎ ማውራቱን አቶ አቻምየለህ በጥብቅ ተቃውሟል፡፡ ታዲያ የትኛው የዘር ዘገባ ነው ትክክሉ? በአቶ አቻምየለህ አስተያየት፤ አለቃ ተክለ እየሱስ የኖሩትና የጻፉት በዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግስት ስለሆነ፤ ከሌሎች ጸሀፊዎች ይልቅ ልንቀበለው የምንችለው የእሳቸውን ቃል መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

     ወ/ሮ እጅጋየሁ የጎጃም ሰው እንደሆኑ የሚተርክ ሌላ ዘገባ ደግሞ እኔ ከቤተሰቤ የሰማሁትን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ እኔ የተወለድኩት በምስራቅ ጎጃም ውስጥ በብቸና አውራጃ በደብረወርቅ ከተማ እንደሆነ አስቀድሜ መግልጽ እወዳለሁ፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ የጎጃም ሰው መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፤ የእኔ ቤተሰብም ዘመድ እንደነበሩ አጎቶቸ በየግዜው ነግረውኛል፡፡ የእኔ አጎቶች ስለቤተሰብ ታሪክና ትውልድ ብዙ የሚያውቁት ነገር ስለነበር፤ ካለፉት 10 አመታት ጀምሮ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በሄድኩ ቁጥር፤ ስለዚህ ታሪክ እየጠየቅኋቸው በማስተዋሻየ እጽፍ ነበር፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ለእኔ ቤተሰብ እንደሚዘመዱ ከጥቂት አመታት በፊት ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ነግሬአቸው፤ እሳቸው የሰጡኝ ምክር፤ የዘር ሃረጋችንን በጽሁፍ መልክ እንዳቀርበውና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ነበር፡፡ ሆኖም ግን፤ ዛሬ ነገ እያልኩ እስካሁን ቆይቸ አሁን ይህን የዘር ሃረግ በጽሁፍ ለማቅረብ የገፋፋኝ የአቶ አቻምየለህን ጽሁፎች ማንበቤ ነው፡፡ 

     በነገራችን ላይ አቶ አቻምየለህ እንዳለው፤ አለቃ ተክለ እየሱስ የተወለዱት በወለጋ ክፍለሃገር በጉድሩ ነው፡፡ እኔ ደግሞ መጨመር የምፈልገው፤ ዶ/ር ስርግው ገላው አስተካክሎ በ2008 ዓ.ም ካቀረበው የአለቃ ተክለ እየሱስ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርእስ በጻፉት መጽሃፋቸው ውስጥ ያገኘሁትን ነው፡፡ አለቃ ተክለ እየሱስ የ11 አመት ልጅ በነበሩ ግዜ ምስራቅ ጎጃም ውስጥ ወደሚገኘው ቀበሌ መኖሪያቸው ደብረ ፅሞና በ1871 ዓ.ም አምጥተው ያሳደጓቸው፤ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት (በፊት ደጃዝማች አዳል ተሰማ ይባሉ የነበሩት) አጎት፤ የሌሚቱ ጎሹ ናቸው፡፡ የሌሚቱ ጎሹ ወለጋ የሄዱት፤ ደጃዝማች አዳል ባደረጉት ዘመቻ ተካፋይ በመሆን ነበር፡፡ የሌምቱ ጎሹም ተክለ እየሱስን (ወለጋ እያሉ ነገሮ ዋቅጅራ ይባሉ ነበር) ክርስትና አስነስተው፤ የቄስ ትምህርታቸውን ከደብረ ፅሞና ብዙ ከማይርቀው በዲማ ጊዮርጊስ ገዳም እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ ተክለ እየሱስ ዲቁናም እንዳገኙ ዶ/ር ስርግው ገልጾልናል፡፡ ታዋቂው የታሪክ ምሁር ዶ/ር ታደሰ ታምራት እንደጻፈው፤ ደብረ ፅሞናና ደብረ ዲማ በ15ተኛው ክፍለዘመን (በ1400ዎቹ አመታት) የተመሰረቱ ጥንታዊ ገዳማት ናቸው፡፡ 

     ከዚህ በታች ያለው የዘር ሃረግ እንደሚያሳየው፤ የዐፄ ምኒልክ አያት፤ የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም አያትና የእኔ የአያቴ አያት የሆኑት የፊታውራሪ እንግዳ በረከታብ አያት የደጃዝማች ማሞ ልጆች ናቸው፡፡ የወ/ሮ እጅጋየሁ አባት ማን እንደሆኑ በወቅቱ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስላልሆንኩ፤ አለቃ ተክለ እየሱስ ያቀረቡትን ዘገባ ትክክል አይደለም ለማለት አልችልም፡፡ በእርግጥ ታዋቂው ጋዜጠኛና  አጎቴ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፤ ወ/ሮ እጅጋየሁ ዘመዳችን መሆናቸውን እንደሚያውቅና የአባታቸውም ስም “አድያሞ” ወይም “አዳምሰገድ” ነው ብሎ ነግሮኛል፡፡ ሆኖም ግን፤ ይህን ስም፤ ምናልባትም ተጽፎ ካገኘው ነገር እንጅ (ማለትም ከአቶ ፓውሎስ ኞኞና ከአለቃ ለማ ኃይሉ መጽሃፎች፤ ወዘተርፈ) ከእኛ ቤተዘመድ የሰማው ወሬ አይመስለኝም፡፡ 

DEJAZMACH MAMO Ancestory-2020

     በተጨማሪም በ1966 ዓ.ም አካባቢ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ፤ የወ/ሮ እጅጋየሁ የእህት ወይም የወንድም ልጅ እንደነበሩ፤ አጎቶቸ ጨምረው ነግረውኛል፡፡ የሚገርመው ስለ ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ብዙ ማዎቅ ፈልጌ ኢንተርኔት ውስጥ ገብቸ ሳነብ፤ በተጉለት ወይም ቡልጋ ተወልደዋል የሚሉ ጽሁፎች አየሁኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የመጡልኝ ሀሳቦች፤ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል፤ የእኛ ዘመድ ከሆኑ ጎጃም መወለድ ነበረባቸው፤ አጎቶቸስ እንዴት እንደዚህ ሊሰሳቱ ቻሉ የሚሉ ነበሩ፡፡ በዚህ ነገር ትንሽ ሳስብበት ግን፤ የዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ሰሜን ሸዋ መወለድ ከወ/ሮ እጅጋየሁ ታሪክ ጋር የማይቃረን መሆኑን ገምቻለሁ፡፡ በመጀመርያ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ቤተመንግስት ውስጥ ሲኖሩ በኋላ ንጉሥ ከሆኑት ከኃይለ መለኮት ዐፄ ምኒልክን እንደወለዱ የሚገልጹ ብዙ ጽሁፎች አሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው፤ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከጎጃም ወደ ሰሜን ሸዋ በመሄዳቸው ይመስለኛል፡፡ ሌላው ደግሞ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከጎጃም ወደ ሰሜን ሸዋ ድረስ ብቻቸውን ሄዱ ለማለት ያዳግታል፡፡ ይልቁንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር (በአንድ ላይ ወይም በመከታተል) በሆነ ምክንያት አገር ጥለው ሄደው ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ፤ ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ከወ/ሮ እጅጋየሁ የእህት ወይም የወንድም ልጅ፤ ሰሜን ሸዋ ሊወለዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን፤ ዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ የተወለዱት በ1920ዎቹ መሆኑን ያነበብኩ ስለሆነ፤ የወ/ሮ እጅጋየሁ የእህት ወይም የወንድም ልጅ ሳይሆኑ፤ የእህት ወይም የወንድም የልጅልጅ መሆን አለባቸው፡፡ የሀገራችን ሰዎች ዘመዳቸውን አቅርበው የመጥራት ባህል ስላላቸው፤ በልጅ ወይም በልጅልጅ መካካል ያለውን ልዩነት ትልቅ ቦታ አይሰጡትም፡፡

     ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የዳሞት (ምእራብ ጎጃም) ገዥ በመሆን ለረዥም ግዜ ያገለገሉ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቦታ የደረሱ ልጆችና የልጅልጆችም አፍርተዋል፡፡ ልጆቻቸው ራስ ከበደ፤ ወ/ሮ ዘውዲቱ፤ ወ/ሮ አስካለወርቅ፤ ወ/ሮ ላቀችና ወ/ሮ ወሰንየለሽ ይባላሉ (ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ)፡፡ ራስ ከበደ የጎጃም ጠቅላይ ገዥ የነበሩት የልጅ ሃይለማርያም አባት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ዘውዲቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስተር የነበሩት የልጅ እንዳልካቸው መኮነን እናት ነበሩ፡፡ የራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ልጅ ወ/ሮ ሰብለወንጌል፤ የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የልጅልጅ (የወ/ሮ አስካለወርቅ መንገሻ ልጅ) ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ሰብለወንጌል ኃይሉም የልጅ እያሱ ባለቤት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ላቀች መንገሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስተር የነበሩት የልጅ ሚካኤል እምሩ አያት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ወሰንየለሽ መንገሻም የልዑል አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴ (የአልጋወራሽ በኋላም በስደት እያሉ ዐፄ አምኃ ሥላሴ የተባሉት) ባለቤት የልዕልት መድፈሪያሽወርቅ አበበ እናት ነበሩ፡፡

     መላከ-ብርሃን ናሁ-ሰናይ ወርቅነህ ይባል የነበረው አጎቴ እንደነገረኝ ከሆነ፤ የእኔ የአያቴ አያት የሆኑት ፊታውራሪ እንግዳ በረከታብ፤ የዐፄ ቴዎድሮስ ወታደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ብዙ ወንድሞችና እህቶችም ነበሯቸው፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለየው ታዋቂው ጋዜጠኛ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፤ የነጪት በረከታብ የልጅልጅ ልጅ ነበር፡፡ የጎጃም ክፍለሃገር አስተዳዳሪ ሆኖ ያገለገለለው አቶ መንገሻ ወርቅነህ ደግሞ የወለላየ በረከታብ የልጅልጅ ልጅ ነው፡፡ 

     ሌላው መጨመር የምፈልገው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አሮጌው ቄራ ሰፈር ትኖር የነበረችው አክስቴ ወ/ሮ ማንጠግቦሽ እምሩ፤ ከገብሩ ማሞ ዘሮችና ከዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ጋር ትገናኝና ትጠያየቅ እንደነበር አሁንም በህይዎት ካሉ ዘመዶቸ የምስማው ነገር ነው፡፡ በመጨረሻም በእኔ በኩል (በቅንዋት ማሞ) ያለው የዘር ሃረግ ሙሉ በሙሉ ተከታታይ ቢሆንም፤ በገብሩ ማሞና በምጥን ማሞ በኩል ያለው የዘር ግንድ ሙሉ በሙሉ ተከታታይ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለምሳሌ አለቃ ተክለ እየሱስ፤ ብላታ አቲከም የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም አባት ሳይሆኑ አያታቸው እንደሆኑ የሚገልጽ አረፍተነገር፤ ዶ/ር ስርግው ባሳተመው መጽሃፋቸው ወስጥ ይገኛል፡፡ ይህም እውነት ከሆነ፤ ራስ ቢትወደድ መንገሻ በአያታቸው ይጠሩ ነበር ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ከጥቂት አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለየው አጎቴ ግራዝማች ሽመልስ ወርቅነህ፤ ገብሩ ማሞ ወይም ደጃች ማሞ ወንዳጥርን እንደወለዱና ወ/ሮ እጅጋየሁም የወንዳጥር ልጅ ወይም የልጅልጅ ናቸው ብሎ የነገረኝ ሲሆን፤ በህይወት የሚገኘው የ92 አመቱ አጎቴ አቶ መኮነን ይልማ ግን፤ ወ/ሮ እጅጋየሁ የምጥን ማሞ ልጅ ወይም የልጅልጅ እንደሆኑ ገልጾልኛል፡፡ ስለሆነም የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከምን የልጅልጆችና የዶ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህን ልጆች ፈልጌና አስፈላልጌ ወደፊት ለማነጋገር እጥርና [ግዜ ሊወስድ ይችላል] የሚጨምሩት ወይም የሚያስተካክሉት ነገር ካለ ውጤቱን በሌላ ግዜ በጽሁፍ መልክ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ 

 

 

     

 

 

 

Filed in: Amharic