>
5:13 pm - Sunday April 19, 8437

የአንድ ወጥቶ አደር ታሪክ!!! (ይታገሱ ጌትነት)

የአንድ ወጥቶ አደር ታሪክ!!!

ይታገሱ ጌትነት
 
* የ42ኛ አመት የጅጅጋ ድል መታሰቢያ!!!
ተርብ ነበር.፣ “የት አረፈ?” የማይባል ፈጣን፣ “የትነው ያለው?” ተብሎ የማይጠየቅ ተስፈንጣሪ፤ ወገን ካሉት  ገደል ይገባል፣ ክብር ሲሉት ጸጉሩ ይቆማል፤ የተበደለን ከሚያይ ቢሞት ይመርጣል፡፡ ሁሌም ከተገፉት ጋር ነው፡፡ ወጣት የነብር ጣት ነው፣ ከ28 አንድ ቢያጎድል አሊያ ቢያክል ነው፡፡ አባቱ እንዲህ ነው ያሳደገው፡፡ አባቱ ገበየሁ በድፍን ሀገር ስሙ ሲነሳ ጎበዝ የሚንቀጠቀጥለት ወንድ ነበር፡፡ ወንድ የወንዶች ቁና፣ ሸፈተ እንዳይባል ከሰው ተቀላቅሏል፤ ደህነኛ አይሉት ህግ የማይገዛው ሳተና፣ ዕብሪተኛ አይሉት ለተበደሉ ራሱን ከሳት የሚጨምር እንጂ በራሱ ጉዳይ አይጋጭ ነገር፡፡ ልጁም እንዲያ ነው – የአባቱ ልጅ፡፡ ቀለም መቁጠር ከለመደበት ሃገር “አንዱ ደም መመለሻ ከሚያደርግህ ጥፋ” ብላ ከወንድሟ ጋር ወደንጉሥ ሃገር የላከችው ስሱ እናቱ ናት፡፡
ንጉሥ ሃገር ካዲስ-አባ ሲገባ አጥንቱ ያልጠና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፡፡ እንደመጣ ከቀለምም ከሥራም ጋር ግብ ግብ ገጠመ፡፡ ቀናው ከግል ድርጅት ተቀጥሮ ወዝ አደር ተባለ፡፡ አብዮቱ ሲመጣም የላብ አደሩ አካል ከመሆን በላይ በላቡ አደረ-በንግድ ማተሚያ ቤት ውስጥ፡፡ አገር በቀይ እና ነጭ ሽብር ሲታመስ የተፈሪ መኮነን ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር፡፡ የትኛውም ቡድን ውስጥ አለመመሰጉ ምክንያት ይደንቃቸዋል፣ እህቶቹ፡፡ የአብዮቱ ጣጣን ቢሻገርም የሚመሰግበት ሌላ ጉዳይ አላጣም፤ “የእናት ሃገር ጥሪ!”፡፡
ሚያዚያ 4 1969 ዓ.ም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትናንት የበቀለችው የኢጣሊያ ቅኝ ሱማሊያ በእብዱ መሪዋ ዚያድባሬ ቅዠት ሰክራ የሀገርን ድንበር አልፋ ወራራ መፈጸሟ ይፋ ሆነ፡፡ ሱማሌያ ከ1952 ዓ.ም አንስቶ ኢትዮጵያን ስትወጋ የነበረች ቢሆንም እንደአብዮቱ መጀመሪያ አመታት ኢትዮጵያን ፈረካክሳ ለመጣል የተመቸ ጊዜ አላገኘችም፡፡ በዚህም አድዋና ማይጨው ላይ እንደገጠመን ሁሉ የሀገር ውስጥ ምንደኞች ከጎኗ ቆመዋል፡፡  ኢሳያስ አፈወርቂ፣ መለስ ዜናዊ፣ ዋቆ ጉቱ፣ ወልደ አማኑኤል ዱባለ እና ሌሎች ለብሔረሰብ ነጻት ታጋዮች ነን ያሉ አማጽያን የሱማሌን ፓስፖርት ይዘው የሚንቀሳቀሱ እንደነበሩ አንዳንድ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፣ ግቡም ያው ሞግዚቷ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመጣል በዘር መበተን ሁነኛ መንገድ ነው ብላ የጋተቻት መርዝ ውጤት ነው፡፡ እነኢህአፓም ጭቁን ጭቁንን አይወጋም በሚል “Opportunities’” ዝንባሌያቸው የራሳቸውን ሀገር በቁሟ ነግደውባታል፡፡
ያም ቢሆን “ከውስጥ ፖለቲካዊ ቁርቁሾች በላይ ሀገር ትልቃለች፣ ባንዲራ ትከብራለች” ያሉ ከ3 መቶ ሺህ በላይ ከሰሜን እስከደቡብ ከምዕራብ እስከምስራቅ የተሰባሰቡ ጭቁኖች በበጎ ፈቃደኝነት ህይወታቸውን ስለሀገራቸው ሊከፍሉ ተሰባሰቡ፡፡ ያ ወጣት፣ ያ ጥቃት እንቢ “ተርብ” ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት ወዝ-አደሩን ወክሎ ሀገሩን ከውርደት ሊታደግ አብረውት ከሚሠሩ 9 ላባደሮች ጋር (አንዷ ሴት ናት) በወዶ ዘማችነት ወደታጠቅ ጦር ሰፈር ገባ፡፡ በዚህ ጊዜ ገና የሁለት እና የሦስት ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ልጆቹን እቤት ውስጥ ትቶ ነበር፡፡ የሱ ወዶ ዘማችነትም ለልጆቹ ሀገር የማቆየት ህልም ነበር፡፡ የሦስት ወር ስልጠናውን ካከናወነ በኋላ ሰኔ 28 ቀን አለምን ጉድ ያሰኘው ሰልፍ ላይ ከታጠቅ ጦር ሰፈር እስከ አብዮት አደባባይ ተሰለፈ፡፡ ቀለም ቀመስና የከተማ ወጣቶች ከሆኑት መካከል ለሬዲዮ ኦፕሬተርነት ስልጠና ሲመለመሉ አንዱ “ተርቡ”ሆነ፡፡ ነሐሴ 8/ 1969 ዓ.ም ስልጠናውን አጠናቆ ወደምስራቅ ግምባር ተመድቦ የተፋፋመው ጦርነት ውስጥ ገባ፡፡
ጥቃት እምቢኙ፣ ሀገር ብርቁ፣ ዘመድ ወዳዱ “ተርቡ” ከሐረር እስከ ካራማራ በተደረጉት ውጊያዎች ውስጥ ግንባሩን ሳያጥፍ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተጋጥሞ ከወገኖቹ ጋር ተዋጋ፡፡ የጠላትን ሬዲዮ ከመጥለፍ የውጊያ ትዕዛዝን መሥጥሮ እስከመላክ ባሉ ሙያዊ ሥራዎች ውስጥ ተሳተፈ፡፡ እንደተራ ወታደር ተኩሶ ከመጣል ቁስለኛ እስከማግለል ደፋ ቀና አለ፡፡ ከስድስት ወር ባልዘለለ ፈጣን ውጊያ ሱማሊያ እግሯ ከተከለችበት የሐረርጌ እና የኢትዮጵያ ሱማሌ መሬቶች ላብ ላብ እስኪላት እየተገረፈች ስትፈረጥጥ ጀግናው የኢትዮጵያ ሰራዊት “ቀን ጥሎን ባንድ ሰሃን በላን”ን እየተረተ ልኳን አሳይቶ የጀግኖቹ አባቶች ደም በደማቸው እንዳለ አስመሰከሩ፡፡
እነ”ተርቡ” የመጨረሻውን የየካቲት 25/ 1970 ምሽት ውጊያ ካራማራን አስለቅቀው ቁልቁል ወደጅጅጋ ተወነጨፉ፡፡ ጊዜው የጥድፊያ የድል ሽታ የሚያሰክርበት ነው፡፡ የዚያድባሬ ጦር በልመና ያገኘውን ዘመናዊ መሳሪያ እያንጠባጠበ ቁልቁል ወደ መቋዲሾ እግሬ አውጪኝ በማለት ለይ ነው፡፡ ውጊያውን የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሻ/ቃ መንግሥቱ ሃይለማርያም በቦታው ላይ ሆነው ይመሩታል፣ እንደነ አብዲሳ አጋ አይነት ስመ ገናን ጀግኖች ጦሩን በቅርብ ሆነው ግፋ በለው ይሉታል፡፡ ሁሉንም እልህ እና ድል አስክሯዋል፡፡ በዚህ መሃል የ”ተርቡ”ሬዲዮ በሱማሊያ ጦር የሬዲዮ ጠለፋ ውስጥ ወደቀ፡፡ ተርቡን ቀን ከዳው፡፡ የድሉ ቀን ጅጅጋ መሬት ላይ ከጠላት በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ከምድብተኛ ጓደኞቹ ጋር ተሰዋ፡፡ ጌትነት ገበየሁ “ተርቡ” ወዶ ዘማቹ ወጥቶ አደር፣ ሀገሬን ባዩ ጀግና ሃገሬን ሰጥቶኝ ሞተ!!
አባቴ ክብሬ ነህ!!
Filed in: Amharic