>

የክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ 108ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ  (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ 108ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ

 

 ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል
ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምረው ኢትዮጵያን በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉትና በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ፖለቲከኞች መካከል በጥንካሬያቸውና በአዋቂነታቸው ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉት ‹‹የምንጊዜም ወርቃማው ኢትዮጵያዊ ላዕከ መንግሥት (Diplomat)›› ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የተወለዱት ከዛሬ 108 ዓመታት በፊት (መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም) ነበር፡፡
ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ውክልናና ጥቅም እንድታገኝ ያደረጉት ተጋድሎ ከማንም ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ሊሰወር የማይገባ አኩሪ ጀብድ ነው፡፡ ቀን በባቡር፣ ሌሊት ደግሞ በመርከብ እንዲሁም በአውሮፕላን ያለምንም እረፍት ለበርካታ ቀናት እየተጓዙ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ደክመዋል፡፡
ገና በወጣትነታቸው በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፤ አፋምቦ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላና ኤርትራን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከነበሩ ቅኝ ገዢ አገራት ግዛትነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሰሩት ስራም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡
ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከመወከልና ለጥቅሟ ከመሟገት በተጨማሪ፣ እድገት እንድታስመዘግብና የበለፀገች አገር እንድትሆን የሰሩት ስራም በዋጋ የማይተመን ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከምትመካባቸው ግዙፍ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሰረት የክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡
ጀግኖቿን ቅርጥፍ አድርጋ እየበላች ጠላቶቿን ግን አንቀባራና አሽሞንሙና የምታኖረው እድለ ቢሷ ኢትዮጵያ፣  ለባለውለታዋ ለአክሊሉ ሀብተወልድ ውለታና በጎ ስራም ምላሿ በጥይት ደብድቦ መግደል ሆነ፡፡ ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ  ቀን ከሌሊት እየተጓዙ ለኢትዮጵያ ጥቅም እንዳልደከሙ ሁሉ፣ እረፍት አጥተው ለኢትዮጵያ እንዳልተሟገቱ ሁሉ … ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከሌሎች 60 ኢትዮጵያውያን ጋር በደርግ ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
 የክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አበርክቶ እንዲህ በቀላሉ የሚዘረዘር አይደለም፡፡ ለበለጠ መረጃ እርሳቸው ፅፈውት ለመርማሪ ኮሚሽን (1967) ያቀረቡትና የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ፕሬስ ‹‹የአክሊሉ ማስታወሻ›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን  ጽሑፍ መመልከት ይቻላል፡፡
ፀሀፌትዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ እና አበርክቷቸው 
• መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ/ም የተወለዱት እኚህ የአገር ባለውለታ : በለጋ እድሜያቸው በዓለም መንግስታት መሐበር (League of Nations) የኢትዮጵያ ጰሐፊ ሆነው ሰርተዋል ።
• የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተሰሩ ታላላቅ ስራዎችና ተቋማት ምስረታ በብዙው መስኮች የተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ምስረታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ።
•አፋምቦ ጋምቤላ ኦጋዴንና ኤርትራን ከቅኝ ገዢዎች በመንጠቅ የኢትዮጵያ ግዛት እንዲሆኑ የአምበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል ።
• እኚህ ታላቅ ዲፕሎማት ኢትዮጵያን በአለምአቀፍ መድረኮች በመወከል የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር ከነ ዶ/ር ምናሴና ክቡር ከተማ ይፍሩ ጋር በነበራቸው ጥምረት የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንም በመመስረት በሀገራችን ውጪ ጉዳይ ታሪክ የምንጊዜም ወርቃማው ዘመን ሆኖ በታሪክ እንዲታወስ ታላቁን ሚና ተወጥተዋል ።
• አለመታደል ሆኖ ጉቶዎችን አንግሶ ዋርካዎችን በሚገለው ፖለቲካችን አይተኬና የምንጊዜም ታላቁ ዲፕሎማት በነብሰ በላውና አረመኔው #የደርግ ጁንታ ኅዳር 14/1967 ዓ/ም ከስልሳዎቹ ጋር በግፍ ተገደሉ ።
• ባለወለታዎቻችንን እንዘክር እላለሁ ።
መልካም ልደት ለታላቁ ዲፕሎማት!
Filed in: Amharic