>

ክቡር ጠ/ ሚ አብይ በባሌ ሶፈመር ዋሻ ያደረጉት ንግግር  ለአድማጭ  ግራያጋባ ስለሆነ፤ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ለምን አይጠየቁም (ታጠቅ መ. ዙርጋ )

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ በባሌ ሶፈመር ዋሻ ያደረጉት ንግግር ለአድማጭ  ግራያጋባ ስለሆነ፤ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ለምን አይጠየቁም?

 

ታጠቅ  መ.  ዙርጋ ፤

ማሳሰቢያ፦ ከትላንት ወዲያ ትላንት አይሆኑም ። ይህ ጽሁፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ትላንት በዓባይ ወንዛችን ግድብ በመገንባት ሂደት፣ትራምፕ ግብጽን ደግፎ በእኛ ላይ የሞከረውን ተጽኖ ባሳዩትን የእምቢተኝነት አቋማቸውና  በአንዳንድ አገር በቀል አፈንጋጭች ላይ በወሰዱት እርምጃ፤  ነሸጥ ነሽጥ ከመሰኘት ስሜት አኳያ ሳይሆን ከትላንት ወዲያ  በባሌ ሶፈመር ያደረጉትን  ንግግር  ስናዳምጥ ወይም በአማርኛ ተተርጉሞ ስናነበው ከነበሩን የተለያዩ ስሜቶች አንጻር እንድናየው ነው ።

ነገር ከሥሩ ውሃ ከምንጩ እንደሚባለው ኦሮምኛ አውቄ የጠቅላይ ምኒስትሩ የኦሮምኛን  ንግግር ይዘትና አቅጣጫ  ከአማርኛው ትርጉም በተሻል እረዳው ነበር ። ቋንቋ በዘረመር/በጄኔቲክ የሚገኝ ሳይሆን የአካባቢ ንብረት/ሃብት  ስለሆነ ፤  ከኦሮሞ ወገኖቼ ጋር ስላልኖርኩ ቋንቋውን የማወቅ እድል አልገጠመኝም ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ከላይ በተጠቀሰው ሥፍራ ያደረጉትን ንግግር፤ እንደ አማርኛው ትርጉም  ከሆነ ግልጽ የሆነና ግልጽ ያልሆነ  አውዶች/ኮንቴክስት አሉት ።

ሀ)  ግልጽ የሆነው  የንግግራቸው አውድ ፦ የወቅቱ የኢትዮጵያ በትረ አገዛዝ ወይም ሥልጣን  ኦሮሞችን  የበላይ ያደረገ ወይም ኦሮሞችን ያማአከለ (Oromo supremacy or Oromo centered)መሆኑንና  የኢትዮጵያ ህብረ ብሄር፣ብሄረሰቦች ፓርቲ የተባልነው ‘የብልጽግና ፓርቲ’ የኦሮሞች መሆኑን መናገራቸው ነው ። ይህ ማለት የብልጽግና ፓርቲ ኅብረቶች/ኮልሽን የሆኑትን ፦ አዴፓና ደኢህዲን እንዲሁም የዚሁ አጋር የተባሉትን  የሶማሌ፣የአፋር፣የቤኔሻንጎል፣ የሥልጤ ወዘተርፈ  ሕዝብ ተወካዮች አጃቢዮች ብቻ  ወይም ምናባዊ እውነታ (virtual realist) መሆናቸውን የሚያሳይ አይሆንምን ?

ለ) ግልጽ ያልሆኑ የንግግራቸው አውዶች ፦ ከዚህ በታች የነጠብኳቸውን ዓይነት ንግግር ሲያደርጉ እያንዳንዱን ቃላት፣እያዳንዱን ሃረግ እና እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ሰንጥቆ የሚያይና የሚተች ማኅበረሰብ ያለበት ዘመን መሆኑን በመዘንጋት ወይም አውቀው ያደረጉት ንግግር  ስለሚሆን፤  ግልጽ ያልሆኑትን የጠቅላይ ምኒስተሩን ንግግር አውዶች  በቅጡ ለመረዳት ንግግራቸውን – በትኖ፣ ሰንጥቆ፣ አብጠርጥሮ ፣ አፍርሶ ወዘተርፈ  (deconstruct,dissect,anatomize etc ) አደርጎ  መተቸት  ያስፈልገዋል። እኔ ያን ያህል
እርቆ መሄዱን ትቼ ፣ በሚከተሉት ጥቂት  ነጥቦች ላይ አስተያየት አዘል ጥያቄዎች እጭናለሁ (will pose questions)

1.  ‘ኦሮሞ ያልሆነ ከቤተ መንግሥት ጠራርገን እናውጣለን’ – ይህ ማለት የቤተ መንግሥት <ለኔ ቤተ ጥፋት> የጸዳት ሠራተኞች፣ ምግብ አብሳዮች፣ እንግዳ አስተናጋጆች፣የቢሮ
ፀሀፊዮች፣ የአበባና የአትልት ተንከባካቢዮች፣ የልጆቻቸውን ሞግዚቶች፣ የጤና ባለሞያዎች  ወዘተ.. በሙሉ ኦሮሞ መሆን አለባቸው ማለት ነውን?

2  .‘ትላትና የሰበሩንን ሰብረናል ፤ ትላንትና ያዋረዱንን አዋርደናል’ ፦ እነማንን ነበሩ ኦሮሞን የሰበሩት? እነማንን ነበሩ ኦሮሞን ያዋረዱት?  በመስቀል አደባባይ በተከበረው
የሬቻ በዓል ዕለት የኦሮሚያ ክልል ፕረዝዴንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ያሉትን ግልባጭ አይደለምን? ‘ነፍጠኛ’’ የተሰኘው ቃል አለመጠቀማቸው  የተለየ ትርጉም ያሰጠው ይሆን?

3.  ‘እንደሚዳቆ እዚህም  እዝያም የሚሉትን እናሳያቸዋልን’ ፦ ሚዳቆቹ እነማን ይሆኑ? ወያኔዎች? ጀዋር? ሸኔ ኦነግ? ኦነግ? አባ ቶርቤ? መሮ? አንድ ኦሮሞ (ከማል ገልቹ)? ኦፌኮ? (እነ ፕሮፌሰር እስቂያስ፣ ጸጋዬ አራርሳና  ቡድናቸው)? አብን? ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጀት?

4.. ‘እኛ ሳንፈቅድ ማንንም ወደ ኦሮሞ ክልል እንዲመጣ አናደርግም’ – ያ ማለት ኦሮሞ ያልሆነ የትኛውም ብሄር ብሄረሰብ አባል የሆነ ፦ ነጋዴ፣ተሸክሞ አደር፣ ሽምኖ አደር፣ ቀጥቅጦ አደር፣ አንጥሮ አደር፣ ሾፍሮ አደር፣ አርሶ አደር፣ ቢሮ ሠራተኛ፣ ወታደር ወይስ ኦሮሞ ያልሆነ ባለሥ  ልጣን ለማለት ነው?

አማካሪያቸው  አርካበ እቁባይ፣ በቅርብ ግዜ የሾሟቸው  አዲስዓለም ባሌማ፣ በቅርብ ግዜ የሾሟቸው  ኦሮሞ ያልሆኑ ጀነራሎችና ባለልዩ ልዩ ማዕረጎች  የአዲስ አበባን ቤተመንግስት (ቤተ ጥፋት) የሚረግጡበት ሁኔት አይኖርም ማለት ነውን?

ከንግግራቸው  መዝዤ ከላይ በ ‘ለ’ ሥር  ካስቀመጥኳቸው  ነጥቦች በተለይ ከ(2 -4) ያሉትን ነጥቦች  መልዕክት ኢግልጽና ማንንም ነጥሎ ተጠንቀቅ የሚል  ይደለም።ስለሆነም
በአገራችን ፖለቲካ መድረክ የሚንቀሳቀሱትን  ሁሉ ፤ ይህ ዱላ ለእኔ  ይሆን እንዲሉና ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ  አደረጋቸው።  በዚህ ጉዳይ ከበርካታ  ኢትዮጵያውያን  ጋር  ስወያይ
ያገኘሁት የበርካታዎች  አስተያየት የሚያዘነብለው ፤ ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ  ማንንም  በጠላትነት እንዳይፈርጃቸው በስሌት ያደረጉት ንግግር  ነው’ የሚል ነው ።
ለወያኔዎች፣ ለጀዋርና ግብረ አበሮች የተሰነዘር ቢሆንስ?  ብዬ ጠየቅኳቸው ። “ እንደዚያ ግልጽ ቢያደርጉትማ  ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እስይ! ይበርቱ ! ከጎኖ ነን! በማለት ለድጋፍ ሰልፍ ይወጣ ነበር” አሉኝ። እኔም መቶ በመቶ እስማማለሁ አልኳቸው።

ብዙ ሃይሎች በጥርጣሬ  ከሚጠሏቸው  ግልጽ አድርገውት  ጥቂቶች ጠላት ቢያደርጓቸው አይሻልምን? አልኳቸው።  “ይሻላል! ጥያቄያችን አደባባይ አውጣልን “ አሉኝ። ስለሆነም ዙሪያ ጥምጥሙን (beating around the bush) ትተው  በ ‘ለ’ ሥር ስለተነጠቡትን  ነጥቦችን  አውድ ወይም ይዘት ለማን እንደሆነ እንዲያብራሩ ይጠየቁ እላለሁ

Filed in: Amharic