>
5:13 pm - Friday April 19, 7697

ካራማራ የኢትዮጵያውያን የድል ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ) ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ

ካራማራ የኢትዮጵያውያን  የድል ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ)

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ
 
እንደ መግቢያ 
  በ1950ዎቹ መጀመሪያና አጋማሽ ላይ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡባቸው አመታት ነበሩ ። የጣሊያን ሶማሊ ላንድና የብሪቲሽ ሶማሊላንድም በ1952 ነፃ ወጡና የሶማሊያን ሪፐብሊክ መሠረቱ ።
  ቀጥሎም ባለ 5 ኮከብ ያለው ባንዲራ አስተዋወቁ ። ትርጉሙም በኢትዮጵያ ፣ በኬንያ ፣ በጅቡቲ እና ሪፐብሊክ በመሠረቱት ሁለቱ ሶማሊላንዶች የሚገኝ መሬት የሶማሊያ ነው የሚል የታላቋ ሱማሊያ ህልም የሚያመለክት ነበር ።
  ከኢትዮጵያ ሉአላዊ መሬት ላይም አጠቃላይ ሐረርጌን ፣ ባሌን ፣ አርሲን ሲዳማንና ከፊል ሸዋን ለመጠቅለል የሚያስችል አዲስ ካርታ አዘጋጁ ።
  ጅቡቲና ኬንያ በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ለጊዜው እነሱን በመተው ነፃ ሀገር በነበረችው ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ይፈፅሙ ጀመር ። ኦብነግና ኦነግን የመሣሠሉ ተገንጣይ ቡድኖችን በማቋቋም የእጅ አዙር ጥቃትን አፋፋሙ ።
  ሶማሌዎች በ1953 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተከሰተውን የታህሳስ ግርግርን ተከትለውና በ1956 ዓ.ም. ላይ ከደፈጣ ጥቃት ወደ መጠነ ሰፊ የወረራ ሙከራ አደረጉ ። ሆኖም በጊዜው ቀጠናውን ይጠበቅ በነበረውና በጀግናው ሌ/ጀ አማን ሚካኤል በሚመራው 3ኛው አንበሳ ክ/ጦር ክፋኛ ተመትቶ ተመለሡ ።
   በ1962 ዓ.ም. ወታደሩ ጀነራል መሀመድ ዚያድባሬ በመፈንቅለ መንግስት የሶማሊያን መንግስት በትረ ስልጣን ተቆጣጠሩ ። የታላቋ ሶማሊያ ህልማቸውንም በይፋ ገልፀው ወታደራዊ ዝግጅታቸውን አጧጧፉት ። የመንግስታቸው ርዕይቶ አለምም በይፋ ሶሻሊዝም መሆኑን አወጁ ።
  በውጤቱም ከሶቪየት ህብረት በገፍ ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቅና ወታደራዊ ኃይላቸውን ለተከታታይ 7 አመታት ማፈርጠም ቀጠሉበት ። በውጤቱም 7 እግረኛ ክፍለ ጦር ፤ 600 ታንኮችን እና ሌሎች የያዘ 4 ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር እንዲሁም 70 አውሮፕላኖችን የያዘ ግዙፍ የአየር ኃይል ገነቡ ።
  በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሌላ የታሪክ ሂደት ላይ ነበረች ። የየካቲት 1966ዓ.ም. አብዮት ተከትሎ ቀኃሥ ከዙፋን አውርዶ መስከረም 2 /1967 ዓ.ም. ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊው ደርግ በበርካታ ጉዳዬች ተጠምዶ ነበር ።
  በሰሜን ነፍጥ አንስቶ የሚታገለው ሻእቢያና ጀብሃ ከአሥመራ ፣ ከፊል ምፅዋና ባሬንቱ በስተቀር ቀሪውን የኤርትራ ክ/ሀገር ተቆጣጥረው ነበር ።
  ኢዲዩ በጎንደር ፤ ህወኃትም በትግራይ መንግስትን በመፋለም ላይ ነበሩ ። በመሃል ሀገርና በሌሎች አከባቢዎችም ኢህአፓና ደርግ በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር ደም ይፋሰሱ ነበር ።
  ተቀናቃኝ ሀይሎቹም በመንግስት ላይ የሚፈፅሙት ጥቃት አልበቃ ብሏቸው ሶማሊያ የምታደርገው ጦርነት ልክ ነው ፤  አድሃሪ ጦርነት የሚያደርገው ደርግ ነው በማለት ሻእቢያ ፣ ህወኃት ፣ መኢሶን ፣ ኢህአፓ ፣ ኦነግ እና ጀብሃ የፕሮፓጋንዳ ድጋፋቸውን ለሶማሊያ ይሰጡ ነበር ።
በውጤቱም ኢትዮጵያ እጅግ ተዳክማ ነበር ።
    በአጠቃላይ ዚያድባሬ ያንን ሁሉ ግዙፍ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ የኢትዮጵያን የመንግስት ስልጣን የያዘው ደርግ ግን ከንጉሱ የተቀበለው 4 ክፍለ ጦሮች ብቻ ነበሩት ።
  እነርሱም 1ኛ ክ/ጦር (ክቡር ዘበኛ ) ፤ 2ኛ ክ/ጦር ኤርትራ የነበረው ፣ 3ኛ ክ/ጦር ምስራቅ (ኦጋዴን) የነበረው እና 4ኛ ክ/ጦር ደቡብ ነገሌ/ቦረና የነበረው ናቸው ። ከነዚህ ውጭ ተጨማሪ ኃይል አሠልጥኖና አስታጥቆ ወደ ሰራዊቱ አልጨመረም ነበር ።
   የጦርነቱ ውጥረት እያየለ ሲመጣ የተለያዩ የማሸማገል ጥረቶች በተለያዩ አካላት ቀጥለው ነበር ። የመጨረሻው የፊደል ካስትሮ ደቡብ የመን ኤደን ላይ ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት በዚያድባሬ እብሪት ምክንያት ከሸፈ ።
  ፊደል ካስትሮም በዚያድባሬ መጠን ያለፈ ንቀት እጅግ ተቆጡ ፤ በአለማቀፍ ህብረተሰባዊነት መርህ መሠረትም ኢትዮጵያንም ማገዝ እንዳለባቸው ወሰኑ ። እያንዣበበ ያለው የመወረር አደጋ ያሰጋቸው የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. በብሔራዊ የቴሌቭዢን ጣቢያ ብቅ ብለው ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ መልእክት ለህዝባቸው እንዲህ በማለት አስተላለፉ ። ሀገርህ ፣ ህልውናህን እና አብዮትህን አድን ፤  ተነስ ! ታጠቅ ! ዝመት ! እናሸንፋለን ! ብለው ተናገሩ
  የእናት ሀገር ጥሪውን ተከትሎ ከአራቱም የኢትዮጵያ መአዘናት ለሀገሩ ሉኣላዊነት ቀናኢ የሆነው ህዝብ በገፍ ወደ ታጠቅ ማሰልጠኛ ጣቢያ ተመመ ።
  በመጀመሪያ የከፋ ክ/ሀገር ዘማች ሚሊሻ ቀጥሎ የጎጃም ክ/ሀገር ሚሊሻ እያለ ወደ 300,000 ሺህ የሚጠጋ ህዝባዊ ሰራዊት ለስልጠና ታጠቅ ከተመ ። ታጠቅ አዲስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ነበር ።
  300,000 ለሚሆነው ሰልጣኝ የሚበቃና የሚመች መሠረት ልማት አልነበረውም ። ታጠቅ በቂ መጠለያ ፣ በቂ ማብሰያ ፣ በቂ መፀዳጃ ፣ በቂ ጠመንጃና ፣ … አልነበረውም ። ወቅቱም ዝናብ ይጥል ስለነበር የጭቃው ነገርም ለስጠናው ስራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር ።
  ከሀረር የጦር አካዳሚና ከሆሎታ ገነት ጦር ት/ቤት ስልጠና ላይ የነበሩት እጩ መኮንኖች ትምህርታቸውን አቋርጠው ከሌሎች የጦር ክፍሎች ከተውጣጡ አሠልጣኞች ጋር በመሆን ሰልጣኝ ህዝባዊ ሰራዊቱን ለማሠልጠን ታጠቅ ከተቱ ።
  የእናት ሀገር ጥሪው የተቀበለው የአዲስ አበባና የአከባቢው ህዝብም ዘማች ሚሊሻውን ሊደግፍ ወደ ታጠቅ ተመመ ። የእድር ድንኳኖች ፣ የማብሰያ ድስቶች ፣ የመመገቢያ ሰሀኖች ፣ የመጠጫ ኩባያዎች ፣ …በገፍ ወደ ታጠቅ ተጫኑ ። እናቶች በዓድዋው ዘመቻ የፈፀሙትን ገድል ለካራማራም ደገሙት ።
 በወቅቱ በኢህአፓ የሚደረገውም አፍራሽ ፕሮፓጋንዳና ማስፈራሪያ ሳያስፈራቸው ወደ ታጠቅ አቀኑ ።
በጉዟቸው ላይም
ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል …
በማለት የነሱንም ፣ የዘማቹንም ወኔ ያበረቱት ነበር ።
  በስራቸውም በፈረቃ ለሠልጣኙ እርጥብ ምግብ ያዘጋጃሉ ። ሚሊሻው ወደ ግንባር ይዞት የሚሄደውን ደረቅ ስንቅ ይቋጥራሉ ። ወንዶችም በፊናቸው እንጨት ይፈልጣሉ ፣ ውሃ ይቀዳሉ ፣ የሰልጣኙን ልብስ ያጥባሉ ።
  ኢትዮጵያ የቶሎ ቶሎ ስልጠናውን በተያያዘችው ወቅት ለተከታታይ 10 አመታት ሲሰለጥንና በገፍ ሲታጠቅ የነበረው የዚያድባሬ ሀይል ሐምሌ 3 ፤ 1969 ዓ.ም ላይ በሰፊው የኦጋዴን ክልል ላይ በርቀት ነጥቦች ላይ ተራርቀውና እርስበእርስ ለመረዳዳት በማይችሉበት ሁኔታ የነበሩትን የ3ኛ ክ/ጦር አካል የሆኑትን የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊቶችን የተለያዩ ክፍሎችን መግፋት ጀመረ ።
  የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚቻለውን መከላከል ቢያደርግም በነበረው ከፍተኛ የኃይል አለመመጣን ምክንያት ሰራዊቱ እየጣለና እየወደቀ ለማፈግፈግ ተገደደ ። ሶማሊያም ገላዲን ፣ ቀብሪደሃር ፣ ደጋሀቡር ፣ ጎዴ ፣ ሙስታሂል ፣ አይሻ/ደወሌ ፣ ገርባሳ ፣ ጭናቅሰን ፣ …የሚገኙ የሠራዊት ክፍሎችን በመግፋት በምስራቅ 700ኪ.ሜ ፤ በደቡብ 300 ኪ.ሜ. ጠልቃ በመግባት የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት በኃይል ተቆጣጠረች ።
   ጅጅጋን ተቆጣጥረው የሀረርና ከተማ በመድፍ ቀለበት አስገብተው መደብደብ ተያያዙት ፤ የድሬዳዋም ከተማ አፍንጫ ስር ደረሡ ።
ሶማሊያ በተቆጣጠረችው አከባቢ የሚኖረውን ህዝብ በዚያድባሬ ሃይል የባርነት ቀንበር ስር ወደቀ ። ንብረት ወደ ሞቃዲሾ ተጋዘ ። ሴቶች ተደፈሩ ። በርካታ ሰላማዊ ዜጎችም በግዞት ወደ ተለያዩ የሶማሊያ ከተሞች በገፍ ተጋዙ ።
  በወቅቱ ሶማሊያ እጅግ ዘመናዊውን ስታሊን ኦርጋን (BM ) ጨምሮ አይነተ ብዙ ሩስያ ሰራሽ የጦር መሳሪያ ታጥቅ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በብዛት የታጠቀችው አሜሪካ ሰራሽ መሳሪያ ነው ።
   በጊዜው የኢትዮጵያ ትጥቅ ከሶማሊያ ጋር ሲነፃፀር ኃላቀር የነበረ መሣሪያ ነበር ።
   በወቅቱ  የጂሚ ካርተር ይመራ የነበረው የአሜሪካ አስተዳደር በቀኃሥ ዘመን የተፈፀመውን የተከፈለበት የጦር መሳሪያ ግዢ ውል እንዳይፈፀም በማገዱ ኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ ላይ ወድቃ ነበር ።
  ኢትዮጵያም የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ምስራቁ የሶሻሊስት ጎራ ፊቷን አዞረች ። በታህሳስ 1968 ዓ.ም ሶሻሊዝምን በማወጅ አጋርነቷን አሳይቷ ስለነበር ከምስራቁ አለም አመርቂ ድጋፍ ማግኘት ጀመረች ።
  ሶቪየትም ከሶማሊያ ጋር መቃቃር ስለጀመረች ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር በብዛት የጦር መሣሪያ ድጋፍና የባለሞያ /አማካሪዎች እገዛ አደረገች ።
  እጅግ ፈታኝ ስራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ሰራዊቷንም ከአሜሪካ ሰራሽ መሣሪያ ስርአት ወደ ሶቪየት መሣሪያ ስርአት ሽግግር በሚያስደንቅ ፍጥነት አካሄደች ።
  ታጠቅ ጦር ሰፈር ሲሰለጥን የከረመው ህዝባዊ ሰራዊትም በሀገራዊ ወኔና በስልጠና ታግዞ ከኮሪያ የመጣ ሬንጀር ፋቲግ ለብሶ ለሰኔ 18 ለአደባባይ ሰልፍ ትርኢት ተዘጋጀ ።
  በእለቱም የነበረው የሰልፈኛው ሰራዊት እርዝማኔ በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በጣም ረጅም ነበር። ጫፉ መስቀል አደባባይ ሆኖ መጨረሻው ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፍያ /ጦር ኃይሎች ይደርስ ነበር።
  በወቅቱ ሰልፉን ይታዘቡ የነበሩ የተለያዩ ሀገሮች ታዛቢዎች እና ወታደራዊ አታሼዎች የደማቁን ሰልፍ እና የሰራዊቱን ብዛት በመጠራጠርቸው ከመነሻ እስከ መድረሻው በሂሊኮብተር ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ነበር ያመኑት ።
  በመስቀል አደባባይ የተገኘዉም ህዝብ ለሰራዊቱ ይሰጥ የነበረው ሞራል እጅግ አስደማሚ ነበር።  ህዝባዊ ሰራዊቱም ይህን ዜማ እያዜመ ለሀገሩና ለክብሩ መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀቱን በከፍተኛ ወኔ ገለጸ።
ለአንድነቱ
ድሉ እንዲሰምር የነፃነቱ
ወጣ ወረደ : ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ ::
አለኝ አደራ
የተቀበልኩት :ከጀግኖች አውራ
እንድትኖር : ሀገሬ ታፍራ ተከብራ
ብሎ ተነሳ : ህዝባዊው ሰራዊት
  ጉዞ ጀመረ
  እየዘመረ
እንዲያበራ
የነፃነት ድል : የአንድነት ጮራ
አውለበለበ የድል በንዲራ
                        እንዲያበራ ::
………….
ሀገሬ
መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ
ነፃነቴ
ውርሱ የአባቴ
ተደፍሮ ማየት : አልሻም መብቴ
ብሎ ነጎደ : ህዝባዊው ሠራዊት
                                  ጉዞ ጀመረ
                                   እየዘመረ ” …
ህዝባዊ ሰራዊቱም በ9ኝ ክፍለ ጦሮች ተዋቅሮ 8ኛ፣ 9ኛ ፣ 10ኛ እና 11ኛ ክ/ጦሮች እየፈከሩና እየሸለሉ ወደ ምስራቅ ዘመቱ ። 12ኛ ክ/ጦር ወደ ደቡብ ዘመተ ። 14ኛ ፣ 15ኛ ፣ 16ኛ እና 17ኛ ክ/ጦሮችም ወደ ኤርትራና ትግራይ ተላኩ ።
  በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አቅምም በፊት ከነበራት 4 ክ/ጦር ታጠቅ የሠለጠነው 9ኝ ክ/ጦር ሲጨመርበት የሰራዊቷ አቅም ወደ 13 ክፍለ ጦሮች አደገ ።
  የሶሻሊስት ኩባ ፕሬዝደንት ጓድ ፊደል ካስትሮም አንጎላ ከነበረው ሰራዊታቸው 18,000 ያህል የእግረኛ ተዋጊና የሜካናይዝድ ኃይል ከህክምና ባለሞያዎች ጋር በጀነራል ኦርላንዶ ኦቾዋ አማካይነት እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ ኢንዲንቀሳቀስ አዘዙ ።
  ደቡብ የመንም እስከ 2000 የሚደርስ ጠንካራ የመድፈኛ ብርጌድ ድጋፍ አደረጉ ። ሶቪየት ህብረትም በማርሻል ፔትሮቭ የሚመራ ልዩ ልዩ የአማካሪ ቡድን ላከች ።
  ኢትዮጵያ 300,000 ሚሊሻ በአጭር ጊዜ አሰልጥና ከማስመረቋ በፊት ሶማሊያ ወረራ በካሄደችበት ወቅት ለንፅፅር ይጠቅም ዘንድ የኢትዮጵያና የሶማሊያ አጠቃላይ የጦር አቅም ንፅፅር ይህን ይመስላል ።
                                        ሶማሊያ            ኢትዮጵያ 
ሀ/ እግረኛ ክ/ጦር               8                      4
ለ/ ኮማንዶ ብርጌድ             4                      0
ሐ/ ሜካናይዝድ ክ/ጦር     4                      0
መ/ታንከኛ ብርጌድ              4                      1
ሠ/ BM /ስታሊን ኦርጋን      125                  1
ረ/ ታንክ                                608                  132
ሰ/ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ    253                  51
ሸ/ ተዋጊ አውሮፕላኖች          65                    8
  በመቀጠል በከፍተኛ እልህና ቁጭት የተሞላው ህዝባዊ ሰራዊት ከመደበኛ ጦሩ ጋር በመቀላቀል በታጠቀው ሀገራዊ ፍቅርና ወኔ ታግዞ በበርካታ ግንባሮች ተሠልፎ ነባሩን ጦር በማጠናከር የሶማሊያን ተጨማሪ መስፋፋት መግታት ጀመረ።
  በጀግንነት ጥሎ መውደቅ ተያያዘው ። ይህም አልበቃ ብሎት በዘመች ሚሊሻ አማካይነት በነፍስ ወከፍ መሳሪያ እየታገዘ የሶማሊያን ታንኮች በአስደናቂ ጀብድ ይማርክ ገባ።
  በወረራ ከተያዘው ህዝብ ጋርም እየተባበረ የሶማሊያን ወራሪ ማርበድበድ ተያያዘው ። ይህ ሀገርን ከወረራ ለማዳን ርብርብ በሚካሄድበት ወቅትም ከመነሻው የሶማሊያን ወረራ ደግፎ  የቆሙ እንደ ኢህአፓ አይነት ሃይሎች በጦሩ ውስጥ አስርገዉ ባስገቧቸው ኃይሎች ርብርብ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያን ሰራዊት በሚያሳዝንን በሚያሳፍር መልኩ ከኋላ ይወጉት ነበር ።
  በጣት የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን ግን እጅግ የበቁ አብራሪዎቹን የያዘው ጀግና የኢትዮጵያ አየር ኃይልም አለምን ባስደመመ የመዋጋት ብቃቱ በቁጥርና በዘመናዊነት የሚበልጡትን የሶማሊያን ሚጎች በአየር ላየር ውጊያ ከሰማይ ወደ መሬት እንደ ዝናብ ያራግፋቸው ጀመር።
  በአጭር ጊዜ የሶማሊያን ጀቶች ከኢትዮጵያ የአየር ክልል ካፀዳ በኋላ የሶማሊያ ግዛት ዘልቆ በመግባት የነዳጅ ዲፖዎችን ፣ የስንቅና ትጥቅ መጋዘኖችን ፣ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳዎችን ማውደም ተያያዘው ።
  አከታትሎም በሰፊው አውደ ግንባር የተጠመዱትን እሳት የሚተፋትን የጠላትን ስታሊን ኦርጋኖችን ላንቃቸው ዘጋቸው ። የእደላ መስመሮችን ቆረጣቸው።
  የአየር ኃይሉ ጀግኖች አብራሪዎቹ ያለምንም እረፍት በመብረር በአጠቃላይ የወራሪውን ኃይል አናት አናትን እየቀጠቀጡ አዳከሙት ።
የአየር ኃይሉን ሽፋን እየተጠቀመም ህዝባዊ ሰራዊቱ ከህዳር አጋማሽ 1970 ዓ.ም ጀምሮ ከመከላከል ደረጃ ወደ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሸጋገረ ።
   መሪር መስዋእትነት እየከፈለ የሶማሊያን እግረኛና ሜካናይዝድ ጦርን አከርካሪ መስበሩን ቀጠለበት ። በጠላት ከበባ ወድቀው የነበሩት ድሬዳዋን እና ሀረር ከተሞችን ከጠላት መንጋጋ አስጥሎ ለቀጣዩ ወሳኝ ፍልሚያ ተዘጋጀ
የካቲት 23 /1970 ዓ.ም የዓድዋ ድል እለት የትዮጵያ ጦር  በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የጎህ መጥቃት ዘመቻ ከፈተ ። የሶማሊያ ጦርም ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ብሎ ካልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ ። ጅጅጋንም ላለመልቀቅ ተሟሟተ ። ሶማሊያ በዚህ መደናገጥ ውስጥ እያለች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተባት ። የሶማሊያም ሰራዊት ጅጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል ። በመሆኑም ከጅጅጋ በስተምእራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ ። ሆኖም በለስ አልቀናውም ።
ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሰራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም ። በውጤቱም የካቲት 26 ረፋድ ላይ በካራማራ ከባድ ሽንፈት ተጎነጨ ። በውጤቱም ከሞትና መቁሰል የተረፈው የጠላት ሠራዊት መሳሪያውን እያንጠባጠበ ጅጅጋን በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር ፈረጠጠ ።
እሁድ የካቲት 26/1970 ዓ/ም ላይ በአከባቢው የነበረ ሰራዊት ወድቃና ተዋርዳ የነበረችውን  ሰንደቃችንን መልሶ ከፍ አድርጎ በክብር ሰቀለ ። የዛሬ 42 አመት እንዳይድን እንዳይሽር ተደርጎ የተሰበረው የዚያድባሬ ተስፋፊ ኃይል በቀጣይ ቀናቶች ጦርነቱን በይፋ አቁሞ በወረራ ተቆጣጥሯቸው ከነበረው ከቀሪ የኢትዮጵያ ሉኣላዊ መሬቶች ተጠቃሎ ወጣ ። ይህ ድል እውን እንዲሆን ግን የበርካታ ውድ ኢትዮጵያዊያን የደምና የአጥንት መስዋእትነት አስፈልጎ ነበር ። ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያንና የደቡብ የመናዊያን ውድ የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል ።
የደረሰው ጉዳት በአጭሩ ይህን ይመስላል ።
ሠራዊት       የሞተ           የቆሠለ          የተማረከ
ኢትዮጵያ         18,000        29,000         450
ኩባ                  163                                   1
የመን                100
ሶማሊያ         15,900       26,200         1,785
  የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉአላዊነት ያላቸውን ቀናኢነት ቀፎ እንደተነካ ንብ በህብረት በመቆም ገልፀውታል ። ለሠንደቃቸው ያላቸውን ልባዊ ፍቅር ውድ መስዋዕትነት በመክፈል በደማቅ የደም ቀለም ፅፈውታል ። ለዘመናት የተገመደው የማይበጠስ አንድነታቸውን በደም ፍሳሻቸውና በአጥንት ፍላጫቸው በድጋሚ በፅኑ መሠረት ላይ ገንብተውበታል ።
   ከታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥሎ የኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድነት ማሳያ የሆነው የካራማራ ጦርነት ለማመን የሚቸግሩ በጀብድ የተሞሉ ጀግንነቶች በተናጠልና በቡድን ተከናውነውበታል። ተዘርዝረው ከማያልቁ የሠራዊቱ ጀብዶች መካከል ለምሳሌ ያህል ሁለቱን ልጥቀስ ።
  የሀረር አካዳሚና የበረራ ት/ቤት ጥምር ምሩቅ የሆኑት የአዲስ አበባው ፍሬ  የአየር ኃይሉ ነብር ጀግናው ብ/ጀ ለገሰ ተፈራ በF5-E ጀታቸው አማካይነት በአየር ላየር ላይ ውጊያ አምስት የሶማሊያ ሚግ 21 ጀቶችን በመምታት ከአየር ወደ መሬት አራግፏቸዋል።
  በርካታ ጀብድ ፈጽመው የድሉ መጨረሻ ሰአት ላይ በፊልቱ ግንባር ላይ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በጠላት ተይዘው ለ11 አመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የስቃይ ህይወት አሳልፈው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
  ለወደር የለሽ የጀግንነት ስራቸውም በጊዜው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ የሆነውን የህብረተሠባዊት ኢትዮጵያ ወደር የለሽ የጀግና ሜዳይ ተሸልመዋል ።
  ሌላው ጀግና ደግሞ የእናት ሀገር ጥሪ ሰምቶ በለጋ እድሜው ከቀድሞ ወለጋ ክ/ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ የመጣው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ነው።
  ጀግናው አሊ በአቡሸሪፍ ግንባር  ሶስት የጠላት ታንኮችን በእጅ ቦንብ በማቃጠል በግንባሩ ለነበረው ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ። ለዚህም ስራው የላቀ የጀብድ ሜዳይ ተሸላሚ ሆኗል ።
  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት የብሔርና የሀይማኖት አጥር ሳያግዱት በጠነከረ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ደሙን አፍስሶ ፣ አጥንቱን ከስክሶ ነው ይህንን ታላቅ ድል ማስመዝገብ የተቻለው።
   ይህ ድል ዕውን እንዲሆን ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያን የሩሲያውያንና የደቡብ የመን ውድ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል።
   ዘንድሮ 42 ዓመት የሚሞላውን የካራማራ ድል የመታሠቢያ በዓል ነገ ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት የመታሠቢያ ፓርክ (ትግላችን ሐውልት) ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ ሀገር ወዳድ እና ታሪክን ዘካሪ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዕለቱ በቦታው በመገኘት የድሉን በዓል ላይ እንድትታደሙ ከወዲሁ እንጋብዛለን።
   መንግስት በቀጣይ ይህንን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መንፈስ በህይወትና በአካል መስዋዕትነት የከፈሉበትን ታላቅ ሀገራዊ የህዝብ ድል ትኩረት ሰጥቶት በቀጣይ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲከበር እና ትውልዱ አባቶቹ ከሰሩት ከዚህ የጋራ የድል ታሪክ ተምሮ አንድነቱን እንዲያጠነክር አበክሮ እንዲሰራ ጥሪ እናስተላልፋለን።
ተፈፀመ!!!!
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖቹ የካራማራ ሠማእታት ይሁን  !!!
ኢትዮጵያ ምንግዜም በክብር ትኑር !!!
Filed in: Amharic